Print this page
Sunday, 09 August 2020 00:00

“የጨቋኝ ተጨቋኝ፣ የገዳይ አስገዳይ ትርክትን እያነሳን ነገን ማጨለም የለብንም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   *በእያንዳንዱ ወረዳ ላይ የሥራ ቋንቋ በህዝበ ውሣኔ መወሰን አለበት
           *ለፌደራሊዝም አወቃቀር ታሪክን መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል
           *ግባችን፤ የበጐ አድራጐት መንግስት መመስረት ነው


                  የተወለደው በአዲስ አበባ ቢሆንም እድገቱና ትምህርቱ ግን ሀረርና ድሬደዋ ነው፡፡ የመጀመሪያ ድግሪውን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስነ ጽሑፍና ታሪክ ያገኘ ሲሆን ሁለተኛ ድግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስነ ጽሑፍና እንግሊዝኛ ቋንቋ ወስዷል፡፡ ሦስተኛ ድግሪውን ደግሞ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ጥናት ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ የዛሬው እንግዳችን ሰለሞን ተሰማ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆን  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበርም ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከአቶ ሰለሞን ተሠማ ጋር በፓርቲው እንቅስቃሴና በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

                 እስቲ ከኢህአፓ ርዕዮተ ዓለም እንጀምር:: እርግጠኛ ነኝ ፓርቲያችሁ የርዕዮተ አለም ለውጥ አድርጓል--?
አዎ፤ የርዕዮተ አለምና ፖሊሲ ለውጥ ተደርጓል፡፡ በፊት ፓርቲያችን የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም ነበር የሚከተለው:: አሁን ግን ርዕዮተ ዓለሙን ወደ ማህበራዊ ዲሞክራሲ (ሶሻል ዲሞክራሲ) ለውጧል:: በፊት ወገንተኝነቱ ለአርሶአደሩ፣ ለአርብቶ አደሩና ለጥቂት የሠራተኛው ክፍል ነበር፤ አሁን ግን በየትኛውም ሁኔታ ለተገፉ ለተቸገሩና በየትኛውም ሁኔታ ለመኖር የጤና፣ የትምህርት መሠረተ ልማት ማሟላት ያቃታቸው ዜጐች ላይ ነው ትኩረታችን:: አሁን የምንከተለው ርዕዮተ ዓለም ከጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የወጣ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እውነታ ያገናዘበ ነው - ርዕዮተ አለማችን፡፡ በዚህም መሰረት አጠቃላይ ግባችን፤ የበጐ አድራጐት መንግስት (ዌልፌር ስቴት) እንመሠረታለን የሚል ነው፡፡ ይሄ የበጐ አድራጐት የመንግስት ቅርጽ በተወሰነ ደረጃ በደርግም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስርአትም ተሞክሯል፡፡ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ጨው፣ ስኳር፣ ዱቄት በራሽን ለማደል ጥረት ተደርጓል፡፡ ግን ያ ሙከራ የግል ባለሀብቶችንና ነጋዴዎችን የገታና ከጨዋታ ውጪ ያደረገ ነበር፡፡ እኛ የምንከተለው ግን እነዚህን አቻችሎ መሄድ የሚችል፣ ባለሃብቱም ነጋዴውም ሁሉም የሚጠቀምበት አካሄድ ነው:: አንድ ዜጋ ሲታመም በነፃ ታክሞ የመዳን መብት አለው፣ አንድ ዜጋ በነፃ የትምህርት እድል ማግኘት መብት አለው፣ ማንኛውንም በገበያ ላይ የሚኖር የዋጋ ንረትን መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሊያረጋጋ ይገባዋል የሚል ነው፤ርዕዮተ አለማችን፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ብልጽግና ፓርቲ የሚሽቀዳደምበትን የቋንቋ ጉዳይ ማለትም አገሪቷ አምስት የስራ ብሔራዊ ቋንቋ  ሊኖራት ይገባል ብለን አስቀድመን በፕሮግራማችን ያስቀመጥነው እኛ ነን፡፡
በኢትዮጵያ አንድነትና በብሔር ፌደራሊዝም ላይ ያስቀመጣችሁት ፕሮግራምስ ምን ይመስላል?
