Monday, 17 August 2020 00:00

በ32ኛው ኦሎምፒያድ የዓለም አገር አቋራጭ ሊካሄድ ይችላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   የዓለም አትሌሊክስ ማህበር በ2024 እኤአ ላይ የፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በምታዘጋጀው 32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን በልዩ ሁኔታ ለማካተት ሃሳብ አቅርቧል፡፡  የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫውን በኦሎምፒክ መድረክ በሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ እንደዱላ ቅብብል ለማካሄድ የታሰበ ነው፡፡ 2.5 ኪሎሜትርን ሁለት ዙር በመሮጥ የሚካሄደው ውድድሩ ላይ አንድ አገር በሁለት ሴት እና በሁለት ወንድ አትሌቶችን ማሳተፍ ይችላል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በረጅም ርቀት ሩጫ ላይ ትኩረት ማጣቱ እያስተቸው ቢሆንም የዓለም አገር አቋራጭን  ከ96 ዓመታት በኋላ ወደ ኦሎምፒክ መድረክ በመመለስ የምስራቅ አፍሪካን ድጋፍ ለማግኘት ያነጣጠረ ይመስላል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከፍተኛ አመራሮች ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ተስፋ እንደሚሰጥ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫን ወደ ክረምት ኦሎምፒክ ለማስገባት ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር፡፡ በ2008 እኤአ ላይ የምስራቅ አፍሪካዎቹ የረጅም ርቀት ምርጥ አትሌቶች ኃይሌ ገብረስላሴ ፖል ቴርጋትና ቀነኒሳ በቀለ ለዓለም አትሌቲክስ ማህበር በፃፉት ደብዳቤ የውድድር አይነቱን ወደ ኦሎምፒክ እንዲመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ በ1912 እና ከዚያም በኋላ በ1924 እኤአ ላይ በተዘጋጁት ኦሎምፒኮች ላይ ከውድድሮቹ መካከል ይገኝበት ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2021 እ.ኤ.አ ላይ 44ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው አውስትራሊያ ስትሆን፤ ባሁርሰት በተባለ ከተማ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ስትወስን የፓናሮማ ተራራ ለውድድሩ ድምቀት ይፈጥራል ብላለች፡፡  ኢትዮጵያ በ2023 እኤአ 45ኛውን ወይንም በ2025 እኤአ 46ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት ማመልከት የምትችል ሲሆን በተለይ በ2024 እኤአ ለሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒያድ መሸጋገርያ እንዲሆን በመስራት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ የአፍሪካ አህጉር  ለ5 ጊዜ መስተንግዶውን ያገኘች ሲሆን ሞሮኮ በ1975፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996፤ ሞሮኮ በ1998፤ ኬንያ በ2007 እንዲሁም ኡጋንዳ በ2017 ናቸው፡፡ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በሁለቱም ፆታዎች በሚዘጋጁ 6 የተለያዩ የውድድር መርሃ ግብሮች ከ60 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ550 በላይ ሯጮችን እንደሚያሳትፍ ይታወቃል፡፡
ባለፉት 60 ዓመታት በተደረጉ 43 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በሁሉም የውድድር መደቦች 324 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ የሆነችው ኬንያ ስትሆን ኢትዮጵያ በ275 ሜዳልያዎች  በሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡


Read 1125 times