Saturday, 25 July 2020 14:52

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  - በኦሮሚያ የተከሰተው ሁከት ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል
              - በግብር መክፈያ ቦታዎች የሚታየው መጨናነቅ ስርጭቱን እንዲያባብሰው ተሰግቷል
              - በሁለት ቀን ብቻ ከ1ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል
                    
           የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በተለይ ባለፈው ሳምንት በሁለት ቀናት ብቻ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚ/ር መረጃ ያረጋግጣል። ባለፈው እሮብና ሐሙስ ብቻ 1080 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋነው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ነው፤ ለዚህም አራት ምክንያቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ወልደሰንበት፤ ቀዳሚው ጉዳይ ህብረተሰቡ በበሽታው መከላከል ላይ ሲያደርግ የነበረውን ጥንቃቄ ቸል እያለ መሄዱና የመገናኛ ብዙሃንም የሚሰሩትን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደ ቀድሞው ባለመቀጠላቸው ነው ብለዋል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ህብረተሰቡ ሀዘኑንና ቁጣውን ለመግለጽ ያለምንም ጥንቃቄ ሰልፍ መውጣቱ እንዲሁም በዚህ ሽፋን ሌሎች ነውጠኛ ቡድኖች ጥፋትና ውድመት ለመፈፀም ተሰባስበው መውጣታቸው ለቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት አስተዋፅኦ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለው የአየር ፀባይ ለበሽታው መባባስ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በተለምዶ 24 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ነዋሪዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ መንደሩ ከእንቅስቃሴ መታገዱንም አመልክተዋል።
ሰሞኑን የግብር መክፈያ ወቅት እንደመሆኑ ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠር የገቢዎች ደንበኞች የግብር መክፈያ ሥፍራዎችን አጨናንቀው እንደሚገኙና ህብረተሰቡ ወደ ግብር መክፈያ ተቋማት ሲገባ እጁን በውሃ ታጥቦ ከመግባትና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጐ ከመግባት ውጪ ርቀትን በመጠበቅ ላይ አለመሆኑን አመልክተዋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ምንም አይነት እርምጃ ሲወሰድ ለማየት አልቻልንም።
በቦሌ ክፍለከተማ የወረዳ 4 ግብር መክፈያ ሥፍራ እንዲሁም በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 4 ግብር መክፈያ ስፍራዎች ተገኝተን ለማየት እንደቻልነው ህብረተሰቡ ለቀናት እየተመላለሰ በከፍተኛ ሁኔታ በተጨናነቀ ሥፍራ ላይ መቆየቱ ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ስጋት እንዳለም ለማወቅ ተችሏል።    
የገቢዎች ሚኒስትር ህዝብ ግንኙነት ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው ሚኒስትር መ/ቤቱ በዚህ የግብር መክፈያ ወቅት ላይ ይህንኑ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ለመቀነስ እያከናወነ ያለው ተግባር አለመኖሩን ጠቁመው፤ በመጪው ሰኞ አጠቃላይ መግለጫ ይሰጣል ብለዋል፡፡



Read 743 times