Saturday, 01 August 2020 12:02

ሃገሪቱን ከቀውስ አዙሪት ሊያወጣ የሚችለው የፖለቲካ ውይይት ብቻ ነው - ኤዴፓ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ሃገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት የእምነት አባቶች ፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ፣ምክንያታዊ አክቲቪስቶችና የዲፕሎማሲ ተቋማት፤ መንግስት ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚገኝበት የውይይት መድረክ እንዲያመቻች ተፅዕኖ ይፈጥሩ ዘንድ ኢዴፓ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የፓርቲውን መስራችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌውን እስር በተቃወመበት መግለጫው፤ ለሃገሪቱ ከቀውስ መውጫ ሁነኛ የፖለቲካ መፍትሄ የሚገኝበት፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት ማካሄድ ነው ባሏል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ ከተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦች ማግስት፣ አቶ ልደቱን  ጨምሮ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችን ኢላማ ያደረገ እስራት ተፈፅሟል ያለው ፓርቲው፤ ከሁከትና ብጥብጥ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የሃሳብ ሰዎች ማሰር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ባሏል፡፡
ሃገሪቱ አሁን ከገባችበት የቀውስ አዙሪት መውጣት የምትችለውም በውይይት ወደ መዋቅራዊ ሽግግር ስታመራ መሆኑን የገለፀው ኢዴፓ፤ ለዚህ አይነቱ መድረክ መንግስት ቀና ምላሽ እንዲሰጥ ኢዴፓ ጠይቋል፡፡ መንግስት ሃገሪቱን ወደነበረችበት የአፈና መንገድ ሊመለስ የሚችለው የጭፍን እርምጃ ትቶ በለውጡ መባቻ ላይ ለህዝቡና ለፖለቲካ ሃይሎች ቃል ገብቶ የነበረውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ማስከበር አለበት ብሏል - ፓርቲው፡፡
የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን፣ ባለፉት 27 ዓመታት ከተለመደው በጭፍን የመደገፍና በጭፍን የመቃወም  ባህሪ ተላቀው፣ ሞያዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል - ኢዴፓ፡፡

Read 1111 times