Saturday, 18 July 2020 15:11

“ነገርዬው ከዚህም በላይ እጅግ አስከፊ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል…” - ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በኮሮና ሳቢያ የከፉ ጥፋቶችን ብታስተናግድም የሚበጃትን መላ ከመምታት ይልቅ አጉል አጉሉን መንገድ መከተሏን የያዘችው አለማችን፣ ቆም ብላ ማሰብና የሚበጀውን መንገድ መከተል ካልጀመረች፣ ከዚህም በላይ የከፋ ነገር ማስተናገዷ አይቀሬ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
“እጅግ በርካታ የአለማችን አገራት በተሳሳተ መንገድ መጓዛቸውን ገፍተውበታል፤ ኮሮና ቫይረስም የአለማችን ቁጥር አንድ የሰው ልጆች ጠላት ሆኖ ጥፋቱን እያስፋፋ ቀጥሏል!... መደባበቅ አያስፈልግም፤ የማይጠቅመውን ነገር ትተን የኮሮናን ጉዳይ ሙያዊ በሆነ መንገድ በቁጥጥር ስር ለማዋል በአፋጣኝ ርብርብ ካላደረግን በቀር፣ ጉዳዩ የበለጠ አስከፊ እየሆነ መሄዱ አይቀሬ ነው!” በማለት ነበር የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እቅጩን የተናገሩት፤ የአለማችን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 13 ሚሊዮን መድረሱ በተነገረባት የሳምንቱ የመጀመሪያዋ ዕለተ ሰኞ፡፡
ሰውዬው ሰኞ ዕለት ይህን ካሉም በኋላ፣ ቀናት በተፈራረቁ ቁጥር ቫይረሱ በመላው አለም በፍጥነት እየተሰራጨና ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት እየዳረገ ነው ሳምንቱን ያገባደደው፡፡
የዎርልዶ ሜትር ድረገጽ ዘገባ እንደሚለው፤ ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ13 ሚሊዮን 780 ሺህ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ559 ሺህ አልፏል:: እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ አሜሪካ 3,639,653፣ ብራዚል 1,972,072፣ ህንድ 992,746፣ ሩስያ 752,797፣ ፔሩ 337,724 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት ሲሆኑ፣ ከአለማችን አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት በተዳረጉባት አሜሪካ የሟቾች ቁጥር ከ140 ሺህ በላይ ማለፉ ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር በብራዚል ወደ 76 ሺህ የተጠጋ ሲሆን፣ በእንግሊዝ ከ45 ሺህ በላይ፣ በሜክሲኮ ከ37 ሺህ በላይ ሲደርስ፣ ከ28 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ስፔን በሞት ያጣቻቸው ዜጎቿን ለማሰብ ባለፈው ሃሙስ ባካሄደችው የመታሰቢያ ሥርዓት ወረርሽኙ በአገሪቷ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ዘክራለች፡፡
አፍሪካ እና መሰንበቻው
በግንቦት ወር መጨረሻ 100 ሺህ የነበረው የአፍሪካ አህጉር የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር፣ በሃምሌ መጀመሪያ ላይ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ማደጉን ያስታወሰው የአለም የጤና ድርጅት፤ከ35 በመቶ በላይ በሚሆኑት የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በእጥፍ ያህል ማደጉን ይጠቁማል፡፡
እስካሁን ድረስ በአህጉሪቱ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአምስት አገራት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆመው ድርጅቱ፣ በሃምሌ ወር አጋማሽ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 75 በመቶ ያህሉ በደቡብ አፍሪካና ግብጽ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡ ቫይረሱ እስካለፈው ሀሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አፍሪካ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ከ645 ሺህ ያለፈ ሲሆን፣ ለሞት የተዳረጉት ሰዎችም 15 ሺህ ያህል መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በበኩሉ፤ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ፍጥነት መሰራጨቱን ከቀጠለና ከመጪው 2020 ግማሽ አመት ካለፈ አህጉሪቱ በ2020/21 የፈረንጆች አመት በቫይረሱ ሳቢያ 236.7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ ሊያጋጥማት እንደሚችልና የአህጉሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በአመቱ በ1.7 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
በቅርቡ ስልጣን የያዙት የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዘሬስ ቻክዌራ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ህዝባቸው ለሶስት ቀናት በሚቆይ ብሔራዊ ጾምና ጸሎት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትና ባለፈው ሰኞ በ59 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ልጅ፣ ዚንዲዚ ማንዴላ በአስከሬናቸው ላይ በተደረገው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደነበር መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቀጣይ የአለማችን ስጋትና ፈተናዎች
