Saturday, 08 August 2020 13:39

በኢትዮጵያ መከሰቱን ለማመን የሚያዳግት የጭካኔ ተግባር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “ባለቤቴ በ200 ሰዎች ነው ተቀጥቅጦ የተገደለው”

     - ተጐጂዎች የደረሰባቸውን አሰቃቂ በደል በአንደበታቸው ይገልፃሉ
     - መንግስት ይድረስልን፤ ህዝብ መከራችንን ይስማ
     - መንግሥት አጥፊዎችን ይቅጣልን

        የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተለይም በኦሮምያ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከትና ግርግር ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውንና በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የመንግስትና የግል ሃብትና ኢንቨስትመንት መውደማቸው ተዘግቧል፡፡
ይሄ ዓይነቱ ዘገባ ከቁጥር ባሻገር የጥፋቱን መጠንና ዕልቂት በቅጡ አይገልፀውም፡፡ እንዴት? ብትሉ የጉዳት ሰለባዎቹ የደረሰባቸውን ሲናገሩ ከአንደበታቸው መስማት እውነታውን ያሳያል፡፡ የተፈፀመው ድርጊት አሰቃቂ ነው፡፡ በኢትዮጵየ ምድር ላይ የተፈፀመ ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ የጭካኔና አረመኔነት ጥግ የሚታይበት አሰቃቂ ክስተት አገራችን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው መቼ ነው የሚል ጥያቄም ያጭርብናል - የጭካኔና አረመኔነት ድርጊቱ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሰሞኑን በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ በጥሮ፣ አለምማያ፣ ባቲ፣ ሀረርና ኮምቦልቻ ከተሞች ተገኝታ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን አነጋግራለች፡፡ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ብሶት እነሆ፡-

                   “ባለቤቴ በ200 ሰዎች ነው ተቀጥቅጦ የተገደለው”

                 ሙስሊም ጐረቤቴ ሁለቱን ልጆቼን ደብቃልኝ ነው የተረፉት
                       (ወይዘሮ ወይንሸት ገብሬ፤ የጭሮ ነዋሪ)


