Wednesday, 22 July 2020 00:00

የድሮው አይበቃን፣ ለዘመኑም አልበቃን!

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)

    "ተዓምረኛ የስልጣኔ ውጤቶች ግን፣ ከእጃችን ውስጥ ገብተው፣ መጫወቻችን ሆነዋል። የውሸትና የአሉባልታ፣ የስድብና የብሽሽቅ፣ የጥላቻና የጥፋት ዘመቻ ማሳለጫ አድርገናቸዋል። በዱላና በጦር ሲገዳደሉ የነበሩ ነውጠኞች፣ ክላሽና ቦምብ ሲታጠቁ እንደማለት ነው። አገሬው በእሳት ለኳሹ፣ እንደተጥለቀለቀ ቁጠሩት፡፡"
           

          እናትና አባት፣ እንደቀድሞው ለልጆቻቸው ነባር አኗኗርን ያላምዳሉ። ከትውልድ ትውልድ፣ ብዙም የሚጨምር የሚቀንስ ነገር የለም። “ያና ያ ድንጋይ፣ ይሄና ይሄ እንጨት፣… ያኛውና ያኛው አፈር፣ ይሄኛውና ይሄኛው ውሃ”፣… እያሉ፣ የሚታይ የሚዳሰሰውን ዓለም ለልጆች ያስተምራሉ፣ ይነግራሉ፤ ያስጠናሉ።
መራመድና መሮጥ፣ እቃ ማምጣትና መውሰድ፣ መልዕክት መናገርና መስማትን ለልጆቻቸው ያለማምዳሉ። ማረስና መዝራት፣ ወፍ ማባረርና ፍሬ መልቀም፣ ማጨድና መውቃት፣ መፍጨትና መጋገርንም ያስተምራሉ። ከብት ማሰማራትና ውሃ መቅዳት፣ በረት ማጽዳትና፣ ወተት ማለብን ያሳያሉ። ጨዋነትንና ቁምነገርን፣ አክብሮትንና ቁጥብነትን ብቻ ሳይሆን፣ ጉዳትና ጥቃትን፣ ነውርና ውርደትን፣ ጥፋትና ወንጀልንም፣ ምንና ምን እንደሆኑ ለልጆቻቸው በየአጋጣሚው ይነግራሉ፤ የመጣላቸውን ያህል ይመክራሉ። ከእከሌ ጋር እንጂ ከእገሌ ጋር አትግጠም፤ እከሌ ጋ አትድረስ። እንቶኔን አታስጠጋ፤ ለዚያኛው ፊት አታሳይ በማለት ልጆቻቸውን ያስጠነቅቃሉ። የወላጆች ስራ መንገርና ማስጠንቀቅ ብቻ አይደለም። ቁጥጥርና ቅጣት አለ። የተነገረውን ካልሰማ፣ የተከለከለውን ካለፈ፣ ውሎ ሳያድር፣ ወሬው ወላጆች ጋ ይደርሳል፤ ዘመድ ጐረቤት ይሰማል። በድሮው የጥንት አኗኗር ውስጥ፣ ማምለጫ የለም። ሁሉም ነዋሪ፣ ሁሉንም ነዋሪ ያውቃል። በድብቅ ካልሆነ በቀር፣ ከነውርና ከውርደት መራቅ የግድ ነው - የወላጆችን ቅጣት በመፍራት፣ እንዲሁም በይሉኝታና፣ በልማድ።
በእርግጥ የድሮው የገጠር አኗኗር በርቀት ነው። ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ፣ አስር ሄክታር አንድ ሺ ነዋሪዎችን ሊይዝ ይችላል። በጥንቱ የገጠር አኗኗር ግን፣ አስር ሄክታር ለ5 ቤተሰብ አይበቃም። ታዲያ፣ አኗኗራቸው በርቀት ቢሆንም በቁጥር ጥቂት ናቸውና፣ ማን ማን እንደሆነ ሁሉም ይተዋወቃሉ። ልጆች ከወላጆች ቁጥጥር ከዘመድ ጐረቤት አይን፣ ከመንደር ወሬና ከሰፈር ጆሮ አያመልጡም። ከተለመደ ጨዋነትና ልማዳዊ ስርዓት ማፈንገጥ ከባድ ነው። ቅጣትና ይሉኝታ ብቻ አይደለም - ልጓሞቹ።
ነገርና ግጭት፣ ወደለየለት ፀብ ካመራ፣ ለቂምና ለበቀል እንደሚዳርግ፣ ሁሉም ሰዎች በቀጥታ በተግባር ያያሉ። እናም፤ አንደበታቸው የተቆጠበና  እርምጃቸውም እንደየ ሁኔታው የተመጠነ እንዲሆን መጠንቀቅ ይለምዳሉ። በአጭሩ፣ የጥንቱ አኗኗር፣ ከልማዳዊው አስተዳደግ የተለየ ትምህርት ቤት፣ የቴክኒክ ስልጠናም ሆነ ዩኒቨርስቲ አያስፈልገውም። በትውልድ የወረሱትን የድሮ አኗኗር፣ በተራቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ያስተምራሉ።
በየእለቱ፣ በየዓመቱ ብዙም የተለየ ነገር አይከሰትም። በአንድ በኩል፣ ሕይወት በሰፈር የታጠረና ወንዝ የማይሻገር ስለሆነ፣ በሌላ በኩልም፣ እያንዳንዱ ወሬ ከሰው ሰው ለመዳረስ ብዙ ጊዜ ስለማይፈጅበት፤ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ሞባይልና ኢንተርኔት ባይኖር፣ ችግር የለውም።
በወር አንዴ በእግር ገበያ ወርዶ፣ ትንሽ ሸጦ፣ ትንሽ ገዝቶ ወደ ቀዬው ከተመለሰ በቂው ነው። መንገድ ተዘጋ፣ ነዳጅ ጠፋ ብሎ አይጨነቅም። ከማያውቀው ሰው ጋር ብዙም አይገናኝም። በቀየው በመንደሩ፣ ከማን ጋር ምን አይነት ግንኙነት እንደሚኖረው ይታወቃል።
አንዱ የሌለውን ባህርይና ልክ እየመዘነ፣ ቅርበትና ርቀቱን ይጠብቃል። ለቁጥጥርና ለይሉኝታ፣ የሰዎች ዝምድናና ጉርብትና ጥብቅ ነው። ነገር ግን፣ ዝምድናና ጉርብትና፣ የጋራ ማሳና የጋራ ጐተራ ማለት ስላልሆነ፣ ነገር ካልፈለገ በቀር፣ አጥር አይጥስም፤ ወሰኑን አያልፍም። “ቤት ለእንግዳ፣ ቡና ይፈላ፣ ቁርስ ይምጣ፣” ብለው ይጋብዙታል በጨዋ ደንብ። እንግዳውም በጨዋ ደንብ ይግደረደራል፤… “ልሂድ፣ አሁን ጠጣሁ፣ ስወጣ በላሁ” ይላል። አለበለዚያ፣ ትዝብት ላይ ይወድቃል። ይሉኝታ ቢስ፣ ቀለዋጭ የሚል ሃሜት ያተርፋል። እንግዳ ተቀባይነት ወግ ነው - አለበዚያ ንፉግ ይሉታል። መግደርደርም ወግ ነው፤ አልፎ ቀላዋጭ ይሉታል። “ይሉኝታ” እንዲሉ። ገመናውን ይጠብቃል።
ይሉኝታው፣ መተዋወቁና መለካካቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሃሜትና ውሸት፣ አሽሙርና ስድብ፣ ፉከራና ፀብ አይኖርም ማለት አይደለም። ግን፣ ከልኩ አያልፍም።
ውሸት ስለተወራ፣ ሃሜት ስለበዛ፣ በዚህ የተነሳ፣ ቀየውና መንደሩ ይበጠበጣል ማለት አይደለም። ቢበጠበጥም እንኳ፣ ወንዝ አይሻገርም። ምንም ቢከፋ፣ የሁለት የሦስት ሰው ፀብ ነው። ከባሰም፣ የአንድ የሁለት ዘመድ በቀልና አፀፋ ይጨመርበታል። ለዚያውም፣ ከሽምግልና ካለፈ፣ ከሰፈሩ የማሃይማኖት መሪም እርቅ ካልተገኘ ነው። ግልፈተኛው ሰውዬ ወንጀል ሰርቶ፣ እልኸኛው ዘመድ በቀል ፈጽሞ፣ ወይ ከአካባቢው ይሰወራል። ወይ ይታሰራል። አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ካልሆነ በቀር፣ መንግስትና ባለስልጣን፣ ከአብዛኛው የድሮ ሰው ኑሮ ጋር ብዙም ቅርበት የላቸውም። ለኑሮ ሩቅ ናቸው። በሰላም ጊዜ፣ ለአብዛኛው ሰው፣ መንግስት የእለት ተእለት ፈተና አይሆንባቸውም። የሚፈታተኑትም አይደለም።  
እነሱም አይደርሱበትም።
በየቀያቸው፣ ጥቃቅን ባለስልጣናትን መውደድና መጥላት ይችላሉ። በስንት ዓመት አንዴ፣ ለአመጽ ይነሳሱም ይሆናል። ግን፣ አስፈሪ የዓመጽ ማዕበል አይፈጠሩም፤ ከስኒ ከኩባያ ማዕበልነት አያልፉም።
ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባልተስፋፋበት ሞባይልና ኢንተርኔት፣ ፌስቡክና ዩቱብ ባልነበረበት የድሮ ዘመን፣ የዓመጽ ፕሮፖጋንዳ፣ ከስኒ ገንፍሎ፣ አገር ምድሩን አያደርስም፤ መንግስትን አይነቀንቅም። ግን ደግሞ፣ የመንግስት ፕሮፓጋንዳም፣ በየገጠሩ ጓዳ አይደርስም - በድሮው ኑሮ። በዚያው ልክ፣ የመንግስት ጦርና ፖሊስ፣ ሌሊቱን በሄሊኮፕተርና በፈጣን መንገድ ገስግሶ፣ ጥዋት ከደርዘን በላይ ከተሞችን የመቆጣጠር፣ በየገጠሩ የመሰማራት፣ በአንድ ቀን በሺ በ10ሺ የሚቆጠሩ ነውጠኞችን ወይም ተቃዋሚዎችን አፋፍሶ የማሰር አቅም፣ በድሮ ጊዜ አልነበረም። ግን መንግስት ደክሟል ማለት አይደለም።
በከተማም ሆነ በገጠር የሚቀሰቀስ ዓመጽ፣ ወደ ጫካ የሚገባ ሽፍታ፣ በጐሳ ተቧድኖ፣ ከወንዝ ማዶ የሌላ ጐሳ ተወላጆች ላይ የሚዘምት የነውጠኞች ቡድን፣ በየጊዜው ይፈጠራል። ጥፋትም ይደርሳል።
ነገር ግን አመጹና ጥፋቱ እንደዛሬ አይደለም። ኢንተርኔትና የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭት ድሮ እንዳልነበረ አትርሱ። ጭፍን ስሜቶችን እያግለበለቡና ለአመጽ አነሳስተው እያዘጋጁ የመክረም እድል ድሮ አልነበረም። ሰበብና አጋጣሚ በተገኘ ቅጽበት፣ ከየአቅጣጫው ለአመጽ ማዝመት፣ እልፍ አእላፍ ወጣቶችን ከመቶ ከሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በፍጥነት ማጓጓዝ፣ በአንድ ንጋት ከመሃል አገር እስከ ዳር ጠረፍ ድረስ ማናወጥ፣ ድሮ አይቻልም ነበር - በእውን ሊታሰብ ቀርቶ ለህልምም ያስቸግራል። በየትኛው መኪና፣ በየትኛው መንገድ? መንገድና መኪና ብርቅ በሆነበት ዘመን፣ ከየት ይመጣል? ለአመጽ የሚዘምት ወይም ማገዶ የሚሆን፣ በሚሊዮን የተትረፈረፈ ወጣት ድሮ አይገኝም። በመንደር በሰፈር ውስጥ፣ ወሬ ፈጣን ተጓዥ ቢሆንም፣ ከሰፈር ውጭ፣ ወሬና መልእክት ቀርፋፋ በነበሩበት በድሮ ዘመን፣ በአራቱ አቅጣጫ፣ የቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳንና የአመጽ ትዕዛዝን ማሰራጨትና መለዋወጥ ጨርሶ የማታለም ነበር።
ፕሮፓጋንዳውም፣ አመፁም፣ ነውጥና ጥቃቱም፣ ወንዝ ለመሻገር ብዙ ጊዜ ይፈጅበታል። የሚደርሰው ጥፋትም፣ እንደዚያው ነው፡፡ የህዝብ ብዛት፣ የነውጠኛ ወጣት ቁጥር ጥቂት በመሆኑ ብቻ አይደለም። የሚወድም ብዙ ንብረት በቅርብ አይገኝም። በዚያ ላይ የአመጽ መሳሪያም ያኔ ውድ ነው። ክላሽና ቦምብ አልነበረም። ዛሬ ይሄ ሁሉ ተቀይሯል። ችግሩ ምንድር ነው? ያልተቀየሩ፣ የኋሊት የተመለሱና የተበላሹ ሌሎች ነገሮች አሉብን።
ከፈጣኑ የዘመናችን ለውጦች ጋር አልተራመድንም፡፡
የመንግስት አንድ ሬዲዮ፣ ለሁለት ለሦስት ሰዓት ብቻ የሚሰራ ቴሌቪዥን፣ እንደብርቅ የሚታይበት ዘመን…በጣም በጣም ጥንት ድሮ ሆኖ ነው የሚታየን። በገጠር ይቅርና በከተሞችም እንኳ፣ የስልክ መስመር የነበራቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው። ከ200 ቤተሰብ ውስጥ አንዱ ቤተሰብ ብቻ ነው የቤት ስልክ የነበረው። ዛሬ፣ ሚሊዮኖች የስልክ ባለቤት ናቸው - እንደ ቤት ስልክ የሚያገለግል ብቻ ሳይሆን፣ የትም የሚሰራ ስልክ ነው።
እንደ ደብዳቤም፤ በየደቂቃው፣ መልዕክት መላላኪያ ነው። እንደ ጋዜጣ፣ መረጃ ማግኛ፣ እንደ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ድምጽና ቪዲዮ መቀበያ አንቴና ነው ለሚሊዮኖች የተዳረሰ የዘመናችን ስልክ።
ምን ይሄ ብቻ? በየኪሳችን የምንይዘው ስልክ፣ መረጃ መቀበያ ብቻ ሳይሆን፣ ማሰራጫ አንቴናም ናቸው። የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች ናቸው ማለት ይቻላል - የዘመናችን ስልኮች። እድሜ ለሞባይል ስልክና ለኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ እድሜ ለኢንተርኔትና እንደ ፌስቡክ ለመሳሰሉ መነሃሪያዎች፤ ለብዙ ሚሊዮኖች የማሰራጫ ጣቢያ ባለቤት ሆነዋል።
ይሄ፣ ከ20 ዓመት በፊት ያልነበረ ተዓምረኛ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል።
ግን፣ ሳይለወጡ የኋሊት የቀሩና የተበላሹ ነገሮች ደግሞ አሉ። ቴክኖሎጂው መጥቋል፤ ተራቅቋል፤ ከታሰበው በላይ ተትረፍርፏል። ለእውነትና ለእውቀት ክብር ያላቸው ሳይንቲስቶች፣ እውቀትን ወደ ቴክኖሎጂ የሚለውጡ የፈጠራ ሰዎች፣ ...ከዚያም፣ በአነስተኛ ዋጋ፣ በጥራትና በብዛት አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ የቢዝነስ ሰዎች… ናቸው የዚህ ተአምረኛ ለውጥ ምንጮች። ከነዚህ የመነጨው የቴክኖሎጂ ውጤት፤ እጃችን ውስጥ ገባ፡፡ ለእውነትና ለእውቀት ክብር የመስጠት፣ ቴክኖሎጂንና ምርታማ ቢዝነስን የማድነቅ አስተሳሰብ አላዳበርንም፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂው፣ መሳሪያውና ቁሳቁሱ ከእጃችን ገብቷል - ለዚያውም በፍጥነት፣ በእልፍና በሚሊዮን። በእውቀትና በአስተሳሰብ፣ በስነምግባርና በሙያ አልሰለጠንም።
ተዓምረኛ የስልጣኔ ውጤቶች ግን፣ ከእጃችን ውስጥ ገብተው፣ መጫወቻችን ሆነዋል።
የውሸትና የአሉባልታ፣ የስድብና የብሽሽቅ፣ የጥላቻና የጥፋት ዘመቻ ማሳለጫ አድርገናቸዋል። በዱላና በጦር ሲገዳደሉ የነበሩ ነውጠኞች፣ ክላሽና ቦምብ ሲታጠቁ እንደማለት ነው። አገሬው በእሳት ለኳሹ፣ እንደተጥለቀለቀ ቁጠሩት፡፡
ተቀጣጣይ ማገዶ በሚሊዮን ተትረፍርፏል
በ55 ዓመት ውስጥ፣ የአገሪቱ የህዝብ ብዛት በ5 እጥፍ ጨምሯል፡፡ የከተማ ነዋሪ 10 እጥፍ ገደማ፣ የተማሪዎች ቁጥር ከ20 እጥፍ በላይ ሆኗል። የተመራቂ ወጣቶች ብዛት ደግሞ ከያኔው ዘመን ጋር ሲነፃፀር፣ መቶ እጥፍ ነው፡፡ ችግሩ ምንድን ነው?
የከተማ ኑሮ፣ በጐረቤትና በዘመድ ቁጥጥር ወይም በይሉኝታ ብቻ አይዘልቅም። ይልቅስ፣ ከይሉኝታና ከልማዳዊ ጨዋታ ባሻገር በሰፊው የተለመደ መሰረታዊ ጨዋነት፣ ስልጡን የስነምግባር መርሆችን ለይቶ ማወቅና ማስተማር ያስፈልጋል - የከተማ ኑሮ እንዲቃና።
ከጉርብትናና ከዝምድና ርቆ ይሄዳል - የከተማ ኑሮ፡፡ እናም የተደላደለ ሰላም፣ አስተማማኝ ህግና ስርዓት ከሌለ፣ የከተማ ኑሮ፣ ፈተና ይበዛበታል፤ አደገኛም ይሆናል። ጐን ለጐን፣ ከሙያ ብቃትና ከምርታማነት እድገት ጋር ካልተሳሰረ፣ በተለይ በተለይ ከከተማ ጋር ኢንዱስትሪ ካልተስፋፋ፣ የከተማ ኑሮ ከገጠር በባሰ አስቀያሚ ድህነት ይቃወሳል።
ድህነት ማለት የኑሮ ችግርና ረሃብ ብቻ አይደለም።
ስራ አጥነት ይባባሳል። ከህዝብ ብዛት ጋር፣ በተለይም ከወጣት ተመራቂዎች ጋር አጣምራችሁ አስቡት። - ተስፋ ያጨልማል፡፡  
ተመርቆ ወደ ጨለማ ይደርሳል - ኢንዱስትሪና የስራ እድል ስለሌለ፣ ግን ከመነሻውም፣ ትምህርቱ ብርሃን የለውም፡፡ ማንበብና መፃፍ እጅግ ብርቅ በሆነበት የሁለተኛና የሦስተኛ ክፍል ትምህርት ውስጥ የሚልፍ፤ እውቀትን በግላጭ የሚያጣጥልና የሚያንቋሽሽ የትምህርት ስርዓት የተጫናቸው ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች።
የትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች በርክተዋል፡፡ እውቀት ግን የኋሊት ተገፍቷል።
ተመራቂዎች በዝተዋል። ከተሞች ተስፋፍተዋል። ግን፤ የስራ እድልን የሚፈጥሩ ትርፋማና ስኬታማ ፋብሪካዎች የሉንም - “ለህዝብ ጥቅም” በሚል ሰበብ፣ ወይም “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “የካርቦን ልቀት” በሚሉ የጥፋት ፈሊጦች፣ የፋብሪካ ኢንቨስትመንት ይኮላሻል። ጥቂት ብቅ ብቅ ቢሉ እንኳ፣ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና በጭፍን አመጽ ይወድማሉ፣ ይሰናከላሉ።
በአጭሩ፣ እውነትና እውቀት ወደ ማክበር አላደግንም። ምርታማነትና የፋብሪካ ኢንቨስትመንት በየጊዜው ይሰናከላል። የስነ - ምግባር መርህን ከሕግና ስርዓት ጋር አላዳበርንም። በተቃራኒው እንሸረሽረዋለን - በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አማካኝነት።
በዚህ መሃል፣ ተዓምረኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እጃችን ውስጥ ገብተዋል፡፡ እውነትንና እውቀትን፣ ስነምግባርንና ቅንነትን ለማስፋፋት ሳይሆን፤ ሃሰትን፣ ጥላቻንና ክፋትን ለመንዛት ያገለግላሉ።
ከተሞችና ዩኒቨርስቲዎች በርክተዋል፡፡ ነገር ግን የምርታማነትና የእውቀት ማዕከላት ከመሆን ይልቅ፣ የአመጽና የቅስቀሳ ማዘዣ ጣቢያዎች፣ የማገዶ ማከማቻ መደብሮች ሆነዋል። ስራ አጥ ተመራቂዎችና ወጣቶች እየተትረፈረፉ ነውና።
ምን ይሻላል? ከዚህም ከዚያም ሳይሆኑ መቅረት!
እንደ ድሮ መሆን አንችልም። አይበቃንም። የከተማ፣ የትምህርት ቤት፣ የሞባይል፣ የኢንተርኔት ዓለም መጥቷል፤ እጃችን ውስጥ ገብቷል። “የድሮ አይበቃን፤ ለዘመናችንም አልበቃን” የሚባለው እዚህ ላይ ነው።
እጃችን ከገባው የዘመናችን ኑሮ ውስጥ፣ አንዳንዱ የስልጣኔ ቅርጽ ነው። ይዘቱን ያላሟላ፣ የህልውና መሰረቱን ያልያዘ ቅርጽ ብቻ። እውቀትን የማያስጨብጥ ትምህርት ቤት፤ “ስራ ፈጣሪና የኑሮ ዋስትና ፋብሪካዎች” የሌሉት ከተማ …ቅርጽ ብቻ ነው። ሌሎቹ የዘመናችን ገፅታዎች ደግሞ፣ ቁንፅል የስልጣኔ ውጤቶች ናቸው - ከስልጣኔ ጋር የተፋቱ፣ ያለ እውቀት፣ ያለ ፋብሪካ፣ ያገኘናቸው የስልጣኔ ውጤቶች በርክተዋል፡፡ የሞባይልና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አንዱ ምሳሌ ነው።
ለስልጣኔ የምንመጥን እስክንሆን ድረስ፣ መንገዳችንን ለማስተካከል እስክንመርጥና መጣር እስክንጀምር ድረስ፣ ከዚህ “አጉል” ኑሮና የመደናበር ቀውስ፣ በሰላም የመውጣትና የመሻሻል እድል ስለማናገኝ፣ በጊዜ ወደ ህሊና ማቅናት ያስፈልገናል።     

Read 6320 times