በፊትም ቢሆን ኢህአፓ የግለሰብና የቡድን መብትን እኩል እውቅና የሚሰጥ ፕሮግራም ነበረው፡፡ የቡድን መብት ሲል ግን መገንጠልን አይደግፍም፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማያሻማ አቋም ነው ያለን:: የቡድን መብትን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ የቡድን መብት እስከ መጨረሻው መጠበቅ አለበት፡፡ ለምሣሌ በአዲስ አበባ ከተማ የሆነ አካባቢ የስልጥኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በዛ ብለው የሚገኙበት አለ:: እዚያ አካባቢ በስልጥኛ ቋንቋ ትምህርት ቢሰጥ፣ የአምልኮ ቦታ ቢኖር፣ ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸው ነገሮች ያለ ገደብ ቢሟሉ የቡድን መብትን ማረጋገጥ ይቻላል የሚል ነው ፕሮግራማችን፡፡ ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ አንድ ሰው የስልጥኛ ትምህርት አልፈልግም ካለ፣ ይሄም መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል:: የኛ የፌደራሊዝም መርህ ከዚህ የመነጨ ሲሆን የግለሰብና የቡድን መብቱም ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን ያለው ግን ጨፍላቂ ፌደራሊዝም ነው፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔሮች ሙሉ መብት የላቸውም፡፡ በራሳቸው ቋንቋ ልጆቻቸው በማህበረሰብ ት/ቤታቸው አያስተምሩም፣ ራሣቸውን አያስተዳድሩም፡፡ መሬት ላይ በግልጽ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ጥያቄው ያንን እንዴት እንፍታ ነው፡፡ ኢህአፓ በመሠረታዊነት ለዚህ የሚያስቀምጠው መፍትሔ ቋንቋ በየትኛውም ሁኔታ ሊመነዘር የሚችል ጉዳይ በመሆኑ ህዝብ ራሱ በህዝብ ውሣኔ ሊወስነው የሚገባ ነው፤ እያንዳንዱ ወረዳ ላይ ያለ ህዝብ የሚጠቀምበትን ቋንቋ በህዝበ ውሣኔ መወሰን አለበት፡፡ ከላይ የተቀመጠው አስተዳደር የፖለቲካ ውሣኔ የሚወስንበት አካሄድ ስህተት ነው:: የህዝብ ወይም የቡድኖች መጨፍለቅ መቆም አለበት:: "ይሄ የኔ መሬት ነው፡፡ ይሄ በቅድመ አያቴ ጊዜ የተቀመጥኩበት ነው" የሚል አካሄድ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው:: ለምሣሌ ትግራይና ሰሜን ጐንደር ያለው የወልቃይት ፀገዴ፣ የራያ፣ የቤኒሻንጉልም ሆነ ሌሎች አካባቢዎችም  እየተከሰተ ያለው ችግር ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ መፍትሔው እዚያ ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ ምን ትፈልጋላችሁ? ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ እናውቅላችኋለን የሚል ድፍረት ያዘለ ውሣኔ ነው እስካሁን እየተሰጠ ያለው፡፡ ያ ደግሞ ዋጋ አስከፍሏል፤ አሁንም ወደፊትም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት ፌደራሊዝሙ እንደገና መዋቀር እንዳለበት ነው የኛ ፕሮግራም የሚያስቀምጠው፡፡ አሁን ያለው አወቃቀር  የሚቀጥል ከሆነ ግን ትርምሱ ይቀጥላል፡፡
በፕሮግራማችሁ መሰረት የፌደራሊዝም ስርአቱ እንዴት ነው መዋቀር አለበት የምትሉት?
