Monday, 27 July 2020 00:00

የፖለቲካዊ ህመሞች ፈውስ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(4 votes)

 (ክፍል ሁለት፡ የምህዳራዊ አስተሳሰብ ዓበይት መርሆዎች )
                       
               በሃያኛው ክፍለ ዘመን የታየው እጅግ ፈጣን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ እድገት በቢሊዮን ለሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች ከድህነት መላቀቅ መሰረት መሆኑ እሙን ነው። በሌላ በኩል ግን ይኸው እድገት ለበርካታ ውስብስብ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች መነሻም ሊሆን ችሏል። ይህም፣ አብዛኛውን የአለማችንን ህዝብ ወደ ከፋ ድህነት ከመግፋት አንስቶ ለዓለማችን ከፍተኛ ስጋት እስከሆነው የምድራችን ሙቀት መጨመርን ያካትታል። እነኚህን ፈተናዎች በልዩ ልዩ የሳይንስ መስኮች በተደረጉ ምርምሮች ለመረዳትና ለመፍታት ጥረት ቢደረግም፣ ችግሮቹ ይበልጥ እየተባባሱና እየተወሳሰቡ ከመሄድ ሊገቱ አልቻሉም። ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) እንዲህ አይነት ውስብስብ ችግሮችን በአግባቡ ለመረዳትና መፍትሄ ለመሻት ከ1960ዎቹ ጀምሮ እየዳበረ የመጣ የልዕለ ዘርፍ (transdisciplinary) ሳይንስ ነው።  በክፍል አንድ ጽሁፌ፣ ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ የሃገራችንን የፖለቲካ ህመሞች በአግባቡ ለመረዳት የሚኖረውን አስተዋጽኦ በመግለጽ፣ በዚሁ እይታ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ዋነኛ የፖለቲካ ህመሞቻችንን ለማመላከት ተሞክሯል።
 በዚህ ጽሁፍ፤ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች መካከል ለሃገራችን የፖለቲካ ህመሞች ፈውስ ለማግኘት ይረዳሉ ከሚባሉት አበይቶቹን እንዳስሳለን። እነኚህ መርሆዎች በማንኛውም የተፈጥሮ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምህዳሮች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ መሰረታዊ መርሆዎች በመሆናቸው አንባቢዎች በግልም ሆነ በሙያ ህይወታቸው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።
የመጀመሪያው መርህ፡- በክፋይነት እና ምሉእነት መካከል ያለውን መስተጋብር ይመለከታል። በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ ማንኛውም ምህዳር በአንድ ተመሳሳይ ወቅት በራሱ ምሉእና የሌላ ከፍ ያለ ምህዳር ደግሞ ክፋይ አካል ነው። በዚህ መሰረት ክፋዮች የማንኛውም ምሉእነት መሰረቶች ሲሆኑ እነኚህ ምሉዕነቶች ግን ከክፋዮቹ ተደማሪነት በላይ የሆነ ልዕልና ይኖራቸዋል። በተጨማሪም፣ በአንድ ምህዳር ውስጥ በሚኖሩ ክፋዮች መካከል የሚኖረው የማያቋርጥ መስተጋብር፣ በአጠቃላይ በምሉዕ ውስጥ ለሚኖረው መሰረታዊ ለውጥ ዋነኛው ምንጭ ስለሆነ  በክፋዮቹ መካከል ያለውን መስተጋብር በጥልቀት መረዳት ምሉዕ ምህዳሩን በአግባቡ ለመረዳትና ለመምራት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ ቤተስብ ውስጥ ያሉ አባላት እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻሉ ምሉእ ሰው ሲሆኑ፣ ቤተሰብ የተባለው ከፍ ያለ ምሉእ ምህዳር ደግሞ ክፋይ ናቸው። ነገር ግን፣ ቤተሰብ በደፈናው የሰዎች ስብስብ ሳይሆን በያንዳንዱ የቤተሰብ አባል መካከል በሚኖረው መስተጋብርና መተሳሰር የሚገለጽ ምህዳር ነው።  