Saturday, 14 July 2012 07:43

ምነው የኢትዮጵያ ህዝብ “ኮረንቲ” መባባል በቻለ!

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)

የዛሬውን የጅማ የጉዞ ማስታሻ ደሞ፤ ለጅማ ዩኒቨርሲቲና ለምርቃት መታሰቢያ በፃፍኩት ግጥም ልባርክ፡፡

አንድ ለእናቱ…አንድ ለአባቱ…አንድ ለአገሩ

አንድ ለእናቱ

አንድ ለአባቱ

አንድ ለአገሩ

በወለደው ልጅ ኩሩ

ለእናቱ አንድ፣ ለአባቱ አንድ፣ ለአገሩ አንድ

አሮጌ ከተማ ማህል፣ እንደ አዲስ እሳት የሚነድ ከርካሳ መንገድ ሳይፈራ፣ አውራ ጐዳና የሚቀድ

አያሌ ትጉ አዕምሮዎች፣ እርግብ ዋኔዎች እሚወልድ የጊዜን ክፉ ተራራ፣ መሀይምነት የሚንድ

ሽለ-ሙቅ የምሁር አብራክ

ድንቁርና እሚያንበረክክ!

ምነው ጐማ በኖረው፣ ከአገር አገር ይዞርበት

ሞዴል ምሣሌ ሆኖ፣ ያንቀላፉ እንዲነቁበት

ሳያዩ የሚያምኑም እንኳ፣ አይተው እንዲማሩበት

ምነው ጐማ በኖረው፣ ባሳየን ሃዋርያነት!

ትቢያ ላይ ችግኝ ቸግኖ፣ ዕንቡጥ አበባ እሚያፈላ

በጠፍ መሬት ዘር አፍርቶ፣ ላገር አብቅቶ እሚያበላ

ክብር ሞገስ አጐናጽፎ፣ ጭኖ የጥቁር ካባ ፈርጥ

አስተምሮ ኩሎ ድሮ፣ ለከተማው ለህዝቡ ጌጥ

ልማድ ቢሆን የባህል ቅጥ

ፈሊጥ ቢሆን የሀገር ቁርጥ

ምንኛ በተገላገልን፣ ከሙሰኛ መሀይም ምጥ!!

ምስኪን ጅማ የቡና እናት፣ ዋ ምንኛ ዐይኗን ትገልጥ?!

እናም ኮሌጅ ማዕደ - ዕውቀት

ህንፃው የሊቅ ደጀ - ሰላም፣ መፃሕፍቱ እንደ ቅኔ ቤት

ቤተ - ትጋት

ቤተ - ትባት

ልጆቹ ቆሎ ተማሪ፣ አድገው ሃዋርያ ብሥራት

አንጐልን በአንጐል እሚቀርጽ፣ ለሀገር አናፂ ብቃት

ሰውን ከፊደል የሚያበቅል፣ ለሀገር የቅኔ ጽናት

ወልዶ አሳድጐ ለባዳ፣ እንዲቀር ብሂሉ እንዲሞት

ወልዶ አሳድጐ ለወገን፣ እንዲሆን የዜማ ሥምረት!

ሲጥር ሲጣጣር ካየሁት

ያንን ነው ኮሌጅ የምለው፣ ያ ነው ለእኔ ትምህርት ቤት!

(ለጅማ ዩኒቨርሲቲና ለትጉሀን ሁሉ)

ሰኔ 2004 ዓ.ም

 

ለቀልድ ያህል

አንዳንድ ተጠቃሽ ምፀቶች ስለጅማ

1ኛው/ ኧረ ስለጅማ አሟሟት እንነጋገር

2ኛው/ መሞቷማ እርግጥ ነው! ይልቅ በእሥላም ወግ

ትቀበር በክርስቲያን ወግ? ነው አነጋጋሪው

***

የወቅቱ ቀመር (Formula)

ሹፌር - ወቅቱን ቀመር ታውቃላችሁ

ተሳፋሪ - አላውቅም፡፡ ምንድነው

ሹፌር - Jimma – Jimma University = Serbo

(ጅማ - ሲቀነስ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ይሆናል ሰርቦ)

***

አንድ አዛውንት “የጅማ መንገድ ሰው ያድግበታል፡፡

ከተማዋ ግን አታድግም፡፡”

መጤ - እንዴት አርገው አደጉ?

አዛውንቱ - በመሬቷ እየፈረዱ!

በኮረኮንቿ እየነዱ!

ከድተዋት እየሄዱ!

