Sunday, 16 August 2020 00:00

የአለማችን እጅግ ውዱ የፊት ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ተተምኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በእስራኤል የሚገኝ አንድ ታዋቂ የጌጣጌጥ አምራች ኩባንያ በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተተመነለትን እጅግ ውድ የፊት ጭምብል ባለፈው እሁድ ለእይታ ያበቃ ሲሆን፣ የጭምብሉ የመሸጫ ዋጋ 1.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ያቬል የተባለው ኩባንያ እያመረተው የሚገኘው ይህ የፊት ጭምብል ከ18 ካራት ነጭ ወርቅ የተሰራና በ3 ሺህ 600 ደቃቅ የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ጭምብሉ በቀጣዩ አመት ተጠናቅቆ ለሽያጭ እንደሚበቃም አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያመርተውን ይህንን እጅግ ውድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር መዥረጥ አድርጎ ለመግዛት የፈቀደ ገዢ መገኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአሜሪካ የሚኖር ቻይናዊ ነጋዴ ከመሆኑ ውጭ ስለ ግለሰቡ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለም ህዝቦች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተመቱና ለስራ አጥነት እየተዳረጉ በሚገኙበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ለአንድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ግፍ ነው የሚሉ አስተያየቶች መደመጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጭምብሉ 270 ያህል ግራም ክብደት ያለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ኮሮናን ለመከላከል በፊት ላይ አጥልቆ ለመንቀሳቀስ አመቺ ላይሆን እንደሚችል መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3116 times