ስለሆነም አንድን ቤተሰብ በአግባቡ ለማስተዳደር እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል እንደ ምሉእ ሰውነቱ መረዳትና በሁሉም የቤተሰብ አባላት መካከል የሚኖረውን መስተጋብር በአግባቡ መገንዘብና መያዝ ይጠይቃል። በተመሳሳይ፣ ቤተሰቦች ወደ ማህበረሰብ፣ ማህበረሰቦች ወደ ብሔረሰብ፣ ብሔረሰቦች ደግሞ ከሁሉም ከፍ ያለ ልዕልና ወዳለው ሃገረሰብ ያድጋሉ ማለት ነው። በክፋይነትና ምሉዕነት መርህ መሰረት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ብሔረሰቦች ሃገር ውስጥ አካታችና ውጤታማ የሆነ ሥርዓተ መንግስት ለመገንባት፣ የእያንዳንዱን ብሔረሰብ ምሉእነት ከሀገራዊው ልዕልና ጋር የሚያጣጥም የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት የግድ ይሆናል።
ሁለተኛው መርህ፡- በምህዳራዊ መስተጋብር እና በእውነት መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለከታል። በዚህ መርህ መሰረት፣ ሁሉም ምህዳሮች ቀጣይ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ስለሆኑ በአንድ ጊዜ በበርካታ እውነቶች ሊገለጹ ይችላሉ።  ይህም ማለት፣ ሁሉም እውነቶች አንጻራዊ ስለሆኑ አንድ እውነታ (reality) ከአንድ በላይ በሆኑ (multivalent) እውነቶች ሊገለጽ ይችላል። በዚህም የተነሳ፣ አብዛኛው ገሃዱ ዓለም በግራጫው ማእቀፍ (grey-zone) ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ጥቁር ወይም ነጭ እውነታ ቅጽበታዊ የሽግግር ሁነት (Transient state) መገለጫ ብቻ ነው። በሳይንሱ ዐለምም ያለው እውነት በአብዛኛው አንጻራዊ ሲሆን፣ ፍጹም እውነት የሚገኘው በሂሳባዊው ቀመር (mathematical models) ውስጥ ብቻ ነው። የሃገራችን ፖለቲካ አንዱ ልዩ መገለጫ፣ አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ሌላው ወገን አለኝ የሚለውን እውነት ለማዳመጥ ዝግጁ አለመሆን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ‘እውነት’ በሌላው ላይ በጉልበት ለመጫን የሚሄዱበት ርቀትም ነው። ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ ብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን በከፍተኛ ደረጃ ክተጠናወታቸው ‘የእኔ ብቻ ነው እውነት’ ከሚለው አመለካከት ተላቀው የሌላውንም ወገን ‘እውነት’ ለመስማት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።  ይህንንም በማድረግ፣ አንድን ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ በመመልከትና በመረዳት ለእውነታው በይበልጥ የሚቀርብ መግባቢያ ሃሳብ ላይ መድረስ ይቻላል።