በመጀመሪያ ደረጃ ፌደራሊዝም ሲዋቀር ታሪክን መነሻ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ እኔ በወሎ ክፍለ ሀገር ስር ነበርኩ እያለ በትግራይ ስር ካልገባህ ወይም በትግራይ ክፍለ ሀገር ስር ነበርኩ እያለ በወሎ ስር ካልገባህ ማለት ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ሌላውም እንደዚያው:: ስለዚህ የህዝቡ ትዝታ የሆነውን ታሪክ መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህዝባችን ደግሞ አካባቢያዊ በሆኑ ታሪኮች ላይ በደንብ የበሰለ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እዚህ ቦታ ላይ ነበርኩ እያለ በደንብ ይተርካል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አወቃቀሩ የማህበረሰቡን አኗኗርና አሠፋፈር መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባዋል:: አኗኗርና አሠፋፈር ስንል በኢኮኖሚ ደረጃ ማህበረሰቡ ተቀራራቢ የሆነ የስራ ስምረትና የህይወት ዘይቤ ያለው መሆን ይኖርበታል:: ለምሣሌ፡- አርብቶ አደር ከሆነ ከአርብቶ አደሩ አካባቢ ጋር እንጂ ከአርሶ አደሩ ጋር ለመቀላቀል መሞከር እርስ በእርስ ተጋደሉ እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አርብቶ አደሩ ስለተዘራው ሰብል በከብት መበላት ብዙ ላይገደው ይችላል፤ አርሶ አደሩም አንድ ሠፊ የግጦሽ መሬት ለአርብቶ አደሩ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ተረድቶ መብቱን ሊጠብቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረትን ያደረገ አደረጃጀት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የባህልና የስነ ልቦና ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በ1987 በፀደቀው ህገ መንግስት ላይ የሠፈረ ነው፡፡ ስለዚህ ባህልና ስነልቦና የሚለውን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል:: ለምሣሌ ቆላማ አካባቢዎች ላይ ያለው ህዝባችን በአመዛኙ ሙስሊም ነው፡፡ ደጋው አካባቢ ደግሞ የክርስትና አሠፋፈር አለ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ህዝቦች ስነልቦናቸው ተጠብቆ ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያደርግ አደረጃጀት ሊኖር ይገባል:: መብትንና ጥቅምን መሠረት ያደረገ የስነልቦና እና ባህልን ሁኔታ ያገናዘበ አሠፋፈርን የተከተለ ፌደራሊዝም መሆን አለበት፡፡ ስያሜውም በአስተዳደር ስቴት ነው መተካት ያለበት:: አካባቢን እንጂ ጐሣን ያጣቀሰ ስያሜ መሆን አይገባውም፡፡ ለምሣሌ ጋምቤላ አካባቢን እንጂ አንድን ብሔር አይገልጽም፤ ደቡብም እንደዚያው ነበር፡፡ በብሔር የሚሰየመው ግን ገፊ ነው፤ ትግራይ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሞ፣ አፋር ክልል ስንል ሌላውን በውስጡ ያለውን ገፊ ነው፡፡ ለምሣሌ አማራ ስንል አገዎችን፣ ዋጐችን፣ ላስታዎችን ወይጦዎችን፣ ቅማንቶችን፣ ከሚሴዎችን የሚገፋ ይሆናል፡፡ አካባቢውን ማን ነው የአማራ ብቻ ያደረገው? በውስጡ ያሉ ለዘመናት እዚያ የኖሩ ህዝቦች ሁሉ ነው:: ሌላው ክልልም በተመሳሳይ በውስጡ ያሉትን የሚደፈጥጥና ለአንድ ብሔር የሠጠ አሰያየምም አደረጃጀትም ነው ያለው፡፡  
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በርካታ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ የችግሮቹ መንስኤ ምንድን ነው?