***

መንገደኛ - መንገዱ ሁሉ እንዴት እንዲህ ከረከሰ?

ሹፌር - እኛ ወንድሜ፣ ኮረኮንቻችንን በባህላዊ መንገድ እየተንከባከብን ነው! አስፋልትና ዘመናዊ መንገድ አያስፈልገንም!

***

አንድ ምሁር፤

“ህዝቡ ቤቱን አፍርሶ፣ የወር ደመወዙን ዐይኑን ሳያሽ አዋጣ ይሄው መንገዱን አጣ

***

 

የተመራቂዎቹ ድባብ ሞቅ ያለ ነው!

ሠርከስ ጂማ፤ “እንኳን ደስ ያላችሁን” ይዘምራል፡፡

ተመራቂዎቹ፤ ጥቁር ካባ የለበሱ ነጭ፡ አረንጓዴና ቀይ እርግቦች ይመስላሉ! እጆቻቸውን ሲያውለበልቡ ክንፎቻቸውን የሚያርግበግቡ ይመስላል፡፡ ወደ አዲስ ህይወት የሚበርሩና ሆታ! እልልታና ፌሽታ ያጀባቸው አዕዋፋት ደስ ይላሉ! የትኛው ዛፍ ላይ እንደሚያርፉ አይታወቅ እንጂ መብረራቸውን እያሰቡ መደሰታቸው በግልጽ ይታያል!

ሴት ተመራቂዎች ለተሸላሚነት ሲወጡ የሚለገሳቸው ጭብጨባ ከወንዶቹ ከፍ ያለ መሆኑን አስተውዬ፤ “ዝቅ ያለ ቁጥር ካላቸው መካከል የላቀ ውጤት በማምጣታቸው ይሆን ወይስ ሴቶች በመሆናቸው ስለሚታዘንላቸው ወይም በነጥባቸው የተለየ ከፍታ መኖር?” የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሮዬ ተመላልሰዋል፡፡

አንዱን የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፤ “የሴቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምን እንደዛ ሆነ?” ብዬ ጠየኩ፡፡

“በብዛት ወደ ዩኒቨርሲቲው አልገቡም፡፡ ከገቡትም የሚያቋርጡ አሉ፡፡ ቆርጠው የቀጠሉት ግን በጣም ጥሩ ውጤት አላቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን አበረታች ሁኔታ እንዳለ እያየን ነው ለቀጣይ ዓመታት ተስፋ አለ” ብለውኛል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ሥነስርዓቱ ቀጥሏል፡፡ የባችለር ደግሪ፤ የማስተርስ ዲግሪና የሰርተፊኬት መቀበል ሥነስርዓት ተካሄደ፡፡ የሰርከስ ጅማ ባንድ እንኳን ደስ አላችሁ የሚለውን መዝሙር አሁንም  አሰማ ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ!!

በመጨረሻም ፤ ክቡር አቶ ሙክታር ከድር ናቸው የክብር ዶክትሬት የሰጡት፡፡ ለፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ ነው የሸለሙት!

“ፕሮግራሙ በቀጥታ ስርጭት በዓለም ሁሉ እየተሰራጨ ይገኛል”፤ አሉ አስተዋዋቂው፡፡ ፕሮፌሰር ገቢሣ እጀታ ተነሳ ቁመተ ረጅሙ ፕሮፌሰር ከቁመቱ የተነሳ ሽልማቱ በቀላሉ ሊጠልቅለት አልቻለም፡፡ ስለዚህ መቀመጥ ነበረበት፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉ ከመቀመጫቸው ተነስተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ  ምስጋናውን ለክብር እንግዳው፤ ለፕሬዚዳንቱና ለመረጠው ሴኔት፣ ለተማሪዎች ከነቤተሰባቸው አቀረበ፡፡  ከዚያ ንግግር ቀጠለ፡-

“የክብር ዶክትሬት ትልቅ ወግ ነው፡፡ ለማንም የትምህርት ቅርስ ነው፡፡ ለእኔ የህይወት ተስፋ ያገኘሁበት ቦታ መገኘት ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ትጋትንና ትምህርትን ያገኘሁት እዚህ ነው፡፡ ኮሌጅ አልነበረም ያኔ፡፡ ለእያንዳንዳችሁ ለዚህ ት/ቤት ያለኝ ስሜት ጠንካራ መሆኑን ልነግራችሁ ነው፡፡

…እዚህ የተሰበሰብነው ስለ እናንተ ለመስማት ነው፡፡ ሆኖም ለሶስት ወገኖች መናገር የምፈልገው ነገር አለ:- ለወላጆች፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች!

