Saturday, 08 August 2020 12:36

የአስራት ቴሌቪዥን 4 ጋዜጠኞች ፍ/ቤት ቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 የአስራት ቴሌቪዥን አራት ጋዜጠኞች በኦሮሚያ ክልል ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ ተጠርጥረው መታሠራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤት ያመለከተ ሲሆን፤ በጋዜጠኞቹ ላይ የ13 ቀን የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የአስራት ቴሌቪዥን አዘጋጅና የፕሮግራም ኃላፊ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ጨምሮ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር፣ ኤዲተርና የካሜራ ባለሙያው ምስጋናው ከፈለኝ እንዲሁም ከጣቢያው ከወራት በፊት የለቀቀው ጋዜጠኛ ዮናታን ሙሉጌታ ባለፈው ረቡዕ የታሠሩ ሲሆን፤ ትናንት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡ ፖሊስም ጋዜጠኞቹ ተጠርጥረው የታሠሩት በሚሠሩበት አስራት ሚዲያ፤ ከህዳር 12 እስከ ሰኔ 2012 ድረስ የአማራ ህዝብ በተለየ ሁኔታ እንደተበደለ፣ መንግስትም የአማራ ህዝብን መከላከል እንዳልቻለ ፕሮግራሞችን በማቅረባቸውና በመዘገባቸው ደምቢዶሎን ጨምሮ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ለሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል የሚል መሆኑን ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኞቹ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ ደምቢዶሎን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ መርማሪ ልኮ የማሰባስበው ማስረጃ አለኝ፤ ለዚህም 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሠጠኝ ሲል ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡
ፍ/ቤቱም ከተጠየቀው 14 ቀን፣ 13 በመፈቀድ የምርመራ ውጤቱን ለመስማት ለነሐሴ 13 ቀን 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የጋዜጠኛ በላይ ማናዬና የካሜራ ባለሙያውና ኤዲተሩ ምስጋናው ከፈለኝ መኖሪያ ቤት ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በፖሊስ መበርበሩም ታውቋል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ፣ ለተፈጠሩ ሁከትና ግርግሮች ምክንያት ሆነዋል ተብለው በጠቅላይ አቃቤ ህግ ከተጠቀሱ ሚዲያዎች መካከል አስራት አንዱ የነበረ ሲሆን ተቋሙ በበኩሉ፤ ስሜ ያለ አግባብ ጠፍቷል፤ ድርጊቱ ከመፀፈሙ ሁለትና ሶስት ሳምንታት በፊት ሥርጭቴን አቋርጬ ነበር ማለቱ ይታወሳል፡፡

Read 9139 times