Print this page
Saturday, 01 August 2020 12:59

“ኮሮና በአለማችን ታሪክ እጅግ አደገኛው የጤና ቀውስ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ17.2 ሚሊዮን አልፏል


             የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለማችን ከዚህ ቀደም ከገጠሟትና በአደገኛነት ከተመዘገቡ የጤና ቀውሶች ሁሉ እጅግ የከፋው እንደሆነና ተባብሶ በቀጠለው በዚህ አደገኛ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ስድስት ሳምንታት በእጥፍ መጨመሩን ባስታወቁበት በዚህ ሳምንት፣ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ17 ሚሊዮን እንዳለፈ ተነግሯል፡፡
ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ17.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ671 ሺህ በላይ ሰዎችን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስነበበው ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ፣ በአለም ዙሪያ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም ከ10.7 ሚሊዮን ማለፉን አመልክቷል፡፡
ከቫይረሱ ተጠቂዎችም ሆነ ሟቾች ቁጥር ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት በዘለቀችው አሜሪካ ቫይረሱ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ4.57 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ የሟቾች ቁጥርም ወደ 154 ሺህ መቃረቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ብራዚል በ2.5 ሚሊዮን ተጠቂዎችና ከ90 ሺህ በላይ ሟቾች በሁለተኛነት ስትከተል፣ 1.59 ሚሊዮን ሰዎች የተጠቁባት ህንድ በተጠቂዎች ብዛት ሶስተኛ ደረጃን፣ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ሜክሲኮ ደግሞ በሟቾች ብዛት በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ተነግሯል፡፡
በአፍሪካ አህጉር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 900 ሺህ መቃረቡን የዘገበው አናዶሉ ኤጀንሲ፣ የሟቾች ቁጥር በበኩሉ ወደ 19 ሺህ መጠጋቱን አስነብቧል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በ7 ሺህ 500፣ ግብጽ በ4 ሺህ 800፣ አልጀሪያ በ1ሺህ 186 የኮሮና ቫይረስ ሟቾች በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት የተዳረጉባቸው ቀዳሚዎቹ ሶስት አገራት መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በ471 ሺህ፣ ግብጽ በ93 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ42 ሺህ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል ብሏል፡፡
ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በሚገኝባት አፍሪካ በቅርብ ጊዜያት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ፣ አገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር ምክንያት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁስቁስ እጥረት ለመቅረፍ ሊዘጋጁ እንደሚገባ መነገሩን አመልክቷል፡፡
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት ቀደም ብሎም እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ እጥረቱ መባባሱ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር በብዙዎች ዘንድ ስጋት መፍጠሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
የአለማችን ኢኮኖሚ ዕድገት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ጋር በተያያዘ በዘንድሮው አመት በታሪኩ ከፍተኛውን የ33 በመቶ ቅናሽ ማስመዝገቡን ፎርብስ መጽሄት የዘገበ ሲሆን፣ አለማቀፉ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በበኩሉ እስከ ግንቦት በነበሩት ያለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 320 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንዳጣ የተባበሩት መንግሥታት የአለም ቱሪዝም ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ድርጅቱ ከሰሞኑ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአለማችን የተለያዩ አገራት ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ ገደቦች በመጣላቸው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የጎብኚዎች ቁጥር በአለማቀፍ ደረጃ በ300 ሚሊዮን ያህል ቀንሷል፡፡
የአለማችን ባንኮች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ጋር በተያያዘ ለደንበኞች ከሰጡት ብድር እስከ 2021 አመት መጨረሻ ሊያገኙት የሚገባውን 2 ትሪሊዮን ዶላር ሊያጡ እንደሚችሉ መነገሩን ቢዝነስ ስታንዳርድ የዘገበ ሲሆን፤ የፎቶግራፍ ካሜራዎችን፣ ማተሚያ ማሽኖችንና ፊልሞችን በማምረት የሚታወቀው የአሜሪካው ታዋቂ ኩባንያ ኮዳክ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በማሰብ ከመደበኛ ስራው ውጭ መድሃኒት ወደ ማምረት መግባቱንም ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡



Read 3209 times
Administrator

Latest from Administrator