Saturday, 08 August 2020 12:34

በክረምቱ 2 ሚ. ዜጐች በጐርፍ ሊጠቁ ይችላሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  በአፋር አሳይታ 1ሺህ ሰዎች በጐርፍ ተከበው ሰንብተዋል

           የክረምቱን ማየል ተከትሎ በተያዘው የነሐሴ ወር ከወትሮው ከፍ ያለ የጐርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን፤ የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፤ እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጐች በጐርፍና ተያያዥ ችግሮች ሊጐዳ ይችላሉ ብሏል፡፡
የዘንድሮ ክረምት ከመግቢያው ጀምሮ ጠንካራ መሆኑን ተከትሎ ባልተለመደ መልኩ በሐምሌ ወር የወንዞችና ግድቦች ሙላት ማጋጠሙን ለአዲስ አድማስ የገለፁት በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቅ ቡድን መሪ አቶ ነጊዬ ሃይሉ፤ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳም ከሁለት ሣምንት በፊት ጀምሮ በተፋሰሱ ያሉ አካባቢዎች በጐርፍ መጠቃታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከሁለት ሣምንት በፊት በአዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ በተባሉ አካባቢዎች ከ1ሺህ በላይ አባወራዎችን የአዋሽ ወንዝ ሙላት ማፈናቀሉን እንዲሁም ከሰሞኑ አፋር አሳይታ ላይ የሁለት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 1ሺህ ያህል ሰዎች በጐርፍ መከበባቸውንና የነፍስ አድን ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ነጊዬ ገልፀዋል፡፡
በጐርፍ ሙላት ተከብበው የሚገኙ የአሳይታ ነዋሪዎችን ከአደጋው ለመታደግ በሄሊኮፕተርና በግመሎች ድጋፍ ሰዎችን የማውጣት ስራ እየተሠራ መሆኑንም የቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡
አስቀድሞ የወንዝና የግድብ ሙላት መከሰቱ፣ በቀጣይ ነሐሴ ወርም ዝናቡ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ጠንካራ የጐርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መገመቱን የጠቆሙት አቶ ነጊዬ፤ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ቀደም ብሎ በመገመቱና ጉዳቱ ሊያጋጥም የሚችልባቸው አካባቢዎች በመታወቃቸው የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ሲያስጨብጡ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡
ከፍተኛ የወንዝ ሙላትና የጐርፍ ጉዳት እንደሚከሰትባቸው ከተገመቱ አካባቢዎችም በዋናነት የአዋሽ ተፋሰስ ማለትም ሰበታ፣ ኢሉ፣ ሊበን ጭቋላ፣ ቦራ፣ አዳማ፣ አፋር እስከ አፋምቦ ያሉ አካባቢዎች ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡
በጋምቤላም የባሮና አኮቦ ወንዝ ሙላት በሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የተገመተ ሲሆን የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ፣ የጣና ዙሪያ እንዲሁም ደቡብ ኦሞ ያንጋቶምና ዳሰነች አካባቢ የወንዝ ሙላትና የጐርፍ አደጋ ይከሰታል የሚል ስጋት መኖሩ ተጠቁሟል፡፡
በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎችም የመሬት መንሸራተትና ቅጽበታዊ የጐርፍ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ የሚገመት መሆኑን የጠቆሙት የቡድን መሪው፤ ችግሩ ሊያጋጥምባቸው ይችላል የተባሉ አካባቢ ነዋሪዎች ከወዲሁ ወደተሻለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ለየወረዳዎችና አካባቢ አስተዳደሮች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በክረምቱ በጐርፍና ተያያዥ አደጋዎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚጠቁ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 4መቶ ሺህ ያህሉ ይፈናቀላሉ ተብሎ መገመቱን  የገለፁት አቶ ነጊዬ ሃይሉ፤ በተገመተው መጠን ለአደጋው ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግድት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
ለጐርፍ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስቀድመው ወደ ተራራማ ቦታዎች እንዲወጡ ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል፡፡  




Read 8636 times