Saturday, 11 July 2020 00:00

አስራት ሚዲያ ቴሌቪዥን ሃሰተኛ ውንጀላ ተፈፅሞብኛል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

አስራት ሚዲያ ቴሌቪዥን፣ ከሰሞኑ ከተፈፀመው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ  ስሙ በአጥፊነት መነሳቱን ጠቁሞ  ሃሰተኛ ውንጀላ እንደተፈጸመበት አስታወቀ፡፡
አስራት ሚዲያ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጧቸው መግለጫዎች ላይ ሀገር እንዲፈርስ፣ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ግጭት እንዲነሳ ቅስቀሳና የፅሁፍ ፕሮፓጋንዳ ሰርተዋል ከተባሉት ሚዲያዎች ጋር ስሜ አብሮ መነሳቱ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡
“ባልፈፀምኩት ድርጊትና ባልነበርኩበት ሁኔታ ነው ስሜ በአሉታዊ መንገድ የተነሳው” ያለው አስራት ሚዲያ፤ የአርቲስቱ ግድያ በተፈፀመ እለትም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ ባሉት ጥቂት ቀናት እንዲሁም  ከዚያም በኋላ በአየር ላይ አልነበርኩም ብሏል፡፡  
ከሳተላይት ስርጭት ክፍያና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ከሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ሥርጭቱ መቋረጡን የጠቆመው አስራት ሚዲያ፤ የስርጭቱን መቋረጥም ለአድማጭ ተመልካቹ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዳስታወቀ አመልክቷል፡፡   
አስራት ሚዲያ ቀደም ብሎ በሰራቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ ከሙያዊ መርሆዎችና ከአገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ተፃራሪ ቆሞ የማያውቅ መሆኑን በመጠቆም፤ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም በዜናዎቹና በፕሮግራሞቹ ላይ አዎንታዊ አስተያየትና የድጋፍ ክትትል ሲደረግለት መቆየቱን አውስቷል፡፡
እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ ሚዲያው አፍራሽ  የጦር እወጃ እንዳደረገና የዘር ጭፍጨፋ ቅስቀሳ እንዳካሄደ ተደርጐ መወንጀሉ የህዝቡን ሞራል ያልጠበቀ፣ ሃሰተኛ ሪፖርት ነው ብሏል፤በመግለጫው፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ በሚዲያው ላይ ለተፈፀመው ሃሰተኛ ፍረጃና ስም ማጥፋት ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ይቅርታና ማስተባበያ እንዲሰጡ ጠይቋል - አስራት ሚዲያ፡፡
በአስራት ላይ የተፈፀመው ውንጀላም የሚዲያውን ሚና የሚያቀጭጭ፣ የሃሳብን በነፃነት መግለፅ መብቱን የሚጋፋና ህዝቡ ታግሎ የጣለውን የአፈና  ሥርዓት እንድናስታውስ ያደረገን ነው ያለው አስራት ሚዲያ፤ ይህም ሆኖ ነፃና ገለልተኛነቱን ጠብቆ፣ ህግን አክብሮና የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አስቀድሞ፣ የህዝብን ሰላምና አንድነት እያገናዘበ ሙያዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡       

Read 2824 times