Monday, 03 August 2020 00:00

የፖለቲካችን መዋቅራዊ ችግሮች

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(2 votes)

 (ክፍል ሦስት)
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሃገራችን ገንነው የሚታዩ የፖለቲካ ውይይቶች በአብዛኛው የሚያተኩሩት የተናጠል ሁነቶችንና ዑደቶችን በመተንተንና የግልም ሆነ የድርጅት አቋምን በማንጸባረቅ ላይ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ነጥብ የማስቆጠሪያ አካሄድ በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ፣ የተረጋጋ ሃገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ጠቃሚና የፖለቲካውም ዋነኛ መገለጫ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ በሌለበት ግን ጽንፍ ለያዘ ንትርክ ከማጋለጡም  ባሻገር፣ ለተባባሰ የፖለቲካ ቀውስ ሊዳርግ  ይችላል። የምህዳራዊ አስተሳሰብ አንዱ ዋነኛ መለያ ከተናጠል ሁነቶችና ዑደቶች ባሻገር በመመልከት፣ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ሞዴሎችንና መዋቅራዊ ምንጮችን መለየትና መፍትሄ መሻት ነው። በክፍል አንድ ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ህመሞች ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ የተመለከትን ሲሆን፣ በሁለተኛው ክፍል ጽሁፍ ደግሞ እነኚህን ህመሞች በአግባቡ ለመረዳትና መፍትሄ ለመሻት ሊያግዙ የሚችሉትን መሰረታዊ የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች ዳስሰናል። በነኚህ ቀዳሚ ሁለት ክፍሎች የቀረቡት ሃሳቦች በፖለቲካችን ውስጥ ሊኖረን የሚገባንን መሰረታዊ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ናቸው። በዚህ ሶስተኛ ጽሁፍ ከፖለቲካችን ዋና ዋና መዋቅራዊ ችግሮች ጥቂቶቹን ቀደም ሲል ከቀረቡት የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች አኳያ ለመመልከት እንሞክራለን።
የመጀመሪያው፣ በሃገራችን ታሪክ የሚታወቀው ሁለት ጽንፍ የያዘ አመለካከት ነው። ባንደኛው ጽንፍ፣ ኢትዮጵያ ቀደምትና እጅግ አኩሪ የሆነ ታሪክ ያላት አገር ናት በማለት ባንዳንድ የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ አሳዛኝና አሳፋሪ የታሪክ ክስተቶች አልነበሩም፣ ቢኖሩም በሌሎችም ሃገሮች ምስረታ የታዩ በመሆናቸው የተለየ ትኩረት አይገባቸውም ብሎ ያምናል። በሌላኛው ጫፍ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር ከአንድ መቶ ሃያ ወይም ሰላሳ ዓመት ወዲህ በነበሩ ወረራዎች የተፈጠረችና ታሪኳም የህዝቦች ጭቆናና ግፍ ታሪክ ነው የሚል ነው። ስለሆነም ይህ ታሪክ ከመሰረቱ መቀየር አለበት ይላል። በዚህ ፀሃፊ እምነት፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ልዩ ስፍራ የሚያሰጣት ታሪክ እንዳላት ብዙም የሚያከራክር አይደለም። ያም ሆኖ ግን፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ እንደ ብዙዎቹ ሃገሮች ኢትዮጵያም አንፀባራቂ የህዝቦችና አሳፋሪ የሥርዓቶች ታሪክ ምዕራፍ አሳልፋለች። በመሆኑም፣ ያለን ብቸኛውና ጠቃሚው መንገድ ከዚህ የታሪክ ዕውነታ በመማር፣ በአኩሪ ና ጠቃሚው የህዝቦች ታሪክ ላይ መገንባትና አሳፋሪውና ጎጂው ሥርዓት ዳግም እንዳይፈጠር መጣር ነው። እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ የምንፈልገውን የፖለቲካ ሥርዓት  በብሔራዊ መግባባት ላይ ለመገንባት ክፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።   
ሁለተኛው፣ መዋቅራዊ ችግር የዴሞክራሲ ሥርዓቱን የሚመለከት ሲሆን፣ ባንዱ ጫፍ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት አሁን ሰፍኖ ካለው የብሔር ፖለቲካ ተቀይሮ በግለሰብ ነፃነት ላይ ወደ ተመረኮዘ የዜግነት ፖለቲካ በአስቸኳይ ካልተሸጋገረ ሃገሪቱ በማያባራ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ትቀጥላለች ብለው ያምናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የብሔር ጥያቄ የሀገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ጥያቄ በመሆኑ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓትም በዚሁ ዙሪያ ከመዋቀር ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ በግለሰብ መብትና ቡድን መብት መካከል ጥብቅ የሆነ መተሳሰር ከመኖሩም በላይ ባንዱ ላይ ብቻ የተመረኮዘ የፖለቲካ ሥርዓት የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሆናል ተብሎ አይታመንም። በተጨባጭ ካለው አለም አቀፍ ተመክሮ እንደምንረዳው፤ በፍጹማዊ የግለሰቦች ነፃነት ላይ የተመረኮዘ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተናል ብለው የሚኩራሩ በርካታ የበለፀጉ ሀገሮች በተለያየ ወቅት በሚነሱ የቡድን ጥያቄዎች ሲፈተኑ ኖረዋል፤ ወደፊትም ይፈተናሉ። በቅርቡ በአሜሪካ የተነሳው የጥቁር ህዝቦች በህይወት የመኖር መብት ጥያቄ በግለሰቦች መብት መጠበቅ ሽፋን ስር ለሰደዱ የቡድን መብት ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። በኢትዮጵያም ሁኔታ ለረዥም ዘመናት የነበረውን የብሔረሰቦች መብት ጥያቄን መመለስ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ወደ ጎን ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን፣ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሚወሰዱ እርምጃዎች በምንም አይነት አግባብ የዜጎችን ወይም የግለሰቦችን በህይወት የመኖር፣ የመሳተፍና የመበልፀግ መብቶችን የሚገድብ ሊሆኑ አይገባም። ስለሆነም የብሔረሰቦችን መብት ከዜጎች መሰረታዊ መብት ጋር ማጣጣም የወደፊቱ የፖለቲካ ሥርዓታችን ዋነኛ መገለጫ ሊሆን ይገባዋል።
ሶስተኛው፣ ፈተና፣ አሁን በስራ ላይ ካለው ህገ መንግስት ጋር የተያያዘ ነው። ባንድ በኩል፤ አሁን ያለው ህገ መንግስት በመሰረታዊ ባህሪው ኢ-ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ማስወገድና በሌላ አዲስ ህገ መንግስት መተካት አለበት ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህ ህገ መንግስት የብሔረሰቦችን መብት ያስከበረ በመሆኑ እርሱን ለመቀየር መሞከር ሃገሪቱን ወደ መበታተን ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ የትኛውም ህገ መንግስት ከጅምሩ ሙሉ በኩለሄ ሆኖ የሚፈጠር ሳይሆን በየወቅቱ እየተሻሻለና እየበለፀገ የሚሄድ ህልው (organic) ሰነድ ነው። ከዚህ አኳያ፣ በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስት አውጥተን እንጣለው የሚለው አቋም እንደከዚህ ቀደሙ አፍርሶ ከዜሮ የመጀመር ቅኝት ያለው በመሆኑ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ሆኖ አይታይም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ምንም እንኳን አንዳንድ ጉድለቶችና ድክመቶች ያሉበት ቢሆንም፣ በርካታ ጠቃሚና አሻጋሪ የሆኑ የህግ አንቀጾችን ይዟል። በመሆኑም፣ የጊዜው ትኩረት መሆን ያለበት ባለው ህገ መንግስት ውስጥ ያሉትን ድክመቶችና ጉድለቶች ህዝብን አካታችና አሳታፊ በሆነ ሂደት እያሻሻሉ፣ ጠቃሚውን እያጠናከሩ መሄድ ነው።
አራተኛው፣ ፈተና፣ በስራ ላይ ካለው ህገ መንግስት ጋር በተያያዘ ሃገሪቱ ሊኖራት የሚገባው የፌደራል አወቃቀርን ይመለከታል። ባንድ በኩል፣ አሁን በስራ ላይ ያለው በብሔር ላይ የተመረኮዘ የፌደራል መዋቅር የሃገሪቱን አንድነት የሚፈታተንና  ወደ መበታተን የሚያመራ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ያለው የፌደራል አወቃቀር ለብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናጸፈ በመሆኑ፣ እርሱን ለመቀየር መሞከር ሀገሪቱን ወደ ብጥብጥና መበታተን ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። መልካሙ ነገር፣ ሁለቱም ወገኖች የፌደራል የመንግስት አደረጃጀት ብቸኛው አማራጭ መሆኑ ላይ ይስማማሉ። ከምህዳራዊው አስተሳሰብ አኳያ፣ የማንኛውም ፌደራላዊ ሥርዓት ውጤታማነት የሚለካው ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ሊኖረው የሚገባውን መሰረታዊ የመኖርና በአካልም በመንፈስም የመበልፀግ መብቶች ከቡድናዊ መብቶች ጋር አጣጥሞ መተግበር ሲችል ነው። በዚህ ረገድ፣ አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር ለብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር መሰረት የጣለ ቢሆንም፣ በህገ መንግስቱ ውስጥ የተነደገጉትን መሰረታዊ የሰው መብት ለሚጥስ አተገባበር እድል የሚሰጥ ሆኖ በመቀረጹ ለበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት ምንጭ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ ያንዳንድ ክልሎች አከላለል ውጤታማ የልማት አስተዳደርን ለመተግበር አመቺ አለመሆንም ይታያል። ስለዚህም፣ የተሻለው አማራጭ ያለው የፌደራል አወቃቀር ያሉበትን የአካታችነትና ልማታዊ ውጤታማነት ውሱንነት በሂደት በማሟላት ለዘለቄታው የሀገሪቱ ልማትና የህዝቦች ብልጽግና እንዲያገለግል ማድረግ ይሆናል።
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች አንዱ ከሌላው በእጅጉ የተሳሰሩ በመሆናቸው አንደኛውን በተናጠል ለመፍታት በመሞከር፣ ወደ ዘላቂ መፍትሔ ማምራት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ከላይ የተጠቀሰውን ያስተሳሰብ ሽግግር ለማሳካት የምህዳራዊ አስተሳሰብ ዋና ዋና መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ሶስት ምዕራፍ ባለው ትብብራዊ  የአስተሳሰብ (Collaborative thinking) ሂደት ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። የመጀመሪያው፣ በሀገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የሚነሱ የተለያዩ ሃሳቦችንና አቋሞችን ምንም ያህል የተቃረኑ (divergent) ቢመስሉም ከልብ ለመስማትና ለመደማመጥ የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠርና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ከዚህ በመቀጠል፣ ለተቃራኒ አመለካከቶች መነሻ የሆኑ ተጨባጭና ግምታዊ ስጋቶችን ለመረዳት መጣርና እነኚህንም ስጋቶች ሲቻል ለመፈወስ ይህም ባይቻል ድጋሚ እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ እይታ እንዲፈልቅ (emergence) ማድረግ ይሆናል። የመጨረሻው ደረጃ፣ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ሂደቶች በተፈጠረው መደማመጥና መተማመን ላይ ተመርኩዞ እንዲኖረን ለምንፈልገው የፖለቲካ ሥርዓት አስፈላጊ በሆኑ ዋና ዋና መዋቅራዊ መሰረቶች ላይ መግባባትን (convergence) መፍጠር ይሆናል።
ለማጠቃለል፣ በቀዳሚው ክፍል እንደተጠቀሰው፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን ነን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጠቃላይ የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር አካል ናቸው። ይህም ማለት፣ አንዱ ፓርቲ ከሌላው ፓርቲ ጋር የሚኖረው መስተጋብር ባጠቃላይ የምህዳሩን ጤናማነት ይወስነዋል።
በመሆኑም በማንኛውም ወቅት ለሚፈጠር የፖለቲካ ቀውስ፣ (የድርሻ ማነስ ወይም መብዛት ካልሆነ በስተቀር) የትኛውም ፓርቲ ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት አይችልም። ከዚህ አኳያ፣ ለህዝቦች መብትና ዘላቂ የልማት ፍላጎት ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ለህዝቦች ልዕልና ተገዢ በመሆን፤ ዋነኛ የሆኑት መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮችን እውቀት ላይ በተመረኮዘ አካሄድ በሂደት ሊፈቱ የሚችሉበትን ፍኖተ ካርታ (roadmap) ማዘጋጀት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የሃገራችን ወጣቶች ጊዜው ካለፈበት ባላባታዊ የፖለቲካ ቅሪቶች ራሳቸውን ነፃ አድርገውና ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የፈጠረላቸውን የዕውቀትና ቴክኖሎጂ አጋጣሚዎች በአስተውሎት በመጠቀም፣ የሃገሪቱንና የራሳቸውን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መጣር ይኖርባቸዋል። ለዚህም፣ ምህዳራዊ አስተሳሰብን እንደ ዋነኛ ያስተሳሰብ መመሪያ መጠቀም ከፍተኛ እገዛ ሊያደርግላቸው ይችላል። ይህ በሶስት ክፍል የቀረበ ጽሁፍ ለእንዲህ አይነቱ ሀገራዊ ሽግግር መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።
ከአዘጋጁ፡ ደስታ መብራቱ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ያስተምራሉ። ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

Read 3965 times