Monday, 10 August 2020 00:00

የማንነት ቀውስና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(4 votes)

  በህዝቦች መካከል ለበርካታ ምዕት ዓመታት በተለያየ ደረጃ የነበሩት መስተጋብሮችና መተሳሰሮች የአሸብራቂው የኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛ መሰረቶች መሆናቸው እሙን ነው። ይህ የህዝቦች መተሳሰር ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት፣ በሃገሪቱ የተከሰቱትን ከፍተኛ የፖለቲካ ምስቅልቅሎች ለመሻገር ዓቢይ ድርሻ የነበረውና ወደፊትም የሚኖረው መሆኑ አያጠያይቅም። ነገር ግን፣ ይህ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየው መተሳሰር በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የሃገረ መንግስት ምስረታ ሂደት ውስጥ ክፉኛ ተፈትኗል፤ በመፈተንም ላይ ይገኛል። የዚህም ፈተና ዋነኛው አስኳል በሁለት ልዩ ታሪካዊ ወቅቶች በተግባር ላይ ከዋሉ የአሃዳዊነት ሥርዓቶች ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ የማንነት ቀውሶች (Identity crises) ናቸው። የመጀመሪያው፣ የአትዮጵያን ሃገረ መንግስት በአንድ ወጥ አሃዳዊነት (Monocultural unitarianism) ላይ በተመረኮዘ ማንነት ለመገንባት ከተደረገው ጥረት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው፤ቀደም ሲል በአሃዳዊነት ዘመን የደረሰውን በደል ለማከም በሚል በተወሰዱ መንግስታዊ እርምጃዎች የተፈጠረው ብሔረሰባዊ አሃዳዊነት (Ethnicisedunitarianism) ናቸው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማከም የሚደረገው ጥረት፣ የእነኚህን የማንነት ቀውሶች ምንጭ ባግባቡ በመረዳት መፍትሄ መሻትን ይጠይቃል። የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ዓላማ፤ እነኚህን አበይት የማንነት ቀውሶች ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ በመመርመር  የመፍትሄ ሃሳቦችን መጠቆም ነው።
ከዘመነ መሳፍንትበኋላ ኢትዮጵያን እንደገና ለማጠናከርና ዘመናዊ ፈር ለማስያዝ በዓጼ ቴዎድሮስ የተጀመረውና በተከታታይ ነገስታቶች የቀጠለው ሂደት፣ በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መመስረት እንደ አዲስ ፈር ቀዳጅ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ፣ እነኚህ በተከታታይ ነገሥታት የተከናወኑት የሀገረ መንግስት ማጠናከር ሂደቶች፣ በሃገራዊ አንድነት ምስረታ ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ አንድ ወጥ አሃዳዊነትን በማጠናከር ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው የበርካታ ማንነት ቀውሶች ምንጭ ሊሆኑ ችለዋል።በዘመነ ዓጼ ኃይለ ሥላሤ ይህ የአሃዳዊነት ሂደት ከፍተኛ ተቋማዊ ቅርጽ እየያዘ ለመምጣቱ በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌም ያህል፣ ለበርካታ ዓመታት በሀገሪቱ ብቸኛ በሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር የአማርኛ ፈተናን ማለፍ ግዴታ ነበር። አማርኛን እንደ ሃገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ እስክ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ማስተማሩ አስፈላጊ መሆኑ ባይካድም፣ አንድን ዜጋ በዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሂደት ውስጥ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የማይኖረውንና ለብዙዎች ሁለተኛ ቋንቋ የሆነውን ካላለፍክ ብሎ የመማር መብትን መከልከል የሚፈጥረውን የተጎጂነት ስሜት መረዳት ይቻላል። ይህና ሌሎች ከቋንቋ ጋር የተያያዙ ተቋማዊ ጭቆናዎች በአፍሪካ ውስጥ ብቸኛ በሆነው የአማርኛ ቋንቋችን መኩራት ሲገባን በርካቶች እንደ መጨቆኛ መሳሪያ እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። በተመሳሳዩ፣ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ተማሪዎች ባሉበት ትምህርት ቤት ውስጥ በየዕለቱ ጠዋት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የክርስትያኑን ፀሎት ሁሉም እንዲጸልዩ ማስገደድ ሌላው የአሃዳዊነት ሥርዓቱ መገለጫ ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በልጅነት አእምሮዬ ከሚያሳዝኑኝና ከሚያስከፉኝ ትውስታዎቼ አንዱ የተወሰኑ  አብሮ አደግ ጓደኞቼ በረመዳን ጾም ወቅት ይህንን የግዴታ ፀሎት ላለመጸለይ ሲሉ ዘግይተው ወደ ትምህርት ቤት በመምጣት፣ ወደ ክፍል ከመግባታቸው በፊት የሚደርስባቸው ቅጣት ነበር። ከላይ የቀረቡት ምሳሌዎች በእኛው ዘመን ከነበረው ታሪካችን እንደ ማሳያ የቀረቡ ሲሆኑ ከዚህም የከፉ በርካታ የአሃዳዊነት መገለጫዎች ተቋማዊ በሆነ ደረጃ ይራመዱ እንደነበር መካድ ራስን መሸንገል ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በርካታ ወገኖቻችን በተለያየ መልክ ለሚገለጹ የማንነት ቀውሶች እንዲጋለጡና አንዳንድ ወገኖችንም ኢትዮጵያዊነታቸውን እስከ መጠራጠር እንዲደርሱ አድርጓቸዋል።
የዘመናዊ ትምህርት በሃገሪቱ እየተስፋፋ መምጣቱና ከፊውዳላዊው ሥርዓት ጋር ተያይዞ ከነበረው መጠነ ሰፊ ጭቆና ጋር መጣጣም አለመቻሉ ለተማሪው እንቅስቃሴ መጀመር ዋነኛ ምክንያት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ በተጠቀሰው አሃዳዊ አገዛዝ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው የማንነት ቀውስ የተለያዩ የማንነት መብት ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።  በመሆኑም፣ በርካታው ተማሪ መሰረታዊ የሆኑ ሃገራዊና ሰብአዊ የመብት ጥያቄዎችን እንደ ሃገራዊ ዋነኛ የለውጥ መታገያ ሲያነሳ፣ የተወሰኑት ደግሞ የብሄረሰቦች የራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደ ዋነኛ መታገያ ሊያነሱ ችለዋል። የተማሪው ንቅናቄ ድርጅታዊ ቅርጽ እየያዘ ሲመጣም፣ የመጀመሪያዎቹ ወደ ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅትነት ሲቀየሩ፣ ሁለተኞቹ ደግሞ ወደ የብሔረሰብ ነፃ አውጪ ድርጅትነት ተሸጋገሩ። የየካቲት 1966 የህዝብ ንቅናቄን ተከትሎ፣ ወታደራዊው ደርግ አንዳንድ የጭቆና መገለጫዎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት የወሰደ ቢሆንም፣ መሰረታዊ ሃገራዊ አንድነትን ለማምጣት የሚያስችሉ መብቶችን ሊያከብር አልቻለም። ከዚህ ይልቅ፣ በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የነበረባቸውን ድክመት በመጠቀም የራሱን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማጠናከር በወሰደው እርምጃ፣ ለበርካታ ብርቅዬ ዜጎች መሰዋት ምክንያት ሆኗል። በዚህ እርምጃው፣ ወታደራዊው ደርግ በቀዳሚነት ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው በፍጹም የሃገርና የህዝብ መውደድ ስሜት በተለያዩ ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ስር ተሰባስበው ይታገሉ የነበሩትን መሆኑ የሃገሪቱን ቀጣይ ዘመን እጅግ ፈታኝ አድርጎታል።
ከዚህ ተከትሎ የመጣው የኢህአዴግ መንግስት፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ያቆጠቆጠውን የብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶችን ለመተግበር የሚያስችሉ ማእቀፎችን ለመመስረት ሙከራ አድርጓል። የህዝቦች ቋንቋና ባህል የሚከበርበትና ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንግስታዊ ሥርዓት መፍጠር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የበርካታ ብሔረሰቦች ሃገር ዘላቂ ልማትና እድገት አስፈላጊ መሆኑ ሊያከራክር አይገባም። ነገር ግን፣ኢህአዴግ የተከተለው መስመር የትናንትናውን በደል ለመካስ በሚል ሽፋን የሌሎች ዜጎችን በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል በነፃነት የመኖር መብት ለመጣስ መጠቀሚያ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበረውን አንድ ወጥ አሃዳዊነት፣ በርከት ወዳለ ብሔረሰባዊ አሃዳዊነት (Ethnicised Unitarianism) ሊያሸጋግር ችሏል። በመሆኑም፣ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የሃገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ለሚያጠራጥር አዲስ አይነት የማንነት ቀውስ ተዳርገዋል። ይህ ባንዳንድ የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኞች አደገኛ ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ፤ ለሃገራዊ አንድነት መጠናከር የሚጠቅሙ እሴቶችን ለመሸርሸር የሄደበት አሳፋሪ መንገድም ሃገሪቱን ዛሬ ላለችበት የፖለቲካ ቀውስና ራሱንም ለታሪክ ተወቃሽነት አብቅቷል። በጥቅሉ፣ የማንነት ጥያቄ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተግባር ላይ ከዋለው የፌደራል አወቃቀር ጋር በተያያዘም ይበልጥ አወዛጋቢ ከሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱና ዋነኛው እንዲሆን አድርጎታል።
ባላፉት ስልሳ አመታት የማንነትን ጥያቄ በተመለከተ የሚሰጡ ትንታኔዎች በአብዛኛው በፖለቲካው መስክ ከሚታየው የተቀነበበ ትንተና ድክመቶች የነጹ ሊሆኑ አልቻሉም። ይህም፣ ባንድ በኩል በሃገሪቱ ምንም አይነት የብሔር ጭቆና አልነበረም ከሚለውና ገሃድ የነበረውን የማንነት በደሎች በሃገራዊ አንድነት ለመሸፈን ከሚደረግ ሰጎናዊ አቋም አንስቶ ፍትሃዊ የሆነውን የብሔሮችን የራስን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ በሚለጥጠው ተስፈንጣሪ የግራ ዘመም አቋም ይገለጻል። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ የማንኛውም ሰው ማንነት በበርካታ ጥምር መለያዎች መስተጋብር እንጂ በአንድ የተናጠል ባህርይ የሚገለጽ አይደለም። በዚህም መሰረት፣ የማንኛውም ሰው ማንነት በሚከተሉት ሶስት ዋነኛ የማንነት ጥምር መስተጋብር የሚገለጽ ይሆናል። የመጀመሪያው ዓቢይ ማንነት፣ የተፈጥሮ ማንነት ሲሆን ይህም የሰው ልጅ ከእንስሳቱ ዓለም የሚለየውን ሰብዓዊ ባህርይ የሚያጎናጽፈው ተፈጥሮዋዊው የዘረ መልእ ማንነቱ ነው። በዚህም ማንነቱ የተነሳ ሁሉም የሰው ልጅ በሰውነቱ የሚጎናጸፈው መሰረታዊ ክህሎትና ባህርያት ይኖሩታል። ይህ የተፈጥሮ ማንነት የማናቸውም ማንነት መነሻ መሰረት በመሆኑ የሉላዊነት (universality) ባህሪ አለው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት፣ በተባበሩት መንግስታት የጸደቀው ሉላዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) በዚሁ የሰው ልጆች ሰብዓዊ ማንነትና ተያያዥ መብቶቻቸው ላይ የተመስረተ ነው። በመሆኑም፣ ለበርካታ አባል ሃገራት ህገ መንግስት እንደ መነሻ መሰረት በማገልገል ላይ ይገኛል። በጥቅል አነጋገር፣ ሰብዓዊነትን በምሉዕነቱ የማይቀበል ማንነት ለሌሎች ማንኛቸውም የማንነት መብቶች መከበር የመቆም ብቃት ሊኖረው አይችልም። መነሻ መሰረቱን አልያዘምና።  
ሁለተኛው ዓቢይ ማንነት፣ ማህበራዊ ማንነት ሲሆን ይህም ማንነት የሰው ልጆች ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ ማህበራዊ እድገት ያለፈ ማንነት ነው። የማህበራዊ ማንነት መሰረት ቤተሰብ ሲሆን፣ የማንኛችንም ማህበራዊ ማንነት ከቤተሰብ በሚተላለፉ የቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ልማዳዊ ውርሶች የሚወሰን ይሆናል። ስለዚህም፣ ማህበራዊ ማንነት ከከባቢ መንደር (neighbourhood) አንስቶ እስከ ጎሳ፣ነገድና የብሔረሰብ ደረጃ ሊኖረው ይችላል። በዚህ ማህበራዊ ማንነት ውስጥ፣ ከቤተሰብና ከመንደር ጋር የተያያዘው ማንነት ከሌሎቹ ማህበራዊ ማንነቶች የጠበቀ ቁርኝት ይኖራቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ማንኛውም ሰብዓዊ ማንነትን ማእከል አድርጎ ያልተደራጀ የብሔረሰብ ነፃ አውጪ ድርጅት በመንደርተኝነት መፈተኑ የማይቀር ይሆናል። እንዲህ አይነቱ ፈተና፣ ባሁኑ ወቅት በሃገራችን በሚገኙም ብዙዎቹ የብሔረሰብ ድርጅቶች ውስጥ የሚታይ ችግር ነው። ሶስተኛው አቢይ ማንነት፣ ፖለቲካዊ ማንነት ሲሆን ይህም ማንነት ከሃገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ ጋር የተያያዝ የዜግነት ማንነት ነው። የዜግነት ማንነት፣ ባንድ ሃገረ መንግስት ወይም ምድራዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በሚጋሯቸው የጋራ ፖለቲካዊና  ታሪካዊ ሁነቶች የሚቀረጹ ይሆናል። በመሆኑም፣ ዛሬ ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንድ ሰው ካንድ በላይ የሆነ ዜግነት ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌም ያህል፣ በአንዳንድ ሃገሮች ካለው የጥምር ዜግነት በተጨማሪ፣ በበርካታ ሃገራት የመስራትና የመኖር እድል ያገኘ ወይም ራሱን ከበርካታ ሃገራት በሚገኙ ዕውቀቶች ያበለጸገ ሰው ራሱን ከኢትዮጵያዊነቱ ባሻገር አፍሪካዊ (Pan African) እና ዓለም አቀፋዊ ዜጋ (Global citizen) ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል። እንዲህ አይነቱ የዜግነት ልህቀት ለማንኛቸውም ማህበራዊ ማንነት ተገቢውን እውቅና እና አክብሮት የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በመጀመሪያ ደረጃ ካነሳነው ሰብዓዊ ማንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ይሆናል። በመሆኑም፣ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዜግነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
ለዘመናት በሃገራችን ሲራመድ የኖረው አሃዳዊ ሥርዓት ከፈጠረው የማንነት ቀውስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቡድኖች በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዙ የፖለቲካ ድርጅቶች መስርተው ለመታገል መነሳታቸው እንደ ሃጢያት ሊቆጠር አይገባውም። በዚህ ረገድ፣ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎችና ተንታኞች ለበብሔር መደራጀት የተለያዩ አፍራሽ ቅጥያዎች በመለጠፍ በህግ እንዲታገዱ መጠየቃቸው አሳፋሪ ብቻም ሳይሆን ስለ ሀገሪቱ ተጨባጭና ታሪካዊ እውነታ እውቀት እንደሚያንሳቸው ይሳያል። በብሔር የመደራጀት ዋነኛው ችግር የሚመነጨው፣ ማህበራዊ ማንነትን እንደ ብቸኛው የማንነት መገለጫ ከማድረግና ይህንንም ለሃገረ መንግስት ምስረታ እንደ ብቸኛ መነሻ መሰረት አድርጎ ከመውሰዱ ላይ ነው። እነኚህ በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዙ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ሰብዓዊ ማንነትን በሚያከብርና ለዘመኑ በሚመጥን የዜግነትአመለካክት ሊቃኙ ይገባቸዋል። ይህ ካልሆነ፣ በብዙዎቹ አንጋፋ የብሔር ድርጅቶች ውስጥ ባሁኑ ሰዓት እንደሚታየው ጠባብ ወደሆነ የመንደርና ቤተሰብ መጠቀሚያነት መሸጋገራቸውና የግጭትና ውዝግብ ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ይሆናል። የሃገራችንን ፖለቲካ አካታችና ፍትሃዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት፣ ለዘመናት የተጠራቀሙትን የማንነት ቀውሶች በሃገራዊ አንድነት ማከም በጣም አስፈላጊ ያደርገዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ባጠቃላይ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይ በሃገሪቱ ገኖ የታየውን ‘የብሔር ፖለቲካ’ በሃገራዊ አንድነት መቃኘት ያሰፈልጋል።ይህ እንዲሆን፣ በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዘ ሃቀኛ ፖለቲካ የሚያራምዱ ቡድኖች፣ ጥያቄዎቻቸው በተሟላ ሁኔታ ሊመለሱ የሚችሉት ሰብዓዊ ማንነትንና የዜግነት መብትን በሚያካትት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ መሆኑን መረዳትና ይህንኑም ማክበርና ማስከበር ይኖርባቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በቅርቡ ከሶማሊያ ክልል የሚሰማው ለውጥ ብርታት የሚሰጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ህብረ-ብሔራዊ ወይንም የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖችም፣ በዘመናት ውስጥ የተፈጠረውን የማንነት ቀውስና ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን የመንፈስ መጎዳት በመረዳት፣ ይህንን ለመፈወስ የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ከማንነት ፖለቲካ አራማጆች ጋር በጋራ መሻትና ለተግባራዊነቱም አብሮ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህንንም በማድረግ፣ ይበልጥ አሰባሳቢና አካታች ወደሆነ የፖለቲካ ሥርዓት መሸጋገር ይቻላል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው፤ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 3442 times