ሶስተኛው መርህ፡- በብዝሃነት እና ምህዳራዊ መረጋጋት (stability) መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለከታል። በዚህ መርህ መሰረት፣ ብዝሀነት የማንኛውም ምህዳር የመረጋጋትና የዘላቂነት ዋነኛ መነሻ ምንጭ ነው። ይህም ማለት፣ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ የሚኖረው ብዝሃነት ወደ ተሻለ ስርዐት ለመሻገር የሚያስችል መወራረስና መዳቀል ከማሳለጡም በላይ ምህዳራዊ መረጋጋትንና ሚዛናዊነትን ለማረጋጋጥ ያግዛል። ከዚህ በተቃራኒው፣ በአንድ ወጥነት (Monocultural) ላይ የተመረኮዘ ምህዳር ለመውደቅ (crash) እና ከዚህም ከከፋ ለመጥፋት (extinction) አደጋ የተጋለጠ ይሆናል። ከዚህ አኳያ፣ በሃገራችን የሚገኘው የስነምህዳር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ብዝሃነት ለሃገሪቱ ቀጣይና ዘላቂ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሰረት ሊሆን እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ግን ሊሆን የሚችለው የነኚህን ብዝሃነት ጠቀሜታ ባግባቡ ተረድቶ የእርስ በርስ ተደጋጋፊነታቸውንና ተወራራሽነታቸውን በሚያጠናክር ህገ መንግስታዊ ስርዓት ሲደገፉ ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው፣ በአሃዳዊነት ወይንም  አሁን ባንዳንድ የክልል ፖለቲካ አራማጆች እንደሚታየው ‘ራስን በራስ ማስተዳደር’ በሚል ሽፋን ‘አንድ ወጥነትን’ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት፣ ያንኑ ማህበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳውና ከከፋም ሊያጠፋው እንድሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።     
አራተኛው መርህ፡-  በትብብር እና ፉክክር መካከል ስላለው ግንኙነት ይሆናል። በዚህ መርህ መሰረት፣ የማንኛውም ምህዳር ውጤታማነትና ዘላቂነት የሚወሰነው በክፋዮቹ መካከል ለሚኖረው ትብብርና ፉክክር በሚኖረው አያያዝ ውጤታማነት ይሆናል። በክፋዮቹ አካላት መካከል የሚኖረው ትብብር የምህዳሩን አሰራር ውጤታማነትና መረጋጋት (efficiency and stability) የሚወስን መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን በነኚሁ ክፋዮች መካከል የሚኖረው ፉክክርና ውድድር ደግሞ ለምህዳሩ ቀጣይ እድገት አስፈላጊ ለሆነው ፈጠራ (innovation) ዋነኛ መሰረት ነው። በዚህ መሰረት፣ በአንድ ሃገር ውስጥ የሚኖረው የፖለቲካ ምህዳር ጤናማነት የሚወሰነው በፓርቲዎች መካከል ሊኖር በሚገባው የመተባበሪያ ማእቀፍ ጥንካሬና በመወዳደሪያ ሜዳው አካታችነት ይሆናል። የአንድ ሃገር ህገመንግስት የፓርቲዎችን የመተባበሪያ ማዕቀፍ የሚወስን ዋነኛ መሰረት ሲሆን በማናቸውም ሁኔታ ዘላለማዊ ምሉዕነት ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም በሁሉም ወገኖች ተሳትፎና ቅቡልነት ባለው አካሄድ በቀጣይነት መዳበር ይኖርበታል። ይህንን ሂደት በመወዳደሪያነት ለህዝብ ድምጽ መቅረብ ከሚገባቸው የፓርቲ ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች መለየትም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምስቅልቅል አንደኛው ምንጭ ይህንን ሃገራዊ የመተባበሪያ ማዕቀፍ ከፓርቲዎች የመወዳደርያ ፕሮግራም ጋር ከማደበላለቅ የሚመነጭ ነው።
