Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

ከሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  "--ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙ ንብረት ወድሟል፤ የብዙዎች አካል ጐድሏል፤ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ሰፊና አሳዛኝ ጉዳት ነው የደረሰው፡፡ ይሄን ለማጣራት አጠቃላይ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡--"
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ ከእስረኞች አያያዝ ሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ፣ ኮሚሽነሩ የሚያደርጋቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን ዶ/ር ዳንኤል በቀለን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ  አነጋግሯቸዋል፡፡


          ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ግድያውን ተከትሎ ከተፈጠሩ ሁከቶች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክታችኋል፡፡ በምልከታችሁ  ምን አገኛችሁ?
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር የሚገኙትን እነ ጀዋር መሃመድና በቀለ ገርባ እንዲሁም እነ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮልና ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን  ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎች ያሉበትን  ሁኔታ ተመልክተናል፡፡ በጉብኝታችን የተረዳነው ነገር በአጠቃላይ ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም በተያዙበት ወቅትና ወደ እስር ቤት ከሄዱም በኋላ በውጪ እንደተወራው ሳይሆን ምንም አይነት አካላዊ ጥቃት እንዳልደረሰባቸው አረጋግጠውልናል፡፡ ሁለቱ ማለትም  እስክንድር ነጋና የኦኤምኤን ድረ-ገጽ ላይ ይሰራ እንደነበር የገለጸልን ሸምሰዲን ጠሃ የተባለ ታሳሪ፤ ፖሊስ ባሰራቸው ወቅት ድብደባ እንደፈጸመባቸው ነግረውን  ነበር፡፡ እኛም ስለ ጉዳዩ ትንሽ ለማጣራት ሙከራ አድርገናል፡፡ ፖሊሶች እንደነገሩን፤ በተለይ እስክንድር ነጋን ሲይዙ ትንሽ አለመግባባትና  የቃላት ልውውጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህም ትንሽ ፍጥጫ ተፈጥሮ እንደነበር ነው የገባን፤ ምን አልባት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ተፈፅሞ ሊሆን እንደሚችል መገመት  ይቻላል፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ሁኔታውን ስላሳወቅነው ፖሊስ ራሱ ጉዳዩን  እንዲያጣራ አሳስበናቸዋል፤ እነሱም እናጣራለን ብለውናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን እስረኞቹን በሙሉ እኛ በአካል ተመልከተናቸዋል፡፡ በአካላቸው ላይ የጤንነትም ሆነ የአካል ጉዳት ምልክት አላየንም፡፡ አካላዊ ጤንነታቸው ደህና ነው፡፡ በተለይ የኢንጂነር  ይልቃል ጌትነት ቤተሰቦች፣ ምን እንደገጠመው በትክክል አያውቁም ነበር፡፡ በደህንነቱ ላይ የከፋ ችግር ደርሷል የሚል ግምት ነበር፤ ነገር ግን ኢ/ር ይልቃልንም ረቡዕ እለት አይቼዋለሁ፤ አካላዊ ጤንነቱ ደህና ነው፡፡ በአጠቃላይ ታሳሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተናል:: አንዳንድ ታሳሪዎች ችግር የሆነባቸው ከኮሮና በሽታ ጋር ተያይዞ በወጣው አዋጅና  ደንብ ላይ የእስረኞች ጉብኝትና ስንቅ ማቀበል፣ አልባሳት ማስገባት ላይ ገደብ የተጣለ መሆኑ ነው፤ ነገር ግን ይሄ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እስረኞች ትልቅ ችግር  ነው የሆነው፤ ስለዚህ ይህን ችግር በማስመልከት ከእስር ቤቱ አስተዳደር ጋር ተወያይተናል፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄም እየተሰጠ ነው፡፡ አንደኛው  መፍትሄ የጤንነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ምግብ ከቤተሰቦቻቸው እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን፣ ልብስንም በተመለከተ እንዳስፈላጊነቱ ዲስኢንፌክት ወይም ታክሞ እንዲገባላቸው  እንዲደረግ ተነጋግረናል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ እጠብቃለሁ፤ ከወዲሁ መሻሻልም የጀመሩ አሉ፡፡ አሁን ለተወሰኑት ነው እየተሻሻሉ ያሉት፤ በቀጣይ ለሁሉም መሆን አለበት:: በሌላ በኩል፤ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያም ሆነ  ሌላም ቦታ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ስላሉ፣ የጠቅላላ የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ክትትል ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡
በአዲስ አበባ የታሰሩት ምን ያህል እንደሆኑ በውል ታውቃላችሁ?