            በእኔም ሆነ በቤተሰቤ የደረሰብን ሰቆቃ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ ሰኔ 23 ከባለቤቴ ከብርሃኑ ዝቅአርጋቸው ጋር የስራ ባልደረባችን ልጅ ሞቶ ቀብር ሄደን ነበር:: ከቀብር ስንመለስ ግርግር ተፈጠረና ገና ሀዘንተኞቹን ሳንሰናበት ነበር ቶሎ ብለን ወደ ቤት የመጣነው፡፡ አሰላ ብንወለድም እዚሁ ጭሮ ከተማ ውስጥ ነው የኖርነውም ሆነ ልጆች ወልደን ያሳደግነው፡፡ ባለቤቴ ቤት ከገባን በኋላ የጐረቤቶቻችን ፎቅ ሲመታ “ድረሱላቸው” እያለ ለህግ አካላት ሲደውል ነበር፡፡ “እኛን አይነኩንም፤ እኔን ሲያዩ ይመለሳሉ ተረጋጉ” ብሎን ነበር፡፡ ነገር ግን 200 የሚሆኑ ሰዎች የውጭውን በር ሰብረው ገብተው  (ወጣቶችም በእድሜም ጠና ያሉም) “በለው በለው” እየተባባሉ፤ የ5 ዓመት ልጄ አይኑ እያየ፣ እንደ እባብ ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡ ልጄ ሌሊት ሌሊት አባቴ እያለ እየተወራጨ ጥርሱን እያፋጨ በቅዠት ሲሰቃይ ነው የሚያድረው፡፡ ልጄ አዕምሮው ተቀይሮብኛል፡፡ “ልጆቹን ይዘሽ ሽሺ ይገድሉሻል” እያለ መትረፋችንን እንኳን ሳያይ ነው የሞተው፡፡
እኔ ያንን የ5 ዓመት ልጄን ይዤ እሪ ስል፣ አትርፉልኝ እያልኩ ስጮህ ሙስሊም ጐረቤቴ፣ ሁለቱን ልጆቼን ደብቃልኝ ነው የተረፉት፡፡ ባለቤቴ ሁለት ጊዜ ነው የሞተው፤ ምክንያቱም ወደ ህክምና እንዳይሄድ እንኳን ሬሳውን ሰው ቤት ውስጥ ደብቀው ቆለፉበት:: “ኧረ ባለቤቴ የት ሄደ እባካችሁ አፋልጉኝ” ስል በቀይ መስቀል አምቡላንስ ወደ ህክምና ተወስዷል ብለውኝ ነበር፡፡ ሁሉም ካለፈ በኋላ ግን አስክሬኑ ሰው ቤት ውስጥ ተደብቆ ነው የተገኘው፡፡ እስካሁን ባለቤቴ ለምን እንደተገደለ የምናውቀው ነገር የለንም፡፡ ይህን ሁሉ በደልና ግፍ የተቀበልነው በምን ምክንያት እንደሆነ አናውቅም፡፡ ቤታችን ወድሟል፣ ንብረታችን የለም፤ አሁንም ዘመድ ቤት ተጠግተን በልመና ነው ከልጆቼ ጋር እየኖርን ያለነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ፤ ወላድ ይፍረደኝ (ለቅሶ…)
ባለቤቴ ከሁሉም ጋር ሰላም ነው፡፡ በኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ሰራተኛ ነበር:: ከበፊት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ሲያገለግል ነው የቆየው፡፡ እኔም በዚሁ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው የምሰራው፡፡ ባለቤቴ ብርሃኑ በደግነቱ በተግባቢነቱ ነው የሚታወቀው:: “እኔን ሲያዩ ይመለሳሉ” ያለውም በዚሁ ቅንነቱ ነው፡፡ እኛ ሌላ ጠላት፣ ሌላ ገዳይ አልመጣብንም፤ እዚሁ እያየናቸው ያደጉ የዚሁ አካባቢ ሰዎች ናቸው ያጠቁን:: መንግስት የባለቤቴን ደም ያውጣልኝ፣ አስተማሪ የሆነ ቅጣት በገዳዮቻችን ላይ ይጣልልን፤ ያን ጊዜ ነው የምንጽናናው:: በእኛ የደረሰ በማንም አይድረስ በእኛ ይብቃ፡፡