ዐምስተኛው መርህ፡- በመዘርዝራዊ (detailed) እና በመስተጋብራዊ (dynamic) ውስብስብነት መካከል ያለውን ግንኙነትና ልዩነት መረዳትን ይመለከታል። በዚህ መርህ መሰረት፣ አንድን ውስብስብ ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ ለመምራት ያለ ብቃት የሚወሰነው መስተጋብራዊ ውስብስብነቱ ላይ ባለን ምሉዕ አረዳድ ይሆናል። ይህም ማለት፣ ለአንድ ውስብስብ ሁኔታ ሁለንተናዊ መፍትሔ ለማግኘት ከተናጠል ሁነቶች (events) እና ድግግሞሽ (patterns) ባሻገር በመመልከት መዋቅራዊ ምንጮችን በጥልቀት መመርመርና መፍታት የግድ ይላል። በተናጠል ሁነቶች ላይ ተመርኩዞ ሃገራዊ መፍትሔ ለመሻት የሚደረጉ ጥረቶች መውጫ ወደሌለው መዘርዝራዊ ውስብስብነት ይከታል። ከዚህ ይልቅ፣ የአመለካከትና መዋቅራዊ ችግሮችን በመመርመር በርካታ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ልዩ ቋጠሮዎችን (dynamic knots) መፍታት ይቻላል። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ አንድን ውስብስብ ሁኔታ ለመፍታት ካንድ በላይ የመፍትሔ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል። እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የሚጠቆሙ መፍትሄዎች በአብዛኛው ወይ በአንድ ክፍል ወገናዊነት ላይ የተመረኮዙ ምሉዕነት የጎደላቸው ይሆናሉ ወይም ሁሉንም ዝርዝር ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት መያዣ መጨበጫው የጠፋበት የመፍትሄ ሃሳብ ሆነው ይገኛሉ።
ስድስተኛው መርህ፡- ተመክሮአዊ መማማር (adaptive learning) ለአንድ ምህዳር ቀጣይነት ያለውን ወሳኝነት ይመለከታል። በዚህ መርህ መሰረት፣ ውጤታማ ተመክሮአዊ የመማማር ስርአት ያለው ምህዳር ያልተቋረጠና ቀጣይነት ያለው ሽግግር ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል። ይህም ማለት፣ ጠቃሚ መረጃዎችን በስርዓት የሚያደራጅ፣ የሚያጠራቅምና ካንድ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ የሚያሸጋግር ምህዳር ላልተቋረጠና ቀጣይ ለሆነ ሽግግር ጥሩ መሰረት ይኖረዋል።
በዚህ ረገድ፣ ሃገር በቀል የእውቀት ስርአቶች በትውልድ የዳበሩ ጠቃሚ መረጃዎች በማከማቸትና ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። እንዳለመታደል ሆኖ፣ የዘመናዊ ፖለቲካ ታሪካችን የነበረውን ከመሰረቱ አፍርሶ እንደ አዲስ የመጀመር በሽታ የተጠናወተው ነው። በክፍል አንድ ጽሁፍ እንደተጠቀሰው፣ የሃገራችን የፖለቲካ ባህል ሃገር በቀል እውቀቶችንም ሆነ ጠቃሚ የፖለቲካ ተመክሮዎችን ባግባቡ አደራጅቶ በመጠቀምም ሆነ ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፉ ረገድ ከፍተኛ ድክመት ያለበት ነው። ይህንን ችግር ለማስወገድ፣ አንጋፋ ፖለቲከኞቻችን ካለፈው ትውልድ በጎም ሆነ ክፉ ተመክሮዎች ልንማር የሚገባንን በቅንነት በማስተማር፤ ወጣት የፖለቲካ መሪዎቻችንም በበጎው ተመክሮ ላይ ለመገንባትና ጎጂ ታሪካችንን ላለመድገም ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ስድስት መርሆዎች በተቀናጀ መልኩ ከተተገበሩ፣ በክፍል አንድ የተጠቀሱትን መሰረታዊ የፖለቲካ ህመሞቻችንን በማከም፣ የወደፊቱን የሃገራችንን የፖለቲካ ምህዳር በጤናማ መሰረት ላይ ለመገንባት ያግዛሉ ተብሎ ይታመናል።  
በቀጣዩ ክፍል ሦስት ጽሁፍ፣ እስካሁን በቀረቡት የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች ላይ በመመርኮዝ፣ በሃገሪቱ ዋና ዋና መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ተቃራኒ አቋሞችን እንመለከታለን።     
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ያስተምራሉ። በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

Read 8848 times