ሁለት አይነት ቁጥር ነው ያለው:: በመጀመሪያ ላይ መንግስት ከዚህ ጉዳይጋር በተያያዘ ወደ 35 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን ነው የገለጸው፡፡ እኛም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን ስንመለከት ቁጥራቸው ከ30 እስከ 35 የሚደርሱ  የታሰሩ ሰዎች አግኝተናል፡፡ ውሎ አድሮ ደግሞ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተጨመሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 1200 የሚደርሱ ሰዎች  መታሰራቸውን የገለጸ ሲሆን አብዛኞቹ ከሁከቱና ከረብሻው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ናቸው፡፡ ፖሊስ የተወሰኑትን ምክር ሰጥተን እንለቃቸዋለን ብሏል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ከንብረት ውድመትና ከሰው ህይወት መጥፋት ጋር በተያያዘ  ተጠርጥረው የታሰሩ ሲሆኑ የእነዚህ ምርመራ እንደሚቀጥል ይታወቃል፡፡ ይሄን እኛም እንከታተላለን፡፡ በሌላ በኩል፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ አባሎቻችንና መሪዎቻችን ታስረውብናል የሚል ቅሬታ እያሰሙ  ነው፡፡ ይህንንም  ጉዳይ ለመከታተል እየሞከርን ነው፡፡
ሰሞኑን ከተፈጠረው ሁከትና ግርግር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን እያጣራችሁ ነው?
አዎ! በእርግጥ ብዙ ውስብስብ ጉዳይ ነው  ያለው፡፡ ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙ ንብረት ወድሟል፤ የብዙዎች አካል ጐድሏል፤ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ሰፊና አሳዛኝ ጉዳት ነው የደረሰው፡፡ ይሄን ለማጣራት አጠቃላይ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ትንሽ ጠለቅ ያለ የምርመራ ስራ እናከናውናለን ብለን አቅደናል፡፡ በሌላ በኩል፤ በፀጥታ ሃይሎች በኩል ህግን ለማስከበር የሚወሰዱ የሃይል እርምጃዎች በተቻለ መጠን ከነገሩ ሁኔታ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆንና ከሚፈለገው በላይ እንዳይሄድ ሃሳብ በመስጠት ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር እንወያያለን:: ሌላው የእስረኞች አያያዝ ጉዳይ ነው:: ስለ ጠቅላላው የእስረኞች አያያዝና ስለ እስራቸው ምክንያት ክትትል ማድረጋችንን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡
የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ ለመንግስትም ሆነ ለህብረተሰቡ ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?
ጉዳዩን የማጣራት ስራ ሲጠናቀቅ የተፈጸመውን ድርጊትና የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ጥፋተኛ የሆኑ ሰዎች ተጠያቂነት መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛ፤ በዚህ ጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ህይወት መልሶ መቋቋም መቻል አለበት፡፡ የሞቱ ሰዎች ህይወት ሊመለስ እንደማይችል የታወቀ ቢሆንም፣ ቀሪ ቤተሰቦቻቸው ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎችም መልሰው መቋቋም እንዲችሉ የተለየ ድጋፍ ይጠይቃልና ያንን ማድረግ ያስፈልጋል::
ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግስትም ሥራ እንደጀመረ እናውቃለን፤ ነገር ግን በተሻለ ደረጃ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ስለሆነ ክትትል እናደርጋለን፡፡ ሦስተኛ፤ ከደረሰው ጥፋት የበለጠ ድጋሚ ጥፋት እንዳይደርስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ በሃገር ውስጥም በውጪ ያሉም ኢትዮጵያውያን በሙሉ የችግሩን ሰፊነት፣ ውስብስብነትና ያስከተለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአመጽ ጥሪ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን በአመጽ ለመፍታት የሚደረገው አካሄድ ነው እንዲህ ያለ ምስቅልቅል ውስጥ በተደጋጋሚ እየከተተን ያለው፡፡ ስለዚህ አደራ በማለት ለማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ፣ ማንኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማራመድ የሚቻልበት እድል በእውነት የተፈጠረ ስለሆነ፣ ከአመጽ መንገድ መቆጠብና የበለጠ ውድመትን የሚያስከትል የአመጽ ጥሪ አለማድረግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በግልጽ ሊያወግዙት ይገባል፡፡ ይሄን ካላደረግንና በተደጋጋሚ ፀብ የያዘ ተቃውሞ የሚቀሰቅስ ከሆነ ጉዳቱ ማቆምያ የሌለው ቀውስ ውስጥ እያስገባን ስለሆነ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡
የህግ አስከባሪዎችም ከነገሩ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ መውሰድና እርምጃዎችን በጥንቃቄ መፈጸም አለባቸው:: ከእስረኞች አያያዝ ጋር በተገናኘም የሰብአዊ አያያዝ ህጎችን የማክበር ግዴታ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ እኛም እነዚህን ጉዳዮች ባለን ውስን አቅም እየተከታተልን ለማሳወቅ ጥረት እያደረግን ነው፡፡



Read 1073 times