Sunday, 19 July 2020 00:00

ዓባይና የግብጽ "እኔ ብቻ ልጠቀም" ባይነት

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

  "-ግብጽ እ.ኤ.አ ከ1875-76 በምፅዋ በኩል ኢትዮጵያን ለመውረር ለቀጠረቻቸው የአውሮፓና የአሜሪካ የጦር ጄኔራሎች መቶ ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረጓ ከፍተኛ እዳ ውስጥ ተዘፍቃ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይህንንም እዳ ለመክፈል ባለመቻሏ እ.ኤ.አ በ1882 የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ቀንበር ሊጫንባት ችሏል:: እ.ኤ.አ እስከ 1922 ድረስም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆና ማቅቃለች፡፡ አበው “የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ነው!--"
         
           የግብጽ መንግስት፣ ፖለቲከኞችና ተራ ዜጎች ስለ ዓባይ ያልተናገሩበት፣ ያልተከራከሩበትና ያልተሟገቱበት ጊዜ የለም፡፡ የግብጽ መንግስት፣ ፖለቲከኞችና ተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የሀገሪቱ ነፃ የሙያ ማህበራት ጭምር በዓባይ ጉዳይ አቋማቸውን ከመግለጽ አልፈው ለመንግስታቸው ድጋፍ የሚሆኑ ውሳኔ ያሳልፉ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለዚህ አባባል ማሳያ ይሆን ዘንድ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ እ.ኤ.አ በ1945 የግብጽ መሃንዲሶች ማህበር ስብሰባ አድርጎ ነበር፡፡ ይህ ማህበር በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ፡- “1) ናይል ዓለም አቀፋዊ አይሆንም፣ 2) ናይል አይከፋፈልም 3) ናይል በግብጽ ቁጥጥር ስር ይሆናል…” የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያሳየን ስለ ዓባይ የማያስብ ግብፃዊ የሌለ መሆኑን ነው:: በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያና ግብፃውያን በዓባይ ወንዝ ጉዳይ የሰላም እንቅልፍ ሊኖራቸው የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ የሰላም እንቅልፍ ሊኖር የሚችለው ሁለቱ ሀገሮች ስምምነት ላይ ሲደርሱ ብቻ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግብፃውያን ደጋግመው እንደሚሉት፤ “የግብፅ ህይወት ዓባይ” ነው፡፡ የዓባይ ባለቤት ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ፤ ከጥንት ጀምሮ ተፈጥሮ በለገሳት ዝናብ ስለምትጠቀም በዓባይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የውሃ ሀብቶቿ ብዙም አትጠቀምም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ግብጽና ሱዳን ሲፈልጉ እየተደራደሩ፤ ሲያሻቸው እየተወዛገቡ የዓባይ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነው ኖረዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት ዓባይን አስመልክቶ ተቃውሞ አሰምቶ የነበረው የኢትዮጵያ መሪ አፄ ላሊበላ ነበር ይባላል፡፡ እሱም ቢሆን ከዛቻና ከማስፈራራት ያልዘለለ፣ ውሃ የመገደብ አቅምን ግምት ውስጥ ያላስገባ ተራ ፉከራ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ የዛሬዋ ግብጽ ረጅም የመንግስትነት ታሪክ እንዳላት ቢታወቅም፣ ያሁኑን ቅርጽዋን አካልላ የተመሰረተቺው በቱርካዊው ወታደር በሙሐመድ አሊ እ.ኤ.አ በ1805 ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንደ ቀድሞዋ ኢትዮጵያ ዘመነ መሳፍንት የውስጥ አስተዳደሯ የተከፋፈለና በማምሉኮች የሚተዳደር ነበር፡፡ ቱርካዊው ወታደር ሙሐመድ አሊ “ታላቅ ሀገር” የመፍጠር ምኞት ስለነበረው ሰራዊቱን በማዝመት ሱዳንን ጭምር አስገብሮ ያስተዳድር ጀመር፡፡ ሰውየው በዚያ አላቆመም፡፡ “ታላቅ ሀገር” የመፍጠር ህልሙን እውን ለማድረግና ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር አስቦ ሱዳንን ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰ፡፡ ይሁን እንጂ ከሱዳን በርሃ (ቆላማ አካባቢ) ባሻገር ያለው ተራራማው የኢትዮጵያ ምድር የሚነካ አልነበረምና ከዚያው ተመለሰ፡፡
ሙሐመድ አሊ እ.ኤ.አ በ1849 ሲሞት ይስሃቅ አባስ ስልጣን ያዘ፡፡ እ.ኤ.አ በ1864 አባስ ሲሞት ደግሞ የሙሐመድ አሊ የልጅ ልጅ የሆነው አስማዔል ፓሻ ተተካ፡፡ ፓሻ እንደ አያቱ እጅግ ህልመኛ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የፓሻ ሰራዊት እ.ኤ.አ ከ1875-76 በምፅዋ በኩል ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራዎችን ቢያደርግም የሀፍረት ማቅ ተከናንቦ ተመልሷል፡፡ ይህ የግብጽ ጦር በአውሮፓና በአሜሪካ የጦር ጄኔራሎች ጭምር የሚታገዝና የሚመራ ቢሆንም ከሽንፈት አላመለጠም፡፡
ግብጽ እ.ኤ.አ ከ1875-76 በምፅዋ በኩል ኢትዮጵያን ለመውረር ለቀጠረቻቸው የአውሮፓና የአሜሪካ የጦር ጄኔራሎች መቶ ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረጓ ከፍተኛ እዳ ውስጥ ተዘፍቃ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይህንንም እዳ ለመክፈል ባለመቻሏ እ.ኤ.አ በ1882 የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ቀንበር ሊጫንባት ችሏል፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 1922 ድረስም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆና ማቅቃለች፡፡ አበው “የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ነው!
ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓባይን በተመለከተ ፈርማለች የሚባለው ውል እ.ኤ.አ በ1902 በአፄ ምኒልክ የተፈረመው የድንበር ውል ነው፡፡ ይህ ውል የተፈረመው በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ሲሆን፤ ዋና ዓላማው በሱዳን በኩል ያለውን ድንበር ለመካለል የተደረገ ውል ነው፡፡ ውሉ ከእንግሊዝ ጋር የተደረገበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ እንግሊዝ የሱዳንና የግብጽ ቅኝ ገዢ በመሆኗ ነበር፡፡
አፄ ምኒልክ ያንን ውል የተፈራረሙበት ዋነኛ ምክንያት ሀገራቸው በሱዳን በኩል ያላትን ድንበር አስረግጦ ለማስመር ነው:: ይሁን እንጂ፤ እድሜ ልካቸውን ሴራና ተንኮል በመጎንጎን ዓለም የሚያውቃቸው እንግሊዞች በዚያ ውል ውስጥ ከውሉ መሰረታዊ ጉዳይ የወጡ ነገር ግን የእነርሱን ፍላጎት የሚያሟሉ አሳሳች አንቀፆችን አስገብተው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በዚያ ውል ኢትዮጵያ ግብጽ በዓባይ ላይ ያላትን “ተፈጥሯዊና ታሪካዊ” መብት እንደሰጠችና በጣና ሐይቅም ሆነ በዓባይ ላይ ግድብ እንደማትሰራ እንዳረጋገጠች ተደርጎ ተጽፎ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ በዚያ ውል ላይ መስፈሩ ኢትዮጵያን እግር ከወርች ጠፍሮ ለማሰር ታስቦ የተደረገ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር የዓባይ ወንዝን በተመለከተ አለኝ በማለት በአንዳንድ መድረኮች ላይ ለመሞገት የምትሞክረው ይህንኑ በቀድሞ ቅኝ ገዢ ጌቶቿ የተፈረመ ባልቴት ውል በመጥቀስ ነው፡፡ በመሰረቱ የሁለትዮሽ (Bilateral) ውል አንዱ ወገን አልፈልገውም ብሎ ከተወው ዋጋ ሊኖረው የማይችል መሆኑን የፖለቲካ ሣይንስ ምሁራን “ዓለም አቀፍ የውሎች ህግ” የሆነውን የቬና ስምምነት (Law of treaties of Veinna convention) በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
አ.ኤ.አ በ1956 ግብጽና ሱዳን በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ድርድር ሲጀምሩ የውሃው ባለቤት የሆነቺው ኢትዮጵያ ግን ተገልላ ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት ቅር ተሰኝቶ ነበር:: ይህንኑም ቅሬታ ለመግለጽ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒው ዮርክ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤትና ካይሮ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ጭምር ሰፊ ደብዳቤ ጽፎ የበተነው እ.ኤ.አ በ1957 ነበር፡፡ የዚህ ደብዳቤ መንፈስ እ.ኤ.አ በ1956 በግብጽና በሱዳን በኩል የተጀመረው ድርድር፣ ኢትዮጵያን ያገለለ በመሆኑ ተገቢ አለመሆኑን የሚያስረዳ ነበር:: ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገሮች የጀመሩትን ድርድር ገፍተውበት እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በዚህ ውል መሰረት የሱዳን ድርሻ 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሲሆን፤ የግብጽ ድርሻ ደግሞ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነበር:: ሱዳኖች ይህንን ዓይን ያወጣና ፍትህ የጎደለው ክፍፍል የተቀበሉበት ምክንያት፤ ሁለቱ ሀገሮች ይዋሃዳሉ የሚል አመለካከት በወቅቱ ይናፈስ ስለነበር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ከላይ እንደተገለጸው፤ ተቃውሞን ከመግለጽ ባሻገር እ.ኤ.አ በ1958 ከአሜሪካን የመሬት ይዞታ መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር በርካታ አሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በእርሻና ኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተዋውለው ነበር:: ይሁን እንጂ እነዚያ አሜሪካውያን ባለሃብቶች እ.ኤ.አ በ1964 ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል:: ከአሜሪካውያኑ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተግባራዊ የሆነው የፊንጫ ስኳር ፕሮጀክት ብቻ ነበር፡፡ ለአሜሪካውያኑ ወደ ሀገራቸው መመለስና ስለ ፕሮጀክቶቹ መቋረጥ በርካታ መላምቶች ቢኖሩም፤ “በግብጽና በእንግሊዝ አሻጥር ነው” በሚለው ሃሳብ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ወደ ስልጣን የመጡ የግብጽ ባለስልጣናት፤ ዓባይን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በተግባር ግን ኢትዮጵያ ያለቺበትን ውሃ ነክ ድርድር አይፈልጉትም፡፡ ለምሳሌ በ1978 ዓ.ም በኡጋንዳ ካምፓላ አንድ ውሃ ነክ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ አልተጠራቺም፡፡ የዚህ ድራማ መሪ ተዋናይ ደግሞ ግብጽ ነበረች፡፡ ዓላማዋም፤ “ናይል ኮሚሽን” የተሰኘ ተቋም ኢትዮጵያን ሳይጨምር ከዘጠኙ የተፋሰሱ ሀገራት ተውጣጥቶ እንዲቋቋም ማድረግ ነበር፡፡
በዚህ አካሄድ የተበሳጨው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ባልተጠራበት ስብሰባ ላይ የልዑካን ቡድን ወደ ካምፓላ በመላክ “ኢትዮጵያ የሌለቺበት የናይል ኮሚሽን ብሎ ነገር ሊቋቋም ቀርቶ ሊታሰብ አይችልም” በማለት አስገነዘበ፡፡ የተፋሰሱ ሀገሮችም የጉዳዩን ትክክለኛነት አምነውበት “የናይል ኮሚሽን” ሳይቋቋም ስብሰባው ተበተነ:: የግብጽም ጥረት በኪሳራ ተደመደመ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል ተጎናጽፋለች ለማለት ይቻላል፡፡
የዓባይ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳት ግብጽ፤ የ1978ቱን ክስረት ለማካካስ ጥረቷን አላቋረጠቺም ነበር፡፡ በተለይም በ1983 ዓ.ም አካባቢ የተፋሰሱን ሀገሮች በተናጠል በመቅረብ በኪስዋሂሊ ቋንቋ “ኡንዱጉ” (ትርጉም፡- ወንድማማችነት) የተሰኘ የዲፕሎማሲ ጥረት ስታደርግ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ስብሰባ ቢካሄድ እንኳ የተፋሰሱ ሀገሮች ከግብጽ ጎን እንዲሰለፉ ለማድረግና ኢትዮጵያን ብቻዋን በማስቀረት የግብጽን ፍላጎት የሚያሟላ ውሳኔ ለማስወሰን የታለመ ነበር፡፡
በአጠቃላይ፤ በዓባይ ጉዳይ ላይ የግብጽ አቋም ምንጊዜም ኢትዮጵያን በማግለል፣ ሌሎቹን የተፋሰሱን ሀገራት በማወናበድ፣ በማጭበርበርና በብልጠት በማታለል በግሏ ለመጠቀም የሚደረግ ጥረት ነው:: ይህንንም በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በይፋ ሲናገሩት የኖረ ሀገር ያወቀው፤ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 13 ቀን 1978 የግብጽ የውሃና የመስኖ ሚኒስትር “የዓባይን ወንዝ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት የግብጽ መንግስት በፍፁም አይፈቅድም” በማለት የተናገሩ ሲሆን፤ የያኔው የግብጽ ፕሬዝዳንት አንዋር አል-ሳዳት ራሳቸው፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወይም በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ እሰራለሁ ብትል የግብጽ መንግስት ጦርነት የሚቀሰቅስ መሆኑን በግልጽ በአደባባይ “ከዚህ በኋላ ጦርነት የሚነሳ ከሆነ በውሃ ጉዳይ ነው” በማለት ተናግረዋል:: የግብጽ መንግስት፣ ህዝብና የሙያ ማህበራት ጭምር በዓባይ ላይ እንዲህ ያለ አቋምና ዝግጅት ያላቸው ሲሆን፤ መንግስት በየጊዜው ቢቀያየር እንኳ የማይቀየሩ፣ የዓባይን ጉዳይ ስራዬ ብለው የሚከታተሉና በጥልቀት የሚያጠኑ ባለሙያዎችም አሉ፡፡
የግብጽ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ “የዓባይ ወንዝ መዳኘት ያለበት በዓለም አቀፍ ህግና ስምምነት መሰረት ነው” በማለት አሳሳች ሃሳብ ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ሃሳብ ያነበበ ሰው “ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ይሁን ነው የምትለው?” የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል:: እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ውሃን በተመለከተ ምንም ዓይነት “ሕግ” የለም! ለማደናገር ነው እንጂ:: የግብጽ ባለስልጣናት ይህንን ሀቅ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም፡፡
ዓለም አቀፍ የውሃ ህግ አለ ከተባለ በሀገሮች መካከል በተናጠል የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ናቸው፡፡ በሁለት ሀገሮች የተደረጉ (Bilateral) ስምምነቶች እንደ ተሞክሮ ሊወሰዱ ይችሉ እንደሆነ እንጂ “ዓለም አቀፍ ህግ” ተብለው የዓለም ሀገሮች ሁሉ የሚዳኙበት ሊሆን አይችልም፡፡ በርግጥ በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የአንድ ሀገር የግል ሀብት አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡ የህግ ባለሙያዎችም ሄልሲንኪ ላይ ተሰባስበው በጉዳዩ ላይ መክረውበታል:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት ግን ወንዝን የሚዳኝ ምንም ዓይነት ህግ አልደነገጉም፡፡ እናም የግብጽ ባለስልጣናት “ዓለም አቀፍ የውሃ ህግ” ሲሉ ለየትኛው “ዓለም”፣ በማን የተዘጋጀውን “ህግ” እንደሆነ በግልጽ ቢናገሩ፣ ኢትዮጵያችን ከዓለም ስርዓት የምትወጣ አይሆንም ብዬ አስባለሁ፡፡
ዓባይን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ጠንካራ የባለቤትነት አቋም ከመኖሩ ባሻገር የወንዙ ማስተር ፕላን እንኳ በቅጡ የተዘጋጀ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ በአሁኑ ወቅት ያለው መንግስት፤ የውሃን ጉዳይ የሚከታተል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲቋቋም ማድረጉ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ባለፉት ዘመናት ለዓባይም ሆነ ለሌሎች ወንዞቿ ጠንከር ያለ ትኩረት አለመስጠቷ ይታወቃል፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት የውስጥ ሰላማችን መናጋትና ድህነታችን ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ይህንን እግር ከወርች ቀፍድዶ የያዘንን ድህነት ለማስወገድ በውሃ ሀብታችን እንጠቀማለን ካልን ደግሞ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የረዥም ጊዜ እቅድና የወንዞችና ተፋሰሶች ማስተር ፕላን ሊዘጋጅ ይገባዋል:: ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ስለ ወንዞቻችን እንዲያውቅ መደረግ ይገባዋል:: በትምህርት ስርዓታችን ውስጥ ድህነትን ከእነ ሰንኮፉ ነቅሎ ለመጣል የውሃ ሀብታችን ትልቁ መሳሪያችን መሆኑን ወጣቶች እየተማሩ እንዲያድጉ ማድረግም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በመንግስት በኩል አንድን ጉዳይ ነጥለው የሚከታተሉ ባለሙያዎች (Experts) መንግስት በተቀየረ ቁጥር የሚቀያየሩ ከሆነ፣ ነገሩ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው:: በግብጽ በኩል ስለ ዓባይ ጉዳይ ጡረታ ከወጡ በኋላ ጭምር 40 ዓመት የሚከታተሉ ባለሙያዎች አሏቸው:: ከዚህ በመማር ከስር ከስር ተተኪዎችን በማሰልጠን ትኩረት ሰጥተን መስራት ይገባናል::
ባንግላዴሽ የምትባለው በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኝ ሀገር፤ በብጥብጥና በሁከት የታወቀች ሀገር ናት፡፡ መንግስትም በየጊዜው ይቀያየርባታል፡፡ የፈለገውን ያህል መንግስት ይቀያየር እንጂ ባለሙያዎች ስለማይነኩ የዚያች ሀገር ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሂደትና ግንኙነት ችግር ገጥሞት አያውቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለሙያዎቹ በጡረታ ቢገለሉ እንኳ በቀድሞ መስሪያ ቤታቸው በአማካሪነት እንዲሰሩ ነው የሚደረገው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር ለእኛም ሀገር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 2222 times