Saturday, 15 August 2020 14:33

በኮሮና የሚያዙ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር መጨመር አሳሳቢ ሆኗል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  - እስካሁን ከ130 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
            - "ይህ ለኛ ጦር ሜዳ ላይ ሰራዊትን እየቀነሱ እንደመሄድ ነው"
            - በ2 ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ 66 ታራሚዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
                  

             በአገራችን የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት አምስት ወራት በአምስት ክልሎች ብቻ ከ130 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ታውቋል፡፡ እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙት የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መካከል አብዛኞቹ የተገኙት መደበኛ ህክምና በሚሰጥባቸው ተቋማት እንደሆነም ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው የጤና ባለሙያዎች መካከል አዲስ አበባ ከፍተኛውን ቁጥር መያዙ ቢነገርም ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ እንደተያዙ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የትግራይ ክልል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ35 በላይ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና፤ በትግራይ ክልል በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል መምህር የነበሩት ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ፣ ባለፈው ሳምንት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉም ተገልጿል፡፡ ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ ከመምህርነታቸው ባሻገርም የቫይረሱን ወረርሺኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ፈጣን ግብረ መልስ ቡድን መሪ በመሆንና በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ፣ የኮሮና ቫይረስ መረጃ ትንተና እና ትንበያ ክፍል ውስጥ ሲሰሩ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዶክተሩ ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ አንዲት ሴትም በቫይረሱ መያዛቸው በመረጋገጡ በህክምና ላይ ይገኛሉ ተብሏል::
ከትግራይ ክልል በመቀጠል በርካታ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙበት ክልል ኦሮሚያ ሲሆን ሰላሳ አራት የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ በክልሉ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ  ሲሆን በቫይረሱ ከሚያዙት መካከልም የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡  
ቫይረሱ ከተገኘባቸው የጤና ባለሙያዎች መካከል አብዛኞቹ የተገኙት የኮሮና ቫይረስ ህክምና በማይሰጥባቸው መደበኛ የህክምና ተቋማት ውስጥ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑባቸው ምክንያቶችም በቂ የመከላከያ ቁሳቁስ አለመኖርና የጥንቃቄ ጉድለት እንደሆነም ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጤና ቢሮ የሥራ  ኃላፊ ነግረውናል፡፡  
በአማራ ክልልም በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን እስካሁን 23 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ በቫይረሱ ከሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በተመሳሳይ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል፡፡  
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን እስካሁን 21 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪዋ ስንታየሁ ዳባሳ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት፤ በቫይረሱ ከተያዙት የህክምና ባለሙያዎች መካከል በድንገተኛና በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ሃኪሞችና ነርሶች ይገኙበታል:: በከተማው እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ  500 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 17 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲሷ የሲዳማ ክልልም እስካሁን 13 የጤና ባለሙያዎችና ሁለት ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ በድምሩ 15 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡    
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋነው ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ በአገራችን የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ ተገቢው ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን የመከላከያ ግብአቶች አቅርቦትን ለማሟላትም ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል:: በመንግስት በኩል አቅርቦቱ ሁሉ ቢሟላም እንኳን የህክምና ባለሙያው ከጤና ተቋማቱ ውጪ እንደ ማንኛውም ሰው እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል ይኖረዋል የሚሉት ዶ/ር ወልደሰንበት፤ እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ሁሉንም አይነት መከላከያ ቢደረግ በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል እንጂ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ማድረግ አይቻልም ያሉት ዶክተሩ፤ የህክምና ባለሙያዎች በስፋት በቫይረሱ መያዛቸው በሽታውን ለመከላከል የምናደርገውን ጥረት ያበላሽብናል ብለዋል፡፡  
 በሽታው እንዲህ እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ያሉን ጥቂት የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው ጦር ሜዳ ላይ ተዋጊ ሰራዊትን እየቀነሱ እንደ መሄድ ይቆጠራል ያሉት ዶ/ር ወልደሰንበት፤ ይህ ደግሞ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምናደርገውን ትግል በአሸናፊነት እንዳንወጣ እንቅፋት ይሆንብናል ብለዋል:: የጤና ባለሙያዎቹ በቫይረሱ ከመያዛቸውም በላይ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው አብዛኞቹ የተገኙት የኮሮና ቫይረስ ህክምና ከማይሰጥባቸው መደበኛ የጤና ተቋማት መሆኑ ነው ይላሉ፤ባለሙያው፡፡   
በሌላ በኩል፤ በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል፡፡ ባለፉት 12 ቀናት በኢንዱስትሪ መንደሩ በተደረገ ምርመራ ከ100 በላይ የኢንዱስትሪ መንደሩ ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው የተገመቱት ሰዎችን በብዛት ለመመርመር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ በሚገኙ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ 66 ታራሚዎችም  በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡    
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ በቫይረሱ የሚያዙ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን የገለፁልን የክልሉ የጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀድራላ አህመድ ምንያህል፤ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ እንደተያዙ፣ ነገር ግን ለጊዜው አሃዛዊ መረጃ እንደሌላቸው ነግረውናል፡፡
በክልሉ በርካታ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተያዙበት አንድ ተቋም እንዲዘጋ ተደርጐ ባለሙያዎቹ ወደ ህክምና ማዕከል ገብተው እንደነበር የገለፁት አቶ ቀድራላ፤ አሁን ግን የጤና ተቋሙ ተከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በቫይረሱ የተያዙት የህክምና ባለሙያዎችም በአብዛኛው የኮሮና ህክምና በማይሰጥባቸውና መደበኛ የህክምና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ እንደሆነም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የጋምቤላ ክልልም በቫይረሱ የተያዙ የህክምና ባለሙያዎች ከሚገኙባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን እስካሁን 7 የጤና ባለሙያዎች (ነርሶችና ዶክተሮች) በቫይረሱ መያዛቸውን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋትሉዋክ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ የተጋለጡት ከህክምና ተቋማቱ ውጪ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው የጤና ባለሙያዎች ወደ ህክምና ተቋም እንዲገቡና እንዲያገግሙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

Read 8702 times