Saturday, 01 August 2020 12:37

ኢህአፓ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ታላቅ ሀገራዊ ድል መሆኑን የገለፀው ኢህአፓ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሁንም ለግድቡ ፍፃሜ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፤ “እንኳን ደስ ያለን፣ አባይ ከቤት ዋለ” በሚል በግድቡ ውሃ መያዝ የተሰማውን ደስታ ባስተላለፈበት መልዕክቱ፤ የግብጽን የዘመናት ሴራና የዲፕሎማሲ ብልጠት ባመከነ መልኩ ግድቡ ውሃ እንዲይዝ መደረጉ የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው ብሏል፡፡
ሀገሪቱ ግድቡን እውን እንዳታደርግ በየአቅጣጫው የነበረውን ዘመቻ በመቋቋም ከእለት ጉርሱ እየቀነሰ ገንዘቡን በማዋጣትና ቦንድ በመግዛት “አባይ የኔ ነው” ብሎ በቆራጥነት እየተሳተፈ ለሚገኘውም የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናውን አቅርቧል - ኢህአፓ፡፡
ኢህአፓ በቀጣይም  ከህዝቡ ጋር በመሆን የግድቡ ስራ እንዲጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ጠቁሞ ህዝብም ያለምንም መታከት ለግድቡ መጠናቀቅ ሙሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል፡፡
የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በጥንካሬ እየተደራደሩ ለሚገኙ ባለሙያዎች አድናቆቱን የገለፀው ፓርቲው፤ በአንፃሩ የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት ሽር ጉድ የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ መክሯል - እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን አጥብቆ እንደሚታገላቸውም በማሳሰብ፡፡


Read 11242 times