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ አለማችን በመጪዎቹ 18 ወራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከኢኮኖሚ እስከ ጂኦፖለቲክስ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችና ስጋቶች እንደሚያጋጥሟት ያስታወቀ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ የአለም ህዝቦችን የሚያሰጋቸው ፈተና ኢኮኖሚያዊ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
አለማችን በተጠቀሰው ጊዜ ያጋጥማታል ተብለው ከተጠቆሙት 31 ያህል ስጋትና ፈተናዎች መካከል አስሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ዘጠኙ ማህበራዊ፣ ስድስቱ ጂኦፖለቲካዊ፣ አራቱ ቴክኖሎጂያዊ፣ ሁለቱ አካባቢያዊ መሆናቸውንም መረጃው ጠቁሟል፡፡
ከቀዳሚዎቹ የአለማችን ቀጣይ ፈተናና ስጋቶች መካከል የተራዘመ አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት፣ ሌላ የበሽታ ወረርሽኝ ክስተት፣ የኢንዱስትሪዎች ማገገም አለመቻል፣ ተጨማሪ የጉዞ እገዳዎችና የንግድ እንቅስቃሴ ገደቦች፣ የማህበራዊ ዋስትና መዳከም፣ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጭማሪ፣ የጤና አገልግሎቶች የዋጋ ውድነትና የከፋ የአእምሮ ጤና ችግር መስፋፋት እንደሚገኙበትም መረጃው አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ቻይና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበች የመጀመሪያዋ ሃያል አገር መሆኗን የዘገበው ብሉምበርግ፤ አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ካነሳችና ፋብሪካዎችን መክፈት ከጀመረች በኋላ ባለፈው ሩብ አመት ያልተጠበቀ የ3.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን አመልክቷል፡፡
ቻይና እስከ ሃምሌ በነበሩት 3 ወራት ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ያልተጠበቀና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚያ በፊት በነበረው ሩብ አመት ኢኮኖሚዋ በ6.8 በመቶ ቀንሶ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
ክትባት እና መድሃኒት
አለም ለመጣባት የጥፋት ማዕበል መላ የሚሆናትን ክትባት ወይም መድሃኒት ለማግኘት ደፋ ቀና ማለቷን አሁንም አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ ከሰሞኑም ከሌሎች በተለየ ተስፋን የሚሰጥ ወሬ ከወደ አሜሪካ ተሰምቷል፡፡
ለኮሮና ክትባት ለማግኘት ሰፊ ምርምር ሲያደርግ የቆየው የአሜሪካው የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ሞደርና፣ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ክትባቱን በሰዎች ላይ ለመሞከር ወደሚያስችለው የመጨረሻ ደረጃ የሙከራ ሂደት እንደሚገባ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሙከራው 30 ሺህ ሰዎችን ለማሳተፍ ማቀዱንም ገልጧል፡፡
ስምንት የአለማችን አገራት መሪዎች በቀጣይ በምርምር ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ የኮሮና ክትባቶችን በፍትሃዊነት ለአለም ህዝቦችና አገራት ለማዳረስ ትኩረት እንዲሰጥ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና የካናዳ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የኒውዚላንድ፣ የደቡብ አፍሪካና የስፔን መሪዎች እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከ150 በላይ የሚሆኑ የአለማችን አገራት የኮሮና ክትባትን በመላው አለም ለሚገኙ አገራት በፍትሃዊነት ለማዳረስ እየሰራ የሚገኘው ኮቫክስ የተሰኘ ስብስብ አባል ሆነው ዜጎቻቸውን የክትባቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከእነዚህ አገራት መካከል 75 የሚሆኑት የራሳቸውን ፋይናንስ በመመደብ ክትባቱን ለማስገባት የፈቀዱ መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል በበኩሉ፤ ውጤታማነታቸው የሚረጋገጡ የኮሮና ክትባቶችን በአፍሪካውያን ኩባንያዎች ማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የክትባቱ ፈጣሪዎች ለኩባንያዎቹ የአእምሮአዊ ንብረት መብት ፍቃድ እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ ገልጧል፡፡