መወለድ ትልቅ ወግ ነው!

ማግባት ትልቅ ወግ ነው!

ተምሮ መመረቅ ትልቅ ወግ ነው!

በመላው ዓለም ኮሌጅ መጨረስ ትልቅ ወግ ነው! ልጄ ዱርዬ ሊሆን ነው! ልጄ ጐዳና አዳሪ ሊሆን ነው! የሚል የወላጆች ሥጋት ያበቃል፡፡

ጭንቀታችሁ የተቃለለበት ጊዜ ነው - ስለዚህ ደስታ ብቻ ሳይሆን የወላጆች ኩራትም ጭምር ነው፡፡

ተማሪዎች ደስታችሁን በጭብጨባ ግለፁ” አለ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡

“አስተማሪዎች ደግሞ እዚህ ኮሌጅ ስትገቡ ያሁኑን ያህል አታውቁም ነበር፡፡

እናንተን ተማሪዎቹን በመፍጠራቸው እንኳን ደስ አላቸው ሊባሉ ይገባል!! የእያንዳንዱን ልጅ ፊት “ስታዩ የሚገባኝን አድርጌያለሁ ወይ?” በሉ፡፡

ለኮሌጅ ምሩቃኑ የምለው ፤ዞራችሁ ስታዩት ኮሌጅ ባላችሁ ጊዜ ትርጉም ያለው ኑሮ እና የሥራ ልምድ አሳልፋችኋል ወይ? ትምህርት ብቻ ሳይሆን ከጓደኞቻችሁ ጋር ሁነኛ ግንኙነት ነበራችሁ ወይ? የብዙ Connection (ግንኙነት) ቦታ ነው ትምህርት፡፡ ዛሬ አላለቀም፡፡ ዕድሜ ልክም አያልቅም፡፡  መሠረት ያለው ስልት ይዛችኋል ወይ? ተስፋ የማደርገው ማንነታችሁን አሁን አውቃችሁ ይሆናል ብዬ ነው፡፡ ማንን መሆን እንደምትፈልጉ አላማ አድርጋችሁ ይሆናልም!! ይሄ መሠረታችሁ ነው፤ ኩሩበት!

ይሄ የኮሌጅ መማር ዕድል ውሱን ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን የመሰለ አገር ውስጥ እንኳን የኮሌጅ ምሩቃን 40% ናቸው፡፡ ከ200 ዓመት በተጀመረ ኮሌጅ!...ዋናው ነገር ግን ሰርቲፊኬት ማግኘት ሳይሆን ምን ልታደርጉበት እንደምትችሉ ካወቃችሁ ነው!

ሀገር የምትገነባው በሰው ጉልበት ነው! በሀገር ሰው ጉልበት ነው! የውጪ ሰው መጥቶ ሀገር ሊገነባ አይችልም! ትምህርት ያለው፣ ስልት ያለው ጉልበት ነው፡፡ መንግሥት ይሄንን ልብ ማለት አለበት፡፡ ይህንን አሳስባለሁ!

ያለው ሁኔታ ወጣቱን ወደ ሌላ አገር መሄድ እንዳያስመኘው መደረግ አለበት!

ከኮሌጅ መመረቅ ክብር ሊሆን ይገባዋል! ለሀገር የሚበጅ ምሁር የሚፈልቀው ከናንተ መካከል ነው! ለወገን መፍትሔ የሚፈልቀው ከናንተ መካከል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ መሪ የሚፈልቀው ከኮሌጅ ምሩቃን ነው! የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እየተሻሻለ ከሄደ የሀገር መሪዎችም የሚፈልቁት ከዚህ ውስጥ ነው! ለራስ ኑሮ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ለወገን ትረፉ!”

ዶ/ር ፍቅሬ ለሜሣ፤ ለክቡር ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ፣ ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦች እንዲሁም ለመምህራን ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በመጨረሻ የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ሙክታር ከድር ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዙ፡፡ የክብር እንግዳው ረዘም ያለ ንግግር አደረጉ፡፡ የንግግራቸው መሠረታዊ ጭብጥ ሀገሪቱ ላለችበት የልማትና የትራንስፎርሜሽን ሂደት ምሩቃኑ ትልቅ ሚና እንዳላቸው አጽንኦት ያደረገ ነበር፡፡