በዋናነት ያልተወራረደ ሂሣብ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ አንደኛ የታሪክ ያልተወራረደ ሂሳብ አለ፡፡ በታሪክ እንደምንረዳው ባለፉት አምስት መቶና ስድስት መቶ አመታት አንደኛው ሃይል ከደቡብ ወደ ሰሜን ይገሰግሳል፤ ሌላኛው ደግሞ ከሰሜን ወደ ደቡብ ይገሰግሳል፡፡ ከዚያ ትንሽ የተረጋጋ መስሎ ደግሞ ግስጋሴው ይቀጥላል:: ይሄ የታሪክ ጉዞ አለ፡፡ ያ ጉዞ የፈጠረው ከፍተኛ የሆነ ያልተወራረደ ሂሳብ አለ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያሉ ህዝቦችን ሙሉ ለሙሉ በቋንቋም፣ በመሬት ይዞታም ውጧቸዋል፡፡ ይሄ የፈጠረው ትልቅ ችግር አሁን ላይ ላለው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ነው፡፡ ልብ ብለን ካጤንን ሁሉም ወደ ኋላ 150 አመትና 100 አመት ተመልሶ ነው በታሪክ ሲወዛገብ የምናየው፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬ 100፣ 1ሺህም አመት ወረራዎች ተካሂደዋል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ የዛሬ 30 አመትም ወረራዎች ተካሂደዋል፡፡ አብዛኞቹ በኢንቨስተር ስም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ወረራዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች እኮ ጭራሽ ነዋሪዎችን ጠራርገው አባርረው የዚያን ማህበረሰብ የደን ሃብት ሳይቀር ወደ ውጭ ሀገር ሸጠዋል፡፡ ወረራ ማለት ይሄ ነው:: ሁለተኛ አሁን ለተፈጠረው ችግር ዋነኛ መንስዔ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አለመኖሩ ነው፡፡ በፌደራል መንግስቱ ቀርቶ በክልልና በዞን ደረጃ ያሉ አስተዳደሮች ሳይቀሩ የስልጣን ሽግግራቸው ሠላማዊ አይደለም፡፡ በማባረር መባረር ላይ የተመሠረቱ ናቸው:: ምክንያቱም ስልጣናቸው ከህዝብ የመነጨ አይደለም፡፡ ሌላው የተረኝነት ስሜት ነው:: በነገራችን ላይ የተረኝነት ስሜት እጅግ መጥፎ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ላይ 85 ብሔረሰብ አለ እንላለን፡፡ በዚህ ላይ የተረኝነት ስሜት ሲጨመርበት 85ኛው ብሔር ስልጣኑን በተራው ለመያዝ እንኳ ጊዜ መጠበቅ አይፈልግም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አስተሳሰቦች ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ሶስተኛ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ፖለቲካና ኢኮኖሚ እርስ በእርስ የተጋባ ነው፡፡ ስልጣን መያዝ ጥቅምንም በእጅ ከማስገባት ጋር ይያያዛል፡፡ ስልጣን ሲያዝ መሬትን ማግበስበስ፣ የስራ እድሎችንም ጠቅልሎ መውሰድ፣ ያሉትን የፖለቲካ ሃላፊነት ቦታዎች ጠቅልሎ መውሰድ ነው፡፡ ይሄ አካሄድ ብዙ ተስፋ ያላቸው ወጣቶችን ተስፋ-ቢስ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች አሁን ይዘው እየወጡ ያለው ዱላ ነው፡፡ ይሄን በአንድ በኩል ስናየው በጐ ነው፤ ነገ ግን ጠመንጃ ይዘው ላለመውጣታቸው ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ይሄ አይነቱ ተጋድሎ እንዳይመጣ ነው ከወዲሁ በርካታ ስራዎች መሠራት ያለባቸው፡፡ አለበለዚያ ግን ይሄ ችግር ብዙ ጣጣ ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡
መጠኑ ይለያይ እንጂ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክልሎች ባለፉት ሁለት አመታት የተለያዩ ደም አፋሳሽ ሁከትና ብጥብጦች ተፈጥረዋል:: ነገር ግን በኦሮሚያ ከሌሎቹ ከፍ ባለ ደረጃ በየጊዜው ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በተደጋጋሚ በክልሉ ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋና መንስኤው ምንድን ነው ይላሉ?
