Saturday, 15 August 2020 13:55

ውሻ ጌታውን እንጂ የጌታውን ጌታ አያውቅም

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ታሪክ ሲያረጅ ተረት ይመስላል፡፡ በድሮ ዘመን የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት ሲፈነዳ አንድ ሐሙስ ሲቀረው ትግራይ ውስጥ ያለ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ሙዚቃ ያንባርቃል::  ወጣቶች ይጨፍራሉ፡፡ ምሽቱ ገፍቷል፡፡ ወጣቶች እንደ ወጣትነት እድሜያቸው ይጨፍራሉ፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎችም ጥግ ጥግ ይዘው እየጠጡ ይዝናናሉ፤ ያጨበጭባሉ::
በመሃል አንድ የሸዋ ሰው የአዲስ አበባ ሰው አዲስ አበቤ (ኒው ዮርከር እንደሚባለው) መሆኑ ነው) ወደ ቡና ቤቱ ይገባል፡፡ ዘፈኑ የታዋቂው ድምፃዊ የሳሚ አብርሃ ነው፡፡ አስረሽ ምቺው ቀልጧል፡፡  
ያ ድንገት የገባው የአዲስ አበባ ሰው ኢትዮጵያ ሬዲዮን ቴሌቪዥን ነጋ ጠባ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሊፈነዳ እንደተቃረበ የሚጠቁም ዜናና ሀተታ በሚያሰማበት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ሆኖ ይሄ ሁሉ አስረሽ ምቺው እንዴት ነው? የኤርትራ መገንጠሏ እያለቀለት እንዴት እንዲህ ያለ ዘፈን ይዘፈናል? ብሎ ገርሞት አጠገቡ የተቀመጡትን አዛውንት ፈራ ተባ እያለ ይጠይቃቸዋል፡፡
“አቦይ?” አዛውንቱን ማጨብጨባቸውን አቋርጠው
“አቤት ወደይ” ይሉታል “ይህን የሚዘፈነውን ዘፈን ያዳምጡታል?” ሲል ይጠይቃቸዋል::
“አዎ!”
“የሳሚ አብርሃ አይደለም ወይ?”
“አዎ! ወደይ”
“የኤርትራ ዘፈን አይደለም”
 “እንዴታ?”
“ኤርትራ እየተገነጠለች እኛ የኤርትራ ዘፈን ያውም እንዲህ እያስጮኹን  ማዘፈን ተገቢ ነው  አቦይ?”
(የነሱን ዘፈን ማዘፈን ትክክል አይደለም ከሚል ስሜት ተነስቶ ነው)፡፡
“ኤርትራና ኢትዮጵያ ቢለያዩም፤ ማናቸውንም ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ቢቋረጥም አንድ ነገር ግን አትርሳ” አሉና ጀመሩ ሽማሌው፡፡
“ምን?” አለ ሰውየው፤ የሚሉትን ለመስማት እየተቻኮለ፡፡
“አየህ የኔ ልጅ” ብለው ቀጠሉ ሽማሌው፡፡
“አየህ ልጄ! በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቻይና ግንብን የሚያክል ግንብ ቢገነባ እንኳን ለካሴት መቀባበያ የምትሆን አንዲት ቀዳዳ መኖሯ አይቀርም”፡፡ አሉት ይባላል፡፡
*    *   *
ጥበብ የማያፈርሰው ግንብ የለም፡፡ ነባር ባሕላዊ ትስስርም በዋዛ አይበጠስም:: ማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በባህል እየታገዘ፣ የህዝቦቹንና የሀገሮቹን ሁነኛ ትስስር እያጠበቀና እያበለፀገ ይጓዛል፡፡ የልብ ከልብ መረጃ ልውውጥም አንድም በአፍ አንድም በጽሑፍ እያቆየ ታሪክ አድርጐ ያኖረዋል፡፡
የልምድና የኑሮ ዘይቤ ከትውልድ ትውልድ እንዲዘዋወርም ይረዳል፡፡ ተራማጅ አስተሳሰብ ለማህበራዊ ለውጥ ምክንያት እየሆነ አዲስ የእድገት መንገድ እንዲቀደድ ጥርጊያ ያበጃል፡፡ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ሥርዓት ስርፀት ግዘፍ - ነስቶ እየተጠናከረ እንዲሄድ ትምህርትና እውቀትን እርካብ አድርጐ ይጠቀማል፡፡ ለዚህም  በየጊዜው የሚነሱ  የሀገር ጉዳዮችን በማስታወስ፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በማንሳት መነጋገሪያ እንዲሆኑ ይቀሰቅሳል፡፡ ጥበብን መገልገያ የሚያደርግ ሥርዓት በቀላሉ መግባቢያ የሚሆኑ መድረኮችን ለመፍጠር አይቸገርም፡፡ ከጋላቢ ፈረስ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የሮማው ንጉሥ ድል ባደረገ ጊዜ አለው የሚባል ተጠቃሽ አነጋገር አለ፡፡ ይኸውም “Veni” “Vidi” “VICI” “መጣሁ” “አየሁ” “ድል መታሁ” የሚል ነው፡፡ ወደ ጦር ሜዳው በወቅቱ መድረሱን ይገልፃል፡፡ ማየት፣ ማተኮር፣ ማስተዋል ካለ ችግሩ ሂደቱና መፍትሔው ፍንትው ብሎ ይከሰታል፡፡ በመጨረሻም በአግባቡ ታግሎ ማሸነፍ ሲታከልበት ዕድገት ይመጣል፡፡ እነዚህ ሦስት መርሆች ለአንድ ለውጥ ለምትሻ እንደኛ ላለች ሀገር ቁልፍ ናቸው፡፡
ለውጥን የምትሻ ሀገር የታደለች ናት፡፡
እንኳንስ እንደኛ ባለ በማደግ ላይ ለሚጉተረተር (የሚውተረተር) ሀገር፤ ያደጉትም ሀገሮች እንኳ እንኳ አሁንም የበለጠ ለማደግ መጣጣራቸው የእድገት ህግ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ መጣጣር እንቅፋቶች መኖራቸው፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሌም ያለ ሂደት ነው፡፡
በዚህ ላይ በኑሮው ዲያሌክቲካዊ ቋንቋ የተቃራኒዎች አንድነትና ትግልም `Unity and Straggle of opposite” አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ ሙስና ብዝበዛ፣ እቅድ አልባነት፣ ዘገምተኝነት፣ ጊዜ አለማወቅ፣ ነካክቶ ሩጫ፣ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት በጥቅሉም አፍራሽ ተልኮ ሁሌም የሚፈታተነን ካንሰር - በሽታ ነው - ልንዋጋው ይገባል፡፡ መድረሻውንም የምናየው ገመድ መነሻ ጫፉ የት እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ ጐረቤቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ከጐረቤቶቻችን ጀርባ ያሉ ትላልቅ ባላንጣዎቻችንን አይናችንን ከፍተን ማየት አለብን የሁሉንም ጠቅላይ ማወቅ አለብን፡፡ ጠቅላይ አዛዣቸውን ማጤን አለብን፡፡  
“ውሻ ጌታውን እንጂ የጌታውን ጌታ” አያውቅምና ነገሮችን በተሰናሰለ መልክ እናስተውል!  

Read 17870 times