ምሩቃኑ ወደ ፕሮግራሙ መጨረሻ ላይ የተቻኮሉ ይመስላሉ፡፡ ዕውነት አላቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው ከሩቅም ከቅርብም ከንጋቱ 10 ሰዓት ጀምረው ዩኒቨርሲቲው ቅጽር ግቢ ታድመው ነው የቆዩት፡፡ አሁን ከረፋዱ 5.30 ሆኗል፡፡ ቁርስ አልበሉም፡፡ ምሣ ገና አለ፡፡ እቅፍ አበባ አልተረካከቡም፡፡ በደስታ ተፍለቅልቀው አልተቃቀፉም፡፡ ፎቶግራፍ አልተነሱም፡፡ ግቢውን ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት፤ በተንጣለለው መስክና አንገታቸውን በግርማ ሞገስ አስግገው አምረው ከተሰደሩት ህንፃዎች መካከል፣ ሽር ሽር አላሉም፡፡ በዘመናዊ ሞድ በተሰራው የተማሪዎች ሻይ ቤት ተቀምጠው አሮጊት እናት፣ አረጋዊ ሽማግሌ፣ ታናሽ ወንድምና እህት ገና በሐሴት አልተገባበዙም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ በፊት የሚደረግ ንግግር በተለይ የባለሥልጣን እጥር ምጥን ቢል ውሉንም፣ ግቡንም እንዳይስት ይረዳል፡፡ በህዝብ ግንኙነቱ ተወካይ በአቶ ካሣሁን ገዛኸኝ ስለ ፕሮፌሰር እጀታ ገቢሣ የቀረበው ትረካ ጥበባዊ አቀራረቡ ይማርካል፡፡ ልብ ይነካል፡፡ ራሱ ፕሮፌሰር እጀታ ገቢሣ የራሱን ታሪክ ሲሰማ በሀሴት ዕንባ ሲጥለቀለቅ ፊቱ ቆሜ አስተውያለሁ፡፡

በአጠቃላይ ፕሮግራሙ ከተለመደው ጥቂት የረዘመ መሆኑንና አንዳንድ ንግግሮች አላግባብ መንዛዛታቸውን እንደታዳሚ ታዝቤአለሁ፡፡ አንድ ወዳጄ “አበሻ ብርጭቆ ካልተሰበረ፣ መጠጥ ካልተደፋ፣ ሰው ካልተጨናነቀ፣ አዳሜ ካልተተረማመሰ፣ ሙሽራ ካልዘገየ፣ ምግቡ ተርፎ ካልተመለሰ፣ ምኑን ድግስ ተደገሰ?!” ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ይሄም ያባት ነው፣ ቤት ያፈራው ነው፡፡ ይሄን ዓይነት አስተሳሰብ ባለበት አገር፤ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማስመረቂያ ሥነስርዓት የተዋጣና የደመቀ ነው ማለት አግባብ ያለው አድናቆት ይመስለኛል!

ከምሩቃኑ መካከል የምህንድስና ተማሪ የሆነውንና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚውን፤ 4 ነጥብ በማምጣት የሰቀለውን፤ የትግራዩን ልጅ ህሩይን አግኝቼ አነጋግሬው ነበር፡፡ ለዐይን ቅልል የሚል፣ ቀጭን፣ አጭር፣ ባለመነጽር ልጅ ፣ካባውም  ሆነ መነሳንሱ የከበደው አይመስልም፡፡ ጓደኞቹ ሁሉ “በሆታ ህሩይ! ህሩይ !ህሩይ!” እያሉ ነው ያጀቡት ለሽልማት ሲነሳ፡፡ ኃይለኛ ቲፎዞ ያለው ልጅ ነው ማለት ነው አልኩኝ በሆዴ፡፡ ምናልባት ማህበራዊ ህይወቱም አሪፍ ሳይሆን አይቀርም!

“ገርልድ ፍሬንድ አለህ ህሩይ?” ብዬ ጠየኩት፡፡

“የለኝም”

“ልትይዝ ታስባለህ?”

“ከእንግዲህ አዎ”

“ኤሌትሪካል ኢንጂነሪንግ ከባድ ነበር?”

“አዎ! በተለይ ይቺን አራት ነጥቤን ለመጠበቅ በጣም ነው የታገልኩት”

“ኢትዮጵያን የምትለወጥ ይመስልሃል ወደፊት?”

