Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 11:59

ሚስቱን፣እናቷንና አክስቷን የገደለው ራሱን አጠፋ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአራዳ ክ/ከተማ ቀበሌ 13/14 ልዩ ቦታው ቀበና ድልድይ፣ ኪዳነ ምህረት ት/ቤት አጠገብ ነዋሪ የነበረው አቶ ዘላለም ፍሠሀ ሚስቱን፣ እናቷንና አክስቷን በሽጉጥ ተኩሶ ከገደለ በኋላ የራሱን ህይወት በተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጠፋ ከፖሊስ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡ አቶ ዘላለም ፍስሃና ወ/ሮ ወርቅነሽ ጉቺ ለስምንት አመታት በትዳር አብረው የኖሩ ሲሆን የዘጠኝ አመትና የሁለት አመት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሆኖም ቅናት በትዳራቸው ገብቶ ኑሮአቸውን ሲበጠብጠው እንደቆየ ነው የወ/ሮ ወርቅነሽ ታናሽ እህት ሶሎሜ ኦልጅራ የተናገረችው፡፡ ጥንዶቹ ህጋዊ ፍቺ ባይፈፅሙም ባል ሲጣሉ በተደጋጋሚ ንብረቱን ይዞ ይወጣ እንደነበር የገለፀችው ሶሎሜ፤ ከአስር ቀን በላይ ግን አይቆይም፤ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር ብላለች፡፡

ባለፈው መጋቢት ወር ግን ግጭታቸው ከረር ያለ ስለነበር አቶ ዘላለም ለአራት ወራት ወደ ቤቱ ሳይመለስ እንደቀረ ተናግራለች - ሶሎሜ፡፡ ወ/ሮ ወርቅነሽ ህጋዊ ፍቺ ለመጠየቅ አስባ እንደነበርና ልጆቿም እናቷ ጋር እንደነበሩ የጠቆመችው ሶሎሜ፤ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወ/ሮ ወርቅነሽና ልጆቿ እንዲሁም እናቷ አክስቷ ቤት ተሰባስበው እንደነበር ትናገራለች - ማህበር ስለነበር፡፡ ይሄኔ ነው አቶ ዘላለም የወርቅነሽ አክስት  ወ/ሮ ገነት ተዘራ ቤት ዘሎ በመግባት “መግደል የምፈልገው አንቺን ነው” በማለት ሽጉጥ አውጥቶ ሚስቱን ደረቷ ላይ ተኩሶ የመታት፡፡ በሚስቱ ብቻ ግን አልበቃውም፡፡ እራሳቸውን ለማዳን በምጣድ ስር ተከልለው የነበሩትን የወርቅነሽ እናት ወ/ሮ የክቴ ተዘራንም ተኩሶ ገድሏቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ወርቅነሽ አክስት ወ/ሮ ገነት ተዘራ ዞረ - እሳቸውንም ደረታቸውና  ጀርባቸው ላይ በመምታት ገደላቸው፡፡ የሦስቱን ሰዎች ህይወት ያጠፋው አቶ ዘላለም፤ በመጨረሻም የያዘውን ሽጉጥ ጭንቅላቱ ላይ በመተኮስ የራሱንም ሕይወት እንዳጠፋ ታውቋል፡፡ ድርጊቱን ሊፈፅም ወደቤት ሲመጣ የሚያውቁ ሠዎች ነበሩ ያለችው ሶሎሜ፤ ዝም ያሉት እራሱን ሊያጠፋ መስሏቸው እንደሆነ ለቅሶ ላይ እንደነገሯት ገልፃለች፡፡ “እኔ 18 አመቴ ነው፤ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፤ ከጐኔ ማንም የለም፤ የእህቴን ልጆች ማሳደግ አልችልም” የምትለው ሶሎሜ፤ እናታቸው ልጆቿን ስትከላከል ከጀርባዋ ተመታ እንደሞተች እንባ እየተናነቃት ተናግራለች፡፡ ገዳይ በሦስቱ ሟቾች ላይ ከተኮሰው አምስት ጥይት ውጪ ስምንት ጥይት በኪሱ ውስጥ እንደተገኘ ታውቋል፡፡

 

 

Read 21897 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 14:08