Saturday, 25 July 2020 15:03

“ከእንግዲህ ግድቡን የሚያቆመው ሃይል የለም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

የውሃ ሙሌቱ አሜሪካን አስቆጥቷል

            የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን መንግስት ማስታወቁን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ደስታቸውን እየገለፁ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአሜሪካ መንግስት  ግድቡ ከስምምነት ውጪ እየተሞላ ነው በሚል ለኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ለማቆም ማሠቡን አስታውቋል።
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን የሚያበስር የደስታ መግለጫ ለመላው ኢትዮጵያውያን ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ ሰዎች በውሃው ሙሌት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል። የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እንደ አድዋ ድል የሚታይ ነው ብለዋል - አስተያየት ሰጪዎች።
የኤርትራ መንግስት ድጋፍ አለው የሚባለው “ኤርትሪያን ፕሬስ” ባስተላለፈው መልዕክት ለመላ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት በመጀመሩ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እኛም ደስ ብሎናል” ብሏል።
“ዛሬ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እጅግ ታሪካዊ ቀን ነው” ሲሉ የደስታ መልዕክታቸውን ያበሰሩት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፤ “ይህ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ጠብቋል፤ ሃላፊነቱንም እየተወጣ ነው፣ የሚጠራጠር ካለ ዛሬ ምላሹን አግኝቷል፤ ተፈጥሮም እንኳ ምስክርነቷን ሰጥታለች” ብለዋል።
ግድቡን ከእንግዲህ ወደ ኋላ የሚመልሰው ነገር እንደሌለ የገለፁት ፕሬዚዳንቷ አሁንም ዜጐች ሃገሪቱን ወደፊት በማሻገር በኩል በርካታ የቤት ስራዎች እንዳሉባቸው ጠቅሰው፤ አንድነታቸውን በማስተባበርና አቅማቸውን በማጐልበት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “አባይ ወንዝ ነበር፤ ተገርቶ ወንዝም ሃይቅም ሆነ” ሲሉ ደስታቸውን ገልፀዋል።
“አባይ ከእንግዲህ በወንዝነቱ ይፈሳል፣ በሃይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለመዋል እጅ ሰጥቷል” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ደስታው የመላው ኢትዮጵያውያን ነው ብለዋል፡፡  
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ “ግድቡ በአጭር ጊዜ እንዲሞላ ተፈጥሮም ከእኛ ጋር ሆናለች” ብለዋል - በደስታ መግለጫቸው።
የውሃ ኢነርጂና መስኖ ሚኒስትሩ ኢ/ር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ መሞላቱ ትልቅ መሠረት ነው… ከእንግዲህ የግድቡን ግንባታ ወደ ኋላ የሚመለሰው ነገር የለም” ብለዋል።
ግድቡ እስከ ቀጣዩ መጋቢት ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሁለት ተርባይኖች አማካይነት የመጀመሪያ የሙከራ ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ጠቁመዋል - በትዊተራቸው።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ መያዝ ከመነገሩ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ተደራዳሪዎች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ፍሬያማ የተባለ ድርድር ማካሄዳቸው ተመልክቷል።
ሀገራቱ በግድቡ የውሃ አሞላል ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል ቢባልም ቅሉ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ግድቡ ሰሞኑን የውሃ ሙሌት መጀመሩን የሚያበስረውን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማሮጣ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ አሁንም በግድቡ የውሃ አሞላል ላይ ስምምነት ያስፈልጋል ማለታቸውን የጠቀሰው “አህራም” የግብጽ ጋዜጣ፤ ግድቡ ከስምምነት ውጪ ውሃ ተሞልቷል ሲል ዘግቧል፡፡  
ግብፃዊው ታዋቂ ቢሊየነር ናጅቢ ሳውረስ በበኩላቸው፤ “ይሄን ከማይ ጦርነትን እመርጣለሁ” ሲሉ ብስጭት የሚያንፀባርቅ አስተያየታቸውን መግለፃቸውን አፍሪካን ሪፖርት ዘግቦታል።
“በር በላያችን ላይ የተዘጋ ያህል ነው የምቆጥረው ሲሉም” ብስጭታቸውን ገልፀዋል ቢሊየነሩ።
በአደራዳሪነት ብቅ ብሎ የነበረው የአሜሪካው የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ግድቡ ከስምምነት በፊት ውሃ መሞላቱ አግባብ አይደለም፤ ይህ ድርጊት በመፈፀሙ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለማቆም እያሰበች መሆኗን ከባለስልጣናት ሰምቻለሁ ሲል “ፎርየን ፖሊሲ” የተሰኘው መጽሔት ጽፏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በጉዳዩ ዙሪያ ትናንት በሰጠው መግለጫ የአሜሪካ መንግስት ይህን ስለማሰቡ በኢትዮጵያ መንግስት ደረጃ የሚታወቅ ነገር የለም ብሏል፡፡
የህዳሴ ግድብ በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የተጀመረ ሲሆን፤ የግድቡን ፕሮጀክት ከጅምሩ አንስቶ ለ6 ዓመታት በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19/2010 ዓ.ም በድንገት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።


Read 12981 times