               “17 የልጅ ልጅ ባየሁበት ከተማ ነው ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብኝ”

                    መጦሪያዬን፣ እምነቴን፣ ተስፋዬን ተነጥቄ ቁጭ ብያለሁ
                       (አቶ አበባው ከበደ፤ የአለማያ ከተማ ነዋሪ)


            እንድንተነፍስ ላበቃን አምላክ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ድምፃችን እንደታፈነ እንሞታለን ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር፡፡ ተንፍሼ መከራዬን አገር ሰምቶት፣ ለምን አሁን አልሞትም፤ አይቆጨኝም፡፡ ጥቃቱ ከደረሰ ልክ ዛሬ አንድ ወር ከአንድ ቀን ሆነው:: በዚህ በአንድ ወር ውስጥ የደረሰችልን ይህቺው የምንሞትላት የምንደበደብላት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ መጠለያም የሆነችን፣ የምንበላውንም የምንለብሰውንም ያቀረበችልን ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በዕለቱ ሥራ አድሬ ወደ ቤት በተመለስኩበት ሰዓት በግምት 3፡30 ይሆናል፡፡ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህፃናትን ከፊት አስቀድመው የውጭውን አጥር ገልብጠው ገቡ፡፡ እኔ በሰዓቱ እየታጠብኩኝ ነበር:: ቤንዚን በፕላስቲክ ጠርሙስ ሞልተው ይዘው እያርከፈከፉ፣ መስታወት እየሰባበሩ በመኝታ ቤት፣ በሳሎንና በተለያዩ ክፍሎች ያሉ ባለፉት 50 አመታት ያፈራሁት ንብረት ሲወድም፣ በእኔ ላይ ከባድ ድብደባ ተፈጽሞብኝ፣ በአዛውንትነቴ ላይ ይህ ጉዳት ሲጨመር ሰውነቴ በሙሉ ተሰባብሮ ደቅቋል:: በመጨረሻም ከፍተኛ መፍጨርጨር አድርጌ፣ ባለቤቴንና ልጄን ይዤ አንድ ክፍል ውስጥ ገብቼ በር ዘጋሁ:: በሩን ቀጠቀጡ ቀጠቀጡና አልሰበር ሲላቸው ትተው ሄዱ፡፡ እኛ ከሞት ተረፍን:: ከልጅነት እስከ እውቀት ሃብትና ንብረት ያፈራነው፣ ልጄ አረብ አገር ተሰቃይታ ያፈራችው ወርቅ፣ መዓት እቃ፣ ምን የቀረ አለ?! ውድም አለ፡፡
በጥቂት ሰዓት ውስጥ ቤታችን ወደ ፍርስራሽነት፣ ንብረታችን ወደ አመድነት ተቀየረ፡፡ በዚህ ውድመት ከ2.ሚ ብር በላይ አጥቻለሁ፡፡ ይህ የሆነው ከ50 ዓመት በላይ በኖርኩበት፣ 17 የልጅ ልጅ ባየሁበት፣  ከጐረቤቶቼና ከአካባቢው ጋር በደስታም በሀዘንም ተካፋይ ሆኜ በኖርኩበት ከተማ  ነው፡፡ ይሄ ሁሉ መከራና ውርደት የደረሰብኝ ይህን ሁሉ ህይወት ባሳለፍኩበት ዓለማያ ከተማ ነው፡፡ አሁን መጦሪያዬን፣ እምነቴን ተስፋዬን… ተነጥቄ ባዶ እጄን ቁጭ ብያለሁ:: የት ነው የምሄደው? ከአለም ማያ ከተማ ውጭ አገር የለኝም፤ አለምም የለኝም፤ ወገኖቼ እስኪ ፍረዱኝ (ሁሉም ተሰብሳቢ እንባ እየተራጨ፤)
“ከእገሌ ቤት ጀምረህ እገሌን ምታው” እየተባለ ስም ዝርዝራችን ተይዞ ነው ጥቃት የደረሰብን፡፡ ክርስቲያን መሆን ሀጢያት ነው እንዴ? ለማን ነው አቤት የምንለው?! “ልጆቻችን መጡብን ሊገድሉን ነው” እያሉ ሌሊቱን እየበረገጉ በስቃይ ላይ ነው ያለነው፡፡ ቆርቆሮ በንፋስ ኳ ባለ ቁጥር “መጡብን እንሽሽ” እያሉ ሌሊት ሌሊት እንቅልፍ የለንም፡፡ ቀጣይ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው? ለቀጣይ ህይወታችን ምን ዋስትና አለን? እንግዲህ መንግስት ምንድን ነው የሚያደርገን? አሁንም ማስፈራሪያና ዛቻው ቀጥሏል፤ “እንደጀመርናችሁ እንጨርሳችኋለን” እየተባልን ነው፡፡ ዋስትና የለንም፤ የዛሬ አዳራችንንም አናውቅም፤ መከላከያ ከዚህ ከተማ እንዳይነሳብን፤ እንዲጠብቀን ለዓለምና ለኢትዮጵያ ህዝብ ንገሩልን፤ ጩኹሉን፤ ድምፃችን ይሰማ፤ መከራችን ይታይ፡፡ እናንተም ጋዜጠኞች ቃላችሁን ጠብቁ፤ የተናገርነውን ወስዳችሁ ለሁሉ አሰሙልን፡፡ እኔ ይህን ተንፍሼ እንባዬን በማፍሰሴ ከላዬ ላይ የሆነ ሸክም የወረደልኝ ያህል ቀለል ብሎኛል፤ ክብር ለመድሃኒዓለም ይሁን፡፡



                 “ለ57 ዓመት ለፍቼ ያፈራሁት ሀብት ወድሞ ያለ መጦሪያ ቀርቻለሁ”
                         (ወ/ሮ ሽቶ ተገኝ፤)


            እኔ የ70 ዓመት አዛውንት ነኝ፤ በአለም ማያ 01 ቀበሌ ላለፉት 57 ዓመታት ኖሬያለሁ:: አግብቼ ንብረት አፍርቼበታለሁ፤ ከሰውም ጥሩ ፍቅር አለኝ፡፡ ምንም በማላውቀው ሰኔ 23 7፡30 ላይ ነው ዱብዳ የወረደብኝ:: እኔ ከሀረር 23 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኝ ኮምቦልቻ የምትባል ቦታ ችግር ተፈጠረ ሲባል፣ እዚያ ላሉ ዘመዶቼ ነበር ዋይ ዋይ እያልኩ የምጨነቀው፡፡ እኔንማ በኖርኩበት ባሳደግኳቸው ልጆች ማን ይነካኛል ብዬ አስቤ፡፡ ከዚያ ቀን በ7፡30 ላይ የውጭ” በር ገንጥለው ገቡ፤ መዓት ናቸው፡፡ “ልጆቼ ምን አደረግኳችሁ? ምን በደልኳችሁ?” ብዬ ጡቴን አውጥቼ “በጠባችሁት ጡት ይዣችኋለሁ፤ እኔ ከማን ነው ጠቤ? ምን አደረግኩኝ? እባካችሁ ተውኝ” ስላቸው፤ “አንቺን ማንም አይነካሽም፤ ነይ ውጭ” ብለው ከደረጃ ላይ ጐትተው ሜዳ ላይ ወረወሩኝ፡፡ “በእጄ የተወለዳችሁ ናችሁ፤ እኔም ለማንም ክፉ አይደለሁም፤ በፈጠራችሁ ተውኝ” ብልም አልሰሙም፡፡ “እሺ በእሳት አታቃጥሉኝ፤ ስቃዬን አታብዙት፤ ባይሆን አርዳችሁ ገላግሉኝ” አልኩ፡፡ የቤቱ ጭስ አፈነኝ፤ ጆሮዬም ተዘጋ፤ አይኔም ተደፈነ፡፡
የድንጋይ ናዳ ከላይ ይወርድብኛል፡፡ እኔ አክስት የሆንኳት ልጅ ቤት ነበረች፡፡ “ዛሬ እኔ ቀፎኛል፤ ተነሽ እንውጣ” ስትለኝ “አርፈሽ ቁጭ በይ፤ እኔን ማንም አይነካኝም፡፡ ይሄ ከተወለድኩበት ቦታ በላይ የምወደው፣ ወግ ማዕረግ ያየሁበት ቦታ ነው” ብዬ ቆይቼ ነው ይሄን ሁሉ መከራ የተቀበልኩት፡፡ እሷን አንዴ እሳት ውስጥ ይከቷታል፤ አንዴ ያወጧታል፤ በስንት መከራ ነፍሳችን ተረፈ፡፡ 57 ዓመት ሙሉ ያፈራሁትን ንብረት፣ ግሮሰሪዬን፣ እቃዬን፣ ገንዘቤን በሙሉ በእሳት አውደመው፣ አልቃጠል ያለውን ቴሌቪዥን… ፍሪጅ ስብርብር አድርገው ያለ መጦሪያ አስቀሩኝ፡፡ አሁን ጉልበቴ ደክሟል፤ ሰርቼ እተካዋለሁ አልልም፡፡ 70 ዓመት ሆኖኛል:: መጦሪያ የለኝም፤ (ለቅሶ)…ለምን ይሄ መከራ እንደደረሰብኝ አላውቅም፡፡
ከዚህ በኋላ ጐዳና ላይ ወድቄ ከመለመን ውጭ ሌላ ተስፋ የለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚህ ቤት  ፀሐፊ የሆነና አንድ ፖሊስ ተከራይ ነበሩኝ፡፡ ፖሊሱ “መሳሪያ ደብቋል፤ አውጪ” ብለው የሁለቱንም ተከራዮች ቤት ከእነ እቃቸው ነው ያወደሙት፡፡ መንግሰትና ህግ ባለበት አገር እንዲህ አይነት ለጆሮ የሚዘገንን ጥቃት ነው የደረሰብን፡፡ መንግስት አጥፊዎቹን ይቅጣልን፤ እኛስ እድሜያችን ሄዷል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖሩት ልጆቻችን ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ ዙሪያው ገደል ነው የሆነብን፡፡ ደማችን ፈሰሰ፤ ሀብታችን ወደመ፡፡ ወዴት እንድረስ? በቀጣይስ ሌላ መከራ አይደርስብን እንደሆነ በምን እናውቃለን? እስካሁን በምን ምክንያት ይሄ ሁሉ ግፍ እንደደረሰብን አናውቅም፡፡ መንግስት ይድረስልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳያችንን ይሰማልን፡፡ ከዚህ በላይ ምንም የምለው የለኝም፡፡ ያገር ያለህ፤ የወገን ያለህ… የመንግስት ያለህ መከራችን ይብቃ፡፡




                        “40 ዓመት በህክምና ያገለገለችውን እናቴን ቀጥቅጠው ገደሉብኝ”

                          የማይሽር ቁስል ይዣለሁ፤ መንግስት ደሜን ይመልስልኝ
                              (ሀኪም ሰራዊት ተረፈ፤ የዓለም ማያ ከተማ ነዋሪ)


                ዓለም ማያ ከተማ ውስጥ ብዙ ዓመት ኖሬያለሁ፡፡ ልጆቼን ሁሉ እዚሁ ከተማ ውስጥ ነው ወልጄ ያሳደግሁት፡፡ እናቴ ከአዲስ አበባ ከመጣች ገና ሃያ ቀኗ ነበር:: ሰኔ 23 የተፈጠረው ችግር ብዙ ጠባሳ ጥሎብን ነው ያለፈው፡፡ የዚያን ቀን ከእንቅልፋችን ስንነሳ አብራኝ የኖረች ጐረቤቴ፤ “ሀጫሉን ቀብረን ስንመለስ ሌላ ሰው መቅበር የምንጀምረው ከዚህ ቤት ነው” እያለች ብሔርና ሃይማኖቴን እየጠቀሰች ስታስተባብርብኝ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ ልጆቼን ሰብስቤ በሬን ዘግቼ፣ ቤት ውስጥ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ትንሽ ቆይተው እየጨፈሩ መጡ፡፡ የድንጋይ እሩምታ ቤታችን ላይ ያወርዱብን ጀመር፡፡ ባለቤቴ ተኝቶ ነበር፤ በዚህ ድንጋጤ ተነስቶ ወጣ:: በጣም ብዙ ድንጋይ ይወረውሩ ጀመር:: እኛ ግራ ተጋባን፡፡ የባለቤቴ የወንድሙ ባጃጅ በር ላይ ቆማ ነበር፡፡ መጀመሪያ እሷን ማንደድ ያዙ፡፡ ከዚያ በኋላ የመንግስት ሃይል እንዲደርስልን ብሎ ባለቤቴ ወደ ሰማይ መተኮስ ጀመረ፡፡ እሱ ሲተኩስ ትንሽ መለስ ይሉና እንደገና ግር ብለው ይመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የመካከለኛውን የውጭ በር ገንጥለው ገቡ፡፡ ባለቤቴን “አንተ ነፍጠኛ አማራ፤ ስምህም ቴዎድሮስ ነው፤ እንገድልሃለን፤ ና ውጣ” አሉት፡፡
ከዚያ እኔ ቤት አንዲት ልጅ ነበረች፡፡ “እሷ ኦሮሞ ነች እንዳትነኩ” ብለው ድንጋይ ውርወራውን አስቁመው፤ እሷ ከወጣች በኋላ እኛ ላይ ጥቃቱን ቀጠሉ፡፡ “እሷን አስወጥተህ እንዴት ደካማ እናቴን አታስወጣልኝም” ስለው “ፖሊስ እኮ ደጅ  አለ” አለኝ፡- ያ  እኔ ጋ የነበረችውን ሚስቱን ያስወጣው ሰውዬ፡፡ ፖሊስ ካለማ ብዬ፣ ባጃጁ እየነደደ የነበረበትን እሳት ዘልዬ ወጣሁና “እባካችሁ እናቴን አውጡልኝ፤ ልጆቼንም አውጡልኝ” አልኳቸው፡፡ ያኔ እኔን ይቀጠቅጡኝ ነበር፡፡ በዚህ መሃል እርዳታ ለመጥራት ወደ ሰማይ ሲተኩስ የነበረውን ባለቤቴን መሳሪያውን ነጥቀው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብቻውን ወሰዱት፡፡ ያኔ እኛ  ብቻችንን ቀረን፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውንማ ምኑን ከምኑ አድርጌ ልንገራችሁ… ወገኖቼ (ከፍተኛ ለቅሶ …) ልጄ እናቴን በእሳቱ ላይ እያንገዳገደ ይዟት ወጣና አሻግሮ አስቀመጣት፤ ምክንያቱም እናቴ የአስም በሽተኛ ስለሆነች ታፍና ልትሞትብን ሆነ፡፡ ከዚያም ልጄን ሰባት ቦታ ጭንቅላቱን ብትንትን አድርገው፣ በሜንጫ ጐኑን ወግተው ሲያበቁ፣ እናቴን ስታገለግል በኖረችበት አገር፣ ጭንቅላቷን በሜንጫም በድንጋይም ቀጥቅጠው፣ ልጄንም እናቴንም ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ሞተዋል ብለው ተዋቸው፡፡  ይኸው እኔን ያለ እናት አስቀሩኝ፡ (ለቅሶ)፡፡ ፖሊሶቹ ባለቤቴን ብቻ ይዘው ከሚሄዱ እኛንም ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ሊያተርፉን ይችሉ ነበር፡፡ ባለቤቴን ይዘው ሄደው ልክ እጥፍ እንዳሉ ቀሪዎቹ እኔን ይሄ እግሬን በጥይት መትተውኝ ጥይቱ በአንድ በኩል ገብቶ በዚህ ወጣ (እግራቸውን እያሳዩ) ከዚያ እኔም አቃተኝ፡፡ እናቴና ልጆቼም እዛ ወድቀው የሚያነሳቸው አጥተው፣ ከአንድ ሰዓት በላይ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ ልጄ ወድቆ “ውሃ ውሃ” ሲል ሰዎች ሊያነሱት ሲመጡ፣ ስታስተባብርብኝ የነበረችው የጐረቤቴ ልጅ “እስኪ ወንድ አንድ ሰው መጥቶ ያንሳው” በማለት ሁለት ጊዜ ከሰዎች እጅ ላይ ውሃውን ተቀብሎ ደፋው፡፡ እኔ ምን አይነት ጉድ እንደመጣብን አላውቅም፡፡ ሁለተኛውን ጉድ ልንገራችሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ልጄንና እናቴን ሃኪም ቤት ለመውሰድ እንኳን ሌላ ፈተና ገጠመን፡፡ እኔ በጥይት መመታቴና ሽባ መሆኔ ሳያንስ፣ በሜንጫ አንገቴን ሊቆርጡኝ ሲሉ አንዷ እግዚአብሔር ይስጣት፣ ጐትታ ቤቷ አስገባችኝና በር ቆለፈች፡፡ ይመጣሉ በር ይደበድባሉ፤ “የለችም ሄዳለች” ትላቸዋለች፤ ተመልሰው ይመጡና በር ይመታሉ፡፡ በጣም ከፍተኛ መከራና ስቃይ ነው የደረሰብን፡፡
እኔ ተቆልፎብኝ እሰማለሁ፤ “ልጁም አሮጊቷም ሞተዋል” እያሉ በኦሮምኛ ሲያወሩ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ እነሱ ሞተው የኔ መትረፍ ዋጋ የለውም ብዬ ተጐትቼ በሩን ከፈትኩና ወጣሁ፡፡ ሁለቱም ወድቀው ደማቸው ይፈስሳል፡፡ “ኡኡ” አልኩ፤ ለፍልፌ ለፍልፌ “ኡኡ” ብዬ አንድ መኪና መጣ፡፡ ስንትና ስንት ቦታ ተደውሎ አንዲት ፀበል ላይ የነበረች ጓደኛዬ “እህቴ እየሞተች ነው” ብላ ቤተ - ክርስቲያኑን በጩኸት ስታናጋው፣ በስንት ሰው ጩኸት ተነስተን ሃኪም ቤት ከሄድን በኋላ፣ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም እንደነገሩ ሰፋፏቸው:: እኔና እናቴን ግን ምንም አላደረጉልንም፡፡ ከሀረር ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎልን ድሬደዋ ለመሄድ እዚህ አለማያ መጣን፤ አጃቢ እንዲሰጠን፡፡ ከግማሽ ሰዓት በላይ አጃቢ እንዲሰጠን ብንጠይቅም “መልሳችሁ ሀረር ሆስፒታል ውሰዷቸው፤ አጃቢ የለንም፤ መንገድም ዝግ ነው፤ ምንም ማድረግ አንችልም” አሉ፡፡ ሹፌሩ እግዚር ይስጠው “እኔ እስከ መጨረሻው እሞታለሁ እንጂ አልመልሳቸውም” ብሎ በሁለት አምቡላንስ ነው የሄድነው፡፡ ሹፌሮቹ ራሳቸው መንገድ የተዘጋበትን ድንጋይ እያነሱ ማታ 12፡00 ድሬደዋ ማሪያም ወርቅ ሆስፒታል ገባን፡፡ እዛ እየተረዳን ቆየን፡፡ ለእናቴ ከአዲስ አበባ ድረስ ኒዮሮሎጂስት  መጥቶ ህክምና ተደረገላት፤ ጭንቅላቷን በጣም ስለተመታች፤  ልትተርፍ አልቻለችም፡፡ በ6ኛው ቀን ሰኔ 29 አረፈች፡፡
እናቴ ካራሚሌ ሆስፒታል ከ40 አመት በላይ ያገለገለች ሀኪም ናት፡፡ ድሮም “ብሞት ካራሚሌ ወስደሽ እንድትቀብሪኝ አደራ” ትለኝ ነበር፡፡ ሆኖም ካራሚሌ ወስደን መቅበር አልቻልንም፤ ድሬደዋ ደብረመንክራት መድሃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀበረች፡፡ እኔም ሆስፒታል ነበርኩኝ፤ እናቴ በዚህ ዓይነት ወድቃ ቀረች፤ የደረሰብን መከራ አይነት ብዙ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎ በነጋታው በሰኔ 24 መጥተው፣ ቤታችንን በድጋሚ አቃጠሉት:: ይህንን አቃጥለው ሲያበቁ ገጠር ውስጥ መልካ ገመቹ የሚባል ክሊኒክና ፋርማሲ ነበረን፡፡ እኔም ከ20 ዓመት በላይ አገርና ህዝብ ያገለገልኩ ሀኪም ነኝ:: እዚያ ገጠር  ድረስ ሄደው 7 ክፍል ቤት የሆነውን ፋርማሲና ክሊንክ አቃጥለው እንዳልነበረ አደረጉት:: ሁለት ሶስት ጊዜ ነው የገደሉን፡፡ በጥናት ስማችን ተለይቶ ተይዞ፣ ከከተማ ውጪ ያለ ንብረታችን ሳይቀር ነው የተቃጠለው፡፡ እናቴን ቀጥቅጠው የገደሉት፣ እኔን በጥይት መትተው ሽባ ያደረጉኝ፣ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም ጭንቅላታቸውን መዓት ቦታ ፈነካክተው ደማቸውን ያፈሰሱት፤ እኔና እናቴ አዋልደን ከልጆቻችን ጋር ያሳደግናቸው የምናውቃቸው ልጆች ናቸው፡፡
እኔ ክሊኒኩን ልጄ ደግሞ ፋርማሲውን ይዘን በገጠር የምንሰራበትን ሁሉ ሲያጠፉት ሲያወድሙት፣ የከተማው መኖሪያ ቤታችን ሲቃጠል፣ ባጃጃችን በራችን ላይ ሲነድ፣ የቤተሰቤ ደም አስፋልት ላይ ሲፈስስ ፖሊስ ደጃፋችን ላይ ቆሞ ነበር፡፡ የቤታችንንም እሳት ማጥፋት፣ እኛንም ከሞትና ከጉዳት መታደግ ይችሉ ነበር፡፡ ከሁሉም ከሁሉም የእናቴ ነገር ነው የሚያንገበግበኝ፤ እዚህ ቦታ በዚህ ሁኔታ መሞት አልነበረባትም:: የእድሜ ልክ ፀፀት ነው የሆነብኝ፤ በሰላም ከተቀመጠችበት ከአዲስ አበባ አምጥቼ አስገደልኳት (ለቅሶ) የኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግስት፣ እናት ያለው፣ ልጅ የወለደ ሁሉ ይፍረደኝ፤ ባለቤቴ ታስሮ፣ ንብረታችን ወድሞ፤ እናቴን ቀብሬ እኔ ሽባ ሆኜ፣ ጭንቅላታቸው ወንፊት የሆኑ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም ይዤ ሜዳ ላይ ወድቄያለሁ፡፡ መቼም ቢሆን የማይሽር ቁስል ይዣለሁ፤ ፍረዱኝ፤ መንግስት ደሜን ይመልስልኝ እላለሁ፡፡  

Read 3207 times