“በአንድ በእኔ 4 ነጥብ እንዴት ብላ ትለወጣለች - ከሌሎች ጋር ሆኜ ነው እንጂ!” ብሎኛል፡፡ ወደፊት ልንደዋወል ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን፡፡”

ግቢውን ተዟዙረን አየን፡፡ 5000 ሰው ይይዛል የተባለውን በመሠራት ላይ ያለ አዳራሽ አይቼ ገረመኝ! ወደመሬት ሁለት ፎቅ የሚወርድ ፓርኪንግ ቦታ ሲቆፈር ተመለከትኩ፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ማዕከሉን አየሁ፡፡

የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎችን ሁሉ በወፍ በረር ጐበኘሁ፡፡

አስፈላጊ የህትመት ማቴሪያሎችን ካሣሁን ከቢሮው ሰጠኝና ወደምሣ ሄድን!

***

ከሰዓት በኋላ በህዝብ ግንኙነት ወዳጄ አማካኝነት ሁለት ወዳጆች አገኘሁ፡፡ ጥሩ አንባቢዎች ናቸው፡፡ “የጠፋው በግ ተገኘ!” አልኩ በሆዴ

አንደኛው - “አንተን የማውቅህ ‘የእሾክ ላይ ሶረኔ’ በሚለው ግጥምህና ‘ነገር የገባት ሰጐን’ ብለህ ለጥሩነሽ ዲባባ በፃፍከው ግጥምህ ነው” ብሎኝ ነው ጨዋታ የጀመርነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ጉዳይ አንስተን ተወያየን፡፡

እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ (አንደኛው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ስለጥሩነሽ ዲባባ ሲገልፁ “ነገር የገባት ሰጐን ናት” ብለዋል አሉኝ፡፡ “ግጥም የሚያነብ ጠቅላይ ሚኒስትር ካለ መቼም የሚያስገርም ነው፡፡ እርግጥ ራሱ ገጣሚ የሆነ የሀገር መሪም አለ” ተባባልን! ከአንባቢዎቹ ጓደኞቼ ጋር ስለ Subconscious (ስለ ድብቅ የአዕምሮ ጓዳ)ስለ ፀጋዬ ገ/መድህንና አንትሮፖሎጂ፣ እንዲሁም ስለ ethnocentrism ፣ ስለ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞና ስለ ዕምነት፣ ተወያየን፡፡

“ስለ ታየ ፈረቀሳው፣ የአርሲዋ እመቤት የማውቀውን እንድነግረው ጋሽ ፀጋዬ ይጠይቀኝ ነበር” አልኳቸው፡፡ ከቀኛዝማች ታየ መሸሻ ጋር አብረን ማዕከላዊ ታስረን ስለነበር ነው! ‘ስለ ነገም ሌላ ቀን ነው’ (Gone with the wind) እና ስለተለያዩ መፃሕፍት፣ ስለ አዲስ አድማስና ስለ አንባቢው ትውልድ… ማነስ፣ ለመገንባት ምን መደረግ እንዳለበት ….ምኑ ቅጡ! ያቺን አንድ ከሰዓት በወርዷም በቁመቷም አጣበን ብዙ ነገር አነሳን ጣልን! ወደፊት በሰፊው እንደምንገናኝና መጽሐፍ መለዋወጥ እንደሚኖርብን አሰመርንበት፡፡ በጣም ነው ደስ ያሉኝ፡፡ መጽሐፍ አንባቢ ልዩ ነብስ ነው ያለው ፡፡ አንባቢያን ነብስ ለነብስ የሚናበቡት ለዚህ ነው ተመሳሳይ ዌቭ ሌንግዝ ለመፍጠር ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ በቅጽበት ውስጥ ዘለዓለምን፣ ከዘለዓለም ውስጥ ቅጽበትን ማግኘት አይገዳቸውም!

ማታ እራት ግብዣ ስላለብኝ ተሰናብቻቸው ወደ Central Jimma Hotel ሔድኩ!

ሴንትራል ሆቴል ከምረቃው ጋር የተያያዙ እንግዶችና መምህራን፤ በዋናነት ፕሮፌሰር ገቢሣ እጀታ አለ፡፡ ምግብ አልተጀመረም፡፡ ቢራ ግን ይታያል፡፡

ራት ግብዣው ላይ ተገኘን! ቢፌ! እኔ፣ ካሣሁን፣  ታሜና አስማማው ተቀመጥን፡፡ እየበላን  እየሳቅን ተወያየን፡፡ የክልል ቲቪ እና የፌዴራሉን ቲቪ አወዳድረን ሳቅን! ዕውነታው

መራርም ቢሆን መሳቁን ችለንበታል! ዕድሜ ለኑሮና ለልማድ!

