Saturday, 11 July 2020 00:00

አቶ ክበበው እና ገራሚዎቹ የልጆቻቸው ስሞች

Written by  በአንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

  (ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ዲዩትሮን፣ ፖሲትሮን…)
                    በአንተነህ ይግዛው



              እ.ኤ.አ በ2015...
በወርሃ መጋቢት አጋማሽ ላይ፣ ኢትዮጵያን ከስም ጋር ያቆራኘ ዜና ከወደ አሜሪካ በተለያዩ ድረገጾች ተሰራጨ፡፡
ለየት ያለ ስም ያላቸውን ግለሰቦች እየመረጠ በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው አንድ ታዋቂ የአሜሪካ ድረገጽ፣ በዚያው ሰሞንም ለ33ኛ ጊዜ በዕጩነት ያቀረባቸውን ስሞች ይፋ በማድረግ፣ ህዝቡ ለመረጠው ልዩ ስም ድምጽ እንዲሰጥ ጋበዘ፡፡
ከፍተኛውን ድምጽ ያገኘው ታዲያ፣ ኢትዮጵያዊው አባት አቶ ክበበው ለልጃቸው ያወጡት ስም ሆነ...
ኤሌክትሮን ክበበው!..
ነገሩ እንዲህ ነው...
ኢትዮጵያዊው አባት አቶ ክበበው፣ በሙያቸው የኤሌክትሪካል ኢንጂነር ናቸው::
ልጆቻቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው እንዲያድጉና በሳይንሱ ዘርፍ ልቀው እንዲወጡላቸው አጥብቀው ይሻሉ፡፡
ይህን መሻታቸውን እውን ለማድረግ ግን፣ ተግተው በልጆቻቸው ላይ መስራት እንዳለባቸው አላጡትም፡፡ በብላቴና ልጆቻቸው ልቦና፣ “ሳይንስ” የሚል ትልቅ ሃሳብ መትከል እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡
ለልጆቻቸው ደጋግመው ስለ ሳይንሱ መስክ ታላቅነት መተረክ፣ ወደ ሳይንሱ መስክ የሚያመሩበትን መንገድ ማመላከት፣ በሳይንሱ ገፍተው እንዲጓዙ ለሚያስችሏቸው የትምህርት አይነቶች ትኩረት እንዲሰጡ መደገፍ... እንዲህ እና እንዲያ ያለውን ጥረት ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ - አባትዬው!
ይሄም ሆኖ...
አቶ ክበበው እንዲህ እና እንዲያ ያለውን የኩትኮታ ስራ ለመጀመር፣ የወለዱት ልጅ ነፍስ እስኪያውቅና ፊደል መቁጠር እስኪጀምር መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
እሳቸው ግን፣ የወለዱት ልጅ ነፍስ እስኪያውቅና ፊደል እስኪቆጥር ስራ አይፈቱም... ገና እንደተወለደ፣ ወሳኝ ያሉትን ሌላ ስራ ይሰሩበታል...
በዘመን በማይላላ፣ በእርጅና በማይበጠስ፣ በጠንካራ የዕድሜ ልክ ክር “ጨቅላውን” ከ“ሳይንስ” ጋር ያስተሳስሩታል... ወደ ነገው ይመሩታል...
“ስም” ይባላል - ይህ ጠንካራ ክር!...
ኤሌክትሮን ክበበው
ፕሮቶን ክበበው
ኒውትሮን ክበበው
ዲዩትሮን ክበበው እና ፖሲትሮን ክበበው
እነዚህ አምስቱ የአቶ ክበበው ልጆች ናቸው፡፡
አቶ ክበበው ለአምስቱ ልጆቻቸው ያወጧቸው ስሞች፣ ግርምትን የሚያጭሩ ቢሆኑም...
ልጆቻቸው ዛሬ የደረሱበት ደረጃ፣ አባትዬው ለስም የሚሰጡትን ዋጋና ልጆቻቸውን በስማቸው በኩል ወደ ሳይንስ ለመጥራት ያደረጉትን ገራሚ ጥረት ልክነት አስመሰከረ...
ይህም ብቻ አይደለም...
ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው ስም በልጁ ቀጣይ ዝንባሌ፣ አመለካከትና የህይወት ምርጫ ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ ይፈጥራል ብለው ለሚሟገቱ የስነ ልቦና ምሁራንም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው - የአቶ ክበበው ልጆች አጋጣሚ፡፡
ከኤሌክትሮን ክበበው እንጀምር...
አድጎ ሳይንስን እንዲያጠናላቸው በማሰብ ጨቅላ ሳለ ኤሌክትሮን የሚል ስም ያወጡለት የትናንቱ ብላቴና፣ ዛሬ በስሙ ብቻ ሳይሆን በስኬቱም ብዙዎችን ያስደመመ የህክምናው ዘርፍ ቁንጮ ሆኗል...
እ.ኤ.አ በ2011...
“የአመቱ የአሜሪካ 1000 ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች” በሚል “ዊኪኦርግቻርትስ” ድረገጽ ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፣ ዶ/ር ኤሌክትሮን ክበበው ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቀጥሎ በሁለተኛነት ተቀምጠዋል!...
መረጃው እንደሚለው፤ ዶ/ር ኤሌክትሮን በአመት 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡
በአዲስ አበባው ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የተማሩት ዶ/ር ኤሌክትሮን ክበበው፤ በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ በህክምና የተመረቁ ሲሆን የአሜሪካን ቦርድ ኦፍ ሰርጀሪን የቀዶ ህክምና ሰርተፊኬትም አግኝተዋል፡፡
ላለፉት ከ20 በላይ አመታት በሳንፍራንሲስኮ በኢንዶክሪንና ታይሮይድ ካንሰር ዘርፍ የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ዶክተሩ፤ በአሜሪካ ብሄራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት፣ የካንሰር ምርምር ማዕከል የኢንዶክራይን ኦንኮሎጂ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሲሆኑ የካንሰር ጄኔቲክስ ክፍሉንም በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶክተሩ በእስካሁኑ የሙያ ዘመናቸው ከሁለት ሺህ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን ያከናወኑ ሲሆን ከ150 በላይ የጥናት ጽሁፎችንና መጽሃፍትን ለህትመት እንዳበቁ “ብሬኪንግጎቭ” የተሰኘ ድረገፅ አመልክቷል::
ሌላኛዋ የአቶ ክበበው ልጅ...
ፖሲትሮን ክበበው...
ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚቺጋን በህክምና ተመርቃ ከ20 አመታት በላይ ያገለገለችና፣ በካሊፎርኒያ ሳንታ ሞኒካ በመስራት ላይ የምትገኝ ዝነኛ ዶክተር ናት፡፡
ደሞ ሌላኛው ልጃቸው...
ዲዩትሮን ክበበው...
ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ አባቱ በተመረቁበት በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቆ፣ በዚያው በአሜሪካ እየሰራ ይገኛል...
አቶ ክበበው ተሳክቶላቸዋል...
ሆነ ብለው ሳይንስ ነክ ስም ያወጡላቸው ልጆቻቸው፣ እንዳሰቡት ወደ ሳይንሱ አለም ተስበዋል... ስኬታማም ሆነዋል...
እርግጥ ነው...
አቶ ክበበው ለልጆቻቸው ያወጡት ስም ብቻውን የፈጠረው ተጽዕኖ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም...


Read 1094 times