Saturday, 08 August 2020 12:19

የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻ እንዳይሸጥ ኢዜማ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ያለ በቂ ጥናትና ውይይት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለውጭ ድርጅቶች ለመሸጥ የተያዘው እቅድ በአስቸኳይ እንዲታጠፍ ኢዜማ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መንግስት ያለ በቂ ውይይትና ግልጽነት በጐደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እያደረገ ያለው ጥረት የወቅቱን የአለማቀፍ የቴሌኮም ገበያ ሁኔታን ከግምት ያላስገባና አክሳሪ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
“የቴሌኮም ዘርፍ የሃገር ደህንነትን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው” ያለው የኢዜማ  መግለጫ፤ መንግስት የቴሌኮም ዘርፍን እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፊያ ብቻ በማየት ለውጭ ድርጅቶች ለመሸጥ የጀመረው መንገድ ፍፁም አደገኛና የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል ብሏል፡፡
የቴሌኮም ዘርፍ በአሁን ዘመን የመረጃ ማስተላለፊያ ብቻ ሳይሆን የወታደራዊ ፋይናንስና የመገናኛ ብዙኃን ስርአቱን ለመቆጣጠር ሚናው የጐላ መሆኑን ማሳያዎች ጠቅሶ ያስረዳው ኢዜማ፤ አሁን ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በገቢ ደረጃ እጅግ አትራፊ ከሆኑ የመንግስት ተቋማት ዋነኛው በመሆኑ ባለበት ሊቀጥል ይገባዋል ብሏል፡፡  ሌላው ኢዜማ ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ እንደማይገባ ማሳያ ያደረገው ከኮቪድ 19 በኋላ የአለማቀፍ የቴሌኮም አክሲዮን ድርሻ ዋጋ በእጅጉ የመቀነሱን ጉዳይ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ 40 የሚጠጉ ትልልቅ አለማቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ ዋጋቸው ቀይ ዞን ውስጥ መግባቱን ኢዜማ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ ወቅት የሚፈፀም ተቋማትን በሽያጭ ወደ ግል የማዞር ሂደት እጅጉን አክሳሪ መሆኑን ኢዜማ አመልክቷል፡፡

Read 8736 times