ከዚያ አንድ እዚሁ ዩኒቨርሲቲ የሚሠራ ዶክተር መጣ፣ “ዐቢይ” ነው የሚለኝ እሱ፡፡ የዳንግላ ልጅ ነኝ አለ - ዶሮ የሚሸጥበት ከተማ ይለዋል - ልዩ መንደሩን፡፡ በግጥሜ እንደሚያውቀኝ ነግሮኛል፡፡

ከዚያም ያለፈ እንደሚያውቀኝ ግን የሚከተለው ንግግራችን አሳይቶኛል:-

“ዕድሜ በምን ይለካል?” አለኝ፡፡ አመነታሁ ለመመለስ፡፡

አንድ ታሪኬን ልነግርህ ነው፡፡ የኢህአፓ መዋቅር ከላይ ወርዶ - ቀጠና፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ይወርዳል፡፡ እኔ ታች ደረጃ ነበርኩ፡፡ ያኔ 8ኛ ክፍል ነበርኩ -  ዋና ሥራዬ ወረቀት ማቀበል ነው፡፡ ተቀባይ ነበረኝ፡፡ በዚህ ሥራዬ ለተወሰነ ጊዜ concentration camp (ማጐሪያ እሥር ቤት እንደማለት ነው) ታስሬ ነበር፡፡ ስለዚህ ለእኔ፤ ዕድሜ የሚለካው በአቀባይና በተቀባይ መካከል ባለው ጊዜ ነው!

“ዋው!” አልኩ እንደ what’s up! ከአሜሪካ እንደተማርኩት!

ቀጥሎ፤ “በአሁኑ ጊዜ ጐጃምን የሚመለከተው ድርጅት ወደኔ መጥቶ ‘ለምን አባል አትሆንም?’ አለኝ፡፡”

“አይ ወዳጄ እኔ አንድ ጊዜ ድንግልናዬን በወጣትነቴ ለኢህአፓ ሰጥቻለሁ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ጋለሞታ ነኝ - አላገባም!!” አልኩት፤ አለ፡፡ ሳቄን ለቀቅሁት፡፡

“አዎ! የልጅነት ፍቅርህን ለአንድ ድርጅት ከሰጠህ አለቀ! ከዚያ ጋለሞታ ትሆናለህ!” አለኝ፡፡ ብዙ የሚያስቁ ነገሮችን አወራን፡፡ “መሸብኝ ልሂድ” ብሎ ተሰናበተኝ፡፡

ቀጥለው ሁለት ዶክተሮች አጠገቤ መጡ፡፡

ውጪ አገር የአካዳሚውን ማህበረሰብ ወደ ከተማ አያስጠጉትም፡፡ ምናልባት ልጆቹን ከተማው እንዳይማርካቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከማንዴላ ትውልድ ሥፍራ አጠገብ ያለው ግራሃምስ ዩኒቨርስቲ “አልኳቸው፡፡ ጅማ ግን ማህል ከተማዋ ውስጥ ሌላ ከተማ የሚያህል ደማቅ ከተማ አብቅላለች!” አልኳቸው፡፡

“ጅማ ዩኒቨርሲቲ የከተማዋ መሠረት እና የከተማው ሞቅታ ነው የሚባለው ዕውነት ነው፡፡ ዋናው የዩኒቨርሲቲው ባህሪ፤ ተማሪዎቹ ከማህበረሰቡ ውስጥ ሆነው መማራቸው ነው፡፡ ስለዚህ ተጨባጭ ዕውቀት ይዘው ነው የሚወጡት!” አሉኝ፡፡ ሌላም የአካዳሚ ጉዳዮችን አነሳን፡፡ ቀጥዬ ፕሮፌሰር ገቢሳን ማግኘት ስላለብኝ ወደሱ ሄድኩኝ! አንድ ዋና ጥያቄ ነው የጠየኩት፡፡ መሀመድ አልሃቢብ ወይም አባ ሚልኪ የሚባል ወዳጅ አለኝ፡፡ የዩኒቨርሲቲ እኩያዬ ነው- ዘመነኛዬ ነው፡፡ አብረን ለዩኒቨርሲቲው ኳስ እንጫወታለን፡፡ እሱ ቅርጫት ኳስ እኔ መረብ ኳስ፡፡ ጮሌ ተጫዋች ነው Play maker ነው! ተግባቢና አስተዋይ፣ ተጨዋች ነው፡፡ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች ሲሰራ ቆይቶ አሁን ኢትዮጵያ ሠፍሯል መሰለኝ፡፡ የአባጅፋር ