Tuesday, 11 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የትኛው ይቅደም?
(መላ ቲዩብ)
የኢትዮጵያ በሁለት እግር መቆም ከእነሱ አንድ እግር እሚቀንስ እሚመስላቸው ምስር እና ወዳጆቿ ምን እንዳየ አሞራ በላያችን ላይ ይዞራሉ፡፡ አለም አቀፍ የሀይል ተገዳዳሪዎች አገራችንን ወደ አፍሪካ ለመግባት እሚጠቀሙባት መስፈንጠሪያ እንደሆነች በማሰብ በጎዳናዎቻችን ላይ ትክሻ ይለካካሉ፡፡ አለምን ግራ ቀኝ ሲያስረግጡ የነበሩ የቀድሞ ጉልበተኞች፤ የነበረውን የዛገ አሰላለፍ (status quo) እንዳይነካ ለማድረግ በሚድያና ዲፕሎማቶቻቸው በስሱ እሚታይ ጫና ጀምረዋል …. በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ … የቤት ስራችንን በይደር ይዘን የከበበን ባለ ግዜ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ፈንታ … ወግቶ በማያደማ ቀንዳችን እርስ በእርስ በመገፋፋት ላይ ነን፡፡
የዛሬውን ፍትጊያ መጨረሻ በእርግጠኛነት መናገር ባንችልም ... ትላንት የተፈፀሙ አንጸባራቂ ድሎች በመከፋፈል እንዳልተገኙ ከአድዋ የተሻለ አስረጂ የለንም:: በሚገርም ሁኔታ ሀገር ውስጥ ያሉ ሀይሎች …. ግድባችን ላይ ሲያነሱ የነበረው ስጋት እና ሰሞንኛ ትችቶች የአረፍተ ነገር ለውጥ ሳይደረግባቸው … ቃል በቃል ከግብጽ ሚዲያዎች ሲደገሙ ስንመለከት …. አጀንዳ እየተሰጠ ያለው ከግብጽ ለሀገር ውስጥ ሀይሎች ነው … ወይስ ከሀገር ውስጥ ሀይሎች ለግብጽ ብለን ግራ እንድንጋባ አድርጎናል፡፡
መላ ትላለች… አሁን ላለንበት ችግር ከጓያ ነቃዩ ምክር የተሻለ ነገር መናገር አይቻልም …. “ ቅድሚያ የፊት የፊቱን”፡፡
የተረሳው የሰብአዊ መብት መርሕ፡ Fraternity - ፍቅረ ቢጽ
(በአማን ነጸረ)
የፈረንሳይ አብዮታውያን ካነሷቸው 3 የሰብአዊ መብት መርሆዎች አንዱ ወንድማማችነት /ፍቅረ ቢጽ/ ነው ይባላል:: አልሰመረለትም እንጂ ዶ/ር ዐቢይም የመርሑን መዘንጋት (ችላ መባል) በመጽሐፉ ያነሣዋል፡፡ መርሑ በመጽሐፍ የሌለ አይደለም፡፡ በክርስትና - ደጋግመን እንደምንለው - አንድ ሰው ብቃት ላይ ሲደርስ ያለ ልዩነትና ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም መውደድ ይችላል፤ ምዕመን መናፍቅ፣ የዚህ ዜጋ የዚያ ዜጋ፣ የዚህ መንደር የዚያ መንደር፣ ጻድቅ ኃጥእ፣ --- ማለት ያቆማል፡፡ የክርስትና ጥጉ ይሄ ነው፡፡ የመጽሐፍ መጠቅለያ እግዚአብሔርንና ወንድምን መውደድ         /ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር/ ነው ይባላል፡፡ በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሁሉ ወንድም ነው፡፡
ደስ የሚለኝ የመጽሐፈ መነኮሳት ቃል አለ፤ ‹‹እመሰ ኮንከ አንተ ወልዱ ለእግዚአብሔር ኩሉ ሰብእ ይኩኑ አኃዊከ - አንተ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ሰዎች ሁሉ ወንድሞችህ ይሁኑ›› ይላል:: በዚህ ዓለም እንደ ክርስቲያን ስትኖር ሁሉንም ሰዎች ያለቅድመ ሁኔታ መውደድ ግዴታ ነው፡፡ መንፈሳዊና ሥጋዊ ተዛምዶ መስፈርቱ አይደለም፡፡ እንደ ዓለማዊ ሰውም መዋደድ በራሱ ሰብአዊነት ነው፤ መብት ነው፡፡ መብትነቱ ሂደት ከሚጠይቁት ወይም ለመሟላት በቢሮክራሲ ከሚያልፉት ወገን ነው ቢባልም ወንድማማችነት መብት ነው:: ስለዚህ ይህን የጽድቅና የመብት መርሕ ጥሶ ጥላቻ መዝራት፣ መራራቅን መጋበዝ፣ ከራስ ሕሊና እየታገሉ ሰውን የፍላጎት መሣሪያ ያውም ለመራራቅ መሣሪያ ማድረግ ኃጢአትም ወንጀልም ነው:: ይህን ኃጢአትና ወንጀል በቀና ልቡና ለማስቀረት የሚታገሉትን ሁሉ በሐሳብም በተግባርም በጸሎትም ማገዝ ቁጥሩ ከጽድቅ ነው፡፡ በጾሙ ጸሎት እናደርግበታለን!
ሳላገኝሽ በፊት
(ሙሀመድ ሙፍቲ)
እንዲህ ነው ‘ማይባል፣
ብዙ ነው ክፍተቴ ሞልቸው የሚጎል፣
ባይመሽም ግብግብ በተነደለው ቀን አንዳቹ ሲታጎል።
ግን አንቺ ስትመጪ ...
አለ አይደል ....
“ብቻነት ገምድሎ፣
ሰው ለሰው ታድሎ፣
አብሮነት ድልዳሉ እህል ውሃ ሲያዝል፣
ጭርታ ጂል ክንዱ ጉልበት ከድቶት ሲዝል፣”
.እንደዛ አይነት ነገር።
.አይነት ግን ምንድን ነው?
.ወይም አለ አይደለ ....
.በዛሬው መራመድ፣
ወደ ነገ መድረስ ተስፋ መቀጠሉ፣
ባብሮ ፍቅር ቀንዲል ብርሀን ማንጠልጠሉ፣
ትናንትን አራግፈው፣
ከፉ ወቅትን ገፈው፣
ህልም አለሙን ገርተው ነገን ሁነው መንጋት፣
በመውደድ ማለዳ በተመስገን ልሳን በፍቅር ጧት ማውጋት፣
አይነት።!
ብቻ አንቺ ስትመጪ ...
ህላዌ ደጃፍ ላይ፣
ጤዛ ጋር እረግፎ ...
ያልነበር የሆነው ... የነበረው ሁሉ፣
አንቺ ስትሄጂ ካገረሸው መሀል የርምጃዬ አመሉ፣
መንሻፈፍ ጀምሯል የግራዬ ጫማ ወደ ግራ ሶሉ።
ብቻ ምን ልልሽ ነው ...
እንኳንስ እድሌን ደግ እጣየን መግለጥ፣
የክፋቴን ወና ባብሮነትሽ
ነድድ ሊፈስ ባንቺ መቅለጥ፣
ገላ ነፍሴን ቀርቶ፣
አላውቅም ነበረ ያበጃጀን ጊዜ የሰራኝ ዘመንሽ፣
በባዕዱ ጫማ ለርምጃዬ ሙላት ውሃ ልኩ እንደሆንሽ።
ወትሮም ...
ትናንት የጎደለው፣
በነበር ሊተረክ በዛሬ ይሞላል፣
(ዛሬም ትናንት ነው!)
ዛሬ ደጉን ላይደግም ሱሉሱን አዛውሮ ነገ ላይ ይጎላል።
ቆይ ግን ውዴ ...
ትናንት ምን ይመስላል?
ዛሬ ምን ያክላል?
ነገስ ምን ይሆናል?
እንጃ!

Read 4718 times