ኦሮሚያ ክልል ላይ እያጋጠመ ያለ ችግር የባህልና የስነልቦና ጉዳይ የፈጠረው ነው:: እዚህ አካባቢ ላይ ያሉ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው በአንፃራዊነት በባህልና በስነልቦና የሚቀራረቡ አይደሉም፡፡ ለምሣሌ ሰሜን ሀረርጌ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ከምዕራብ ወለጋ ማህበረሰብ ጋ በጭራሽ አይገናኝም:: የሀረርጌና የባሌው ማህበረሰብ ከአርሲው ይለያል፡፡ ይሄ ሁሉ ባለበት የአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ይሄን አካባቢ አንድ መልክ ሰጠው፡፡ በሽግግሩ ወቅት ህወኃት፣ ኦነግና ሻዕቢያ አንድ ላይ ሆነው በቋንቋ ብቻ ኦሮሚያ ክልል ብለው ደነገጉ፤ ነገር ግን በባህል፣ በስነልቦናና ታሪክ አንድ ናቸው ወይ የሚለውን ለማየት አልተቻለም:: አፄ ምኒልክ በብዙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይወቀሳሉ፤ ነገር ግን አፄ ምኒልክ አንድ ለኦሮሞ ህዝብ ያደረጉት በጐ ነገር በጐሳ በባህልና በስነ ልቦና ተለያይቶ የነበረውን ህዝብ አንድ ሆኖ ለሀገሩ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻላቸው ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ህዝቡን ወደ አንድነትና አንድ አስተዳደር ለማምጣት ያደረጉት ጥረት በጐ ይመስለኛል:: ብዙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ግን መሬቱን ሲፈልጉ መሬቱ የኛ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን ያንን መሬት በአንድ አስተዳደር ያመጣውን ደግሞ ያወግዛሉ:: ይሄ ተቃርኖ በትርክት ደረጃ ችግር ያለበት ስለሆነና ያንን መሻገር ስላልተቻለ መሬቱ ላይም ያለው ነዋሪ መሻገር አቃተው፡፡ መቻቻል አቃተው::
መጀመሪያ ትርክቱ ከፍ ብሎ አቃፊ አስተሳሳሪ አወዳጅ መሆን ነበረበት:: እዚያ ላይ ባለመሠራቱ ምክንያት አፄ ምኒልክ የመሯቸው ዘመቻዎችና ውጤቱን የተመለከቱ ችግሮች አሁንም መሬቱ ላይ አሉ፡፡ ለምን ከተባለ ህዝብን ሊያለያይ እንጂ ሊያስተሳስር የሚችል ትርክትን የፖለቲካ ልሂቃኑ አላመጡም፡፡ ይሄ አስተሳሳሪ ትርክት ሳይኖር አንዳንዴ ኦሮሚያን እንገነጥላለን ይላሉ፡፡ እነሱ ይሄን ሲሉ ደግሞ ከውስጥ ይሄማ አይቻልም የሚሉ ነዋሪዎች አሉ:: ዋነኛው ኦሮሚያን በተመለከተ ያለው ችግር ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ በትግራይና አማራ ክልል ይሄ ችግር በስፋት የማይታየው ህዝቡን የሚያስተሳስረው ትልቅ ትርክት ስላለ ነው፡፡ ደቡብ ላይ ቢያንስ ባለፉት 27 አመታት ደቡብ የሚባል አስተሳሳሪ ትርክት ተፈጥሮ ነበር፡፡  አሁን ግን በዞንና በክልሉ አመራሮች ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡  
የተዛቡና ለሀገር አንድነት አደጋ የሆኑ ትርክቶችን እንዴት ነው ማቃናት የሚቻለው?
አሁን ያለው የታሪክ ትርክት ከምን የተነሳ የመጣ ነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል:: ማርክስ ታሪክን እንደ ቁስ አካል ነው የሚያየው፡፡ የሆነ ደረጃ መድረሻ መሣሪያ ማድረግን እንጂ እውነታው ላይ አይደለም የሚያተኩረው ማርክስ፡፡ ታሪክን እንደ ቁስ አካል ቆጥሮ የትግሉ መሣሪያ አድርጐት ስለሚነሳ ከሚፈልገው ግብ ለመድረስ ሁልጊዜ የጨቋኝ ተጨቋኝ ታሪክ ይፈጥራል:: ጠላትና ወዳጅ፣ የነበረ ያልነበረ፣ የሆነ  ያልሆነ የሚሉ ነገሮችን ይፈጥራል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለመድረሻ ግቡ የሚሆኑትን ብቻ ነው መርጦ የሚነሳው፡፡ አሁንም እንደምናየው በእኛ አገርም፣ በማርክሳዊ እሳቤ በተቃኘ መልኩ ለጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የሚጠቅማቸውን ብቻ እየጨለፉ በትውልድ ኪስ ውስጥ ይከቱለታል፡፡ ነገር ግን የኛ ታሪክ በማርክሳዊ እይታ የሚታይ አይደለም፡፡ የሀገር ምስረታና የሀገር ግንባታ ታሪክ ነው ያለን፡፡ ብዙዎቹ ህዝቦች ለዚያ ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡
ከደቡብ ወደ ሰሜንም፣ ከሰሜን ወደ ደቡብም የተደረጉ ዘመቻዎች የሀገር ግንባታው አካል ናቸው:: ለሀገር ግንባታ ደግሞ ግብር ማስገበር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሃያል የነበረው በሃይል ግብር ያስገብራል:: አሁንም ያለው ዘመናዊ የሀገር ግንባታም ግብር ማስገበርን መሠረት ያደረገ ነው:: አንድ የግዛቱ አካል ላይ ያለ ማህበረሰብ አልገብርም ሲል በሃይል እንዲገብር ያደርጋል:: ይሄን በቅርብ ጊዜ ታሪካችንም አይተነዋል፡፡ ስለዚህ ጥንትም ይሁን ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ የተደረጉ ጦርነቶች የሀገር ግንባታው አካል ናቸው፡፡ አሁን ያለንበት አገር በአጥንትና ደም የተገነባ ነው:: ጦርነቶቹም የጋራ ታሪካችን አካል ናቸው:: አንድ ማህበረሰብ በጦርነት ከተገናኘ አንድ የጋራ ታሪክ አለው:: አንዳንዶች የጋራ ታሪክ የለንም ሲሉ ይደመጣል፤ ይሄ ስህተት ነው:: እንኳን በአንድ ላይ ለሺህ አመታት የኖርን ህዝቦች ቀርቶ ጣሊያንና እኛም ባደረግናቸው ጦርነቶች የጋራ ታሪክ አለን፡፡
አንዱ የችግሮቹ ምንጭ ኢትዮጵያ የማን መልክ ይኑራት የሚለው ነው… ይሄ በዋናነት ከባህልና ቋንቋ አንፃር ነው ልንመለከት የምንችለው፡፡ በማን ቋንቋ እንወከል፣ በማን ቋንቋ እንጨፍር፣ በማን ቋንቋ ራሳችንን እናስተዋውቅ የሚል ነው፡፡ ከባህል አንፃር ደግሞ በየትኛው አለባበስ እንወከል፣ በየትኛው አመጋገብ እንወከል የመሳሰለው ነው ጥያቄው:: ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው:: ምክንያቱም ይሄ ሀገር በሶስት መልክአ ምድሮች የተካለለ ነው፡፡ ደጋ ወይና ደጋ፣ ቆላ የምንለው አለ፡፡ የቆለኛው አለባበስና ቋንቋ አንድ የሚያደርጉትና የሚያመሳስሉት አለ:: ለምሣሌ ነጠላ በሁሉም ይለበሳል፤ እንጀራ በሁሉም መልኩ ይለያይ እንጂ ይበላል:: ሌላው አለባበስ ነው፡፡ ይሄን በተመለከተ የብሔር ብሔረሰቦች ጥናት ማዕከል ውስጥ ከ1967 እስከ 1969 ተጠንተው የቀረቡ የመፍትሔ ሃሳቦች አሉ:: የኢህአፓ የፌደራሊዝም አንዱ መስመር ከእነዚህ ጥናቶች የመነጨ ነው፡፡
ብሔራዊ መዝሙራችን በአምስት ቋንቋ ይሁን ያልነው፤ አሠፋፈራችን ባህልን፣ ታሪክን፣ ቋንቋን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ያልነውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ዜጋ የትኛውንም ልብስ ቢለብስ የኢትዮጵያ እንደሆነ እንዲቆጠር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ መልካችን በምን ይወከል የሚለውን መገናኛ ብዙሃንና የባህል ተቆርቋሪዎች በሚገባ ሊሠሩበት የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ ሊያሻግሩ የሚችሉ መፍትሔዎች ምንድን ናቸው?
በመጀመሪያ ለመፍትሔ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ አመራሮች ዝግጁነት ይጐድላቸዋል፡፡ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ራሱ የመፍትሔው የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከፖለቲካ አመራሩ፣ ከተቃዋሚው፣ ከህዝቡም በኩል ፍቃደኝነት ያስፈልጋል:: ለመነጋገር ለመደራደር ፍቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ከተደረገ ችግራችን በብዙ መጠን ይቃለላል:: በሶስተኛ ደረጃ ለወደፊት የምትኖረን ኢትዮጵያ የተሻለች እንደሆነች፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ መስራት እንደሚያስፈልግ ማመን ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን “መሬት የማንም ናት ባለቤት የላትም/ ጐበዝ እየሄደ ያስገብራል የትም” እንዳለው ከበደ ሚካኤል፤ በዚህ መንገድ ነው የመጣነው፡፡
ከዚህ በኋላ ግን ጐበዝ ማለት የወደፊቱን መፃኢ እድል ተረድቶ ለዚያ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ የጨቋኝ ተጨቋኝ፣ገዳይ አስገዳይ ጉዳይን እያነሳን ነገን ማጨለም የለብንም፡፡


Read 2212 times