Wednesday, 05 August 2020 00:00

ሁዋዌ የአለማችን ቁጥር አንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ባለፉት 3 ወራት ሬኖ 8.58 ቢ. ዶላር፣ ሼል 18.3 ቢ. ዶላር ከስረዋል

             የቻይናው የሞባይል አምራች ኩባንያ ሁዋዌ ለረጅም አመታት በሳምሰንግ ተይዞ የነበረውን የአለማችን ቁጥር አንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ ክብር መንጠቁን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ካናሊስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከሰሞኑ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው አንዳለው ሁዋዌ እስካለፈው ሰኔ ወር በነበሩት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 55.8 ሚሊዮን ሞባይሎችን በመሸጥ ነው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለማቀፉ የስማርት ስልኮች ገበያ ድርሻ ቀዳሚነቱን የያዘው፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ በተጠቀሰው ጊዜ 53.7 ሚሊዮን ሞባይሎችን ብቻ በመሸጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለተኛነት ደረጃ ዝቅ ቢልም፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመላው አለም በርካታ ሰዎች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን ለመስራትና በርቀት ለመማር ከመገደዳቸው ጋር በተያያዘ ገቢውና ትርፉ እንደጨመረለት ኩባንያው አስታውቋል፡፡
ሳምሰንግ በዚህ አመት ያገኘው ትርፍ ካለፈው አመት ጋር ሲወዳደር በ23 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱንና አብዛኛውን ትርፍ ሊያገኝ የቻለው በኮምፒውተር መለዋወጫና የመረጃ ቋት ምርቶቹ ሽያጭ መሆኑንም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
በሌሎች የቢዝነስ ዜናዎች ደግሞ፣ ታዋቂው የፈረንሳይ የመኪና አምራች ኩባንያ ሬኖ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ መደብሮቹንና ፋብሪካዎችን ለሳምንታት ለመዝጋት መገደዱን ተከትሎ ሽያጩ ከ33 በመቶ በላይ ቅናሽ ማሳየቱንና በዚህም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ8.58 ቢሊዮን ዶላር የመንፈቅ አመት ኪሳራ እንዳጋጠመው ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡
ታዋቂው የነዳጅ ኩባንያ ሼል በበኩሉ የነዳጅና የዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ከማሽቆልቆሉ ጋር በተያያዘ ባለፉተት ሶስት ወራት ብቻ የ18.3 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠመው ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ያስነበበው ብሉምበርግ፣ ቶታል ኩባንያ በበኩሉ በተጠቀሰው ጊዜ የ126 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ማስመዝገቡን አመልክቷል፡፡

Read 6472 times