Saturday, 15 August 2020 14:17

የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የምግብ ሸቀጦች  የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው የሐምሌ ወር አሃዛዊ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሀገሪቱ የሸቀጦች የግብይት ሰንሰለቱ በደላሎች መያዙና የብር የመግዛት አቅም መዳከም የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እየናረ ለመምጣቱ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡  
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ወራት ያለማቋረጥ አማካይ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መጨመሩን በዚህም የነሐሴ ወር ብቻ በ23.7 በመቶ መጨመሩን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ24.9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል:: አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበቱም በ22.3 በመቶ ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል፡፡
የዋጋ ግሽበቱ በተለይ አነስተኛ ገቢ ባላቸውና በኮቪድ 19 ምክንያት ስራቸውን ባጡ ዜጐች ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል:: በዋናነትም የአትክልቶች፣ ጥራጥሬዎችና ፍራፍሬዎች ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጐች የሚመጥን አይደለም ተብሏል፡፡
መንግስት ቀደም ሲል የዋጋ ግሽበቱን በአመቱ መጨረሻ ላይ ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ እቅድ እንደነበረው ያወሳው ሪፖርቱ፤ ይህ በዋናነት አስፈላጊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ውጤታማ መሆን አለመቻሉን አመልክቷል፡፡  
በቀጣይም በዋናነት የገበያ አቅርቦት ሰንሰለቱን ማስተካከል እንዲሁም አምራቾችና ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚገናኙበት ስርአት እንዲዘረጋ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

Read 1042 times