ኖቫርቲስ የተባለው የስዊዘርላንድ ኩባንያ ምንም አይነት የገንዘብ ትርፍ የማይገኝባቸውን ከኮሮና ጋር በተያያዘ ለህክምና የሚውሉ 15 አይነት መድሃኒቶች ለ79 ያላደጉ አገራት እንደሚለግስ ማስታወቁን የዘገበው አልጀዚራ፣ ሩስያ በበኩሏ ለ30 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን በሙከራ ላይ የሚገኝ የኮሮና ክትባት በአገር ውስጥ ለማምረት ማሰቧን አስነብቧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በፈረንጆች አመት 2019 በመላው ዓለም 14 ሚሊዮን ያህል ህፃናት መሰረታዊ የሚባሉና በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ ህመሞችን ክትባቶች  አለመከተባቸውን የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ያስታወቁ ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክትባቶች በመቋረጣቸው ቁጥሩ በእጥፍ ያህል ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት 30 አመታት ታሪክ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተለያዩ ህይወት አድን የሆኑ ክትባቶች አለመከተባቸውን የጠቆሙት ተቋማቱ፣ በ2020 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ብቻ የፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ ማጅራት ገትር፣ ቲታኖስና የማያቋርጥ ሳል መከላከያ ክትባቶችን የወሰዱ ህጻናት ቁጥርም በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
ህጻናት እና ትምህርት
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በመላው አለም በርካታ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች አገልግሎታቸውን አቋርጠው መዘጋታቸውን ያስታወሰው ሴቭ ዘ ችልድረን፣ 9.7 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት ዳግም ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በመላው አለም ወረርሽኙን ለመግታት ታስቦ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በመዘጋታቸው ከአለማችን ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ ወይም 1.6 ቢሊዮን ያህል ወጣቶች ትምህርት ማቆማቸውን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ በቀጣይም 9.7 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የቤት ውስጥ ስራ እንዲሰሩ፣ ተገድደው እንዲዳሩ በመደረጋቸው እስከ ወዲያኛው ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ተጽዕኖ፣ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የ2021 የፈረንጆች አመት የትምህርት ዘርፍ በጀት ላይ የ77 ቢሊዮን ዶላር እጥረት ሊያስከትል እንደሚችልም ባለፈው ሰኞ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
አንዳንድ ነገሮች - በኮሮና ዙሪያ
ኮሮናን እንደ ቀላል ጉንፋን በመቁጠር የራሳቸው መዘናጋት ሳያንሳቸው ህዝባቸውንም ለከፍተኛ ጥፋት የዳረጉትና በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ፣ ባለፈው ረቡዕ በድጋሚ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የዘገበው አልጀዚራ፣ ሰውዬው ግን አሁንም ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት ኮሮናን ለማዳን ተጠቀሙ ሲሉ መደመጣቸውን ገልጧል፡፡ የደቡብ አፍሪካው የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር እና ባለቤታቸውም በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
የቺሊ መንግስት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን አነፍንፈው መለየት የሚችሉ ውሻዎችን ማሰልጠን መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፣ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ላብ ከሰውነታቸው ስለሚወጣና የተለየ መዓዛ ስለሚያመነጩ ውሾቹ ይህንን መዓዛ በማነፍነፍ የቫይረሱ ተጠቂዎችን እንዲለዩ ለማድረግ መታሰቡን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የእንግሊዝ ጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ፤የአገሪቱ ዜጎች በቢሮ ውስጥና በሥራ ቦታዎች ላይ የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብል ወይም ማስክ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ ማስተላለፋቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ በአገሪቱ በህዝብ መጓጓዣዎችና በሱቆች አካባቢ ማስክ ማድረግ ግዴታ ከሆነ ወራት መቆጠራቸውን አስታውሷል፡፡
ቫይረሱ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎችን የቀጠፈባትና ከሰሞኑ ደግሞ በፍጥነት መሰራጨት የጀመረባት ፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፤ በዝግ ህዝባዊ ስፍራዎች ውስጥ የአፍና የፊት ጭምብል ማድረግ ከመጪው ነሃሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ ግድ እንደሚሆን ከትናንት በስቲያ ለህዝባቸው አስታውቀዋል፡፡
በአገሪቱ ፖሊስ ስልጠና እየተሰጣቸው የሚገኙት እነዚሁ አነፍናፊ ውሾች እስከ መጪው ወር ስልጠናቸውን ጨርሰው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ባቡር ጣቢያዎችና የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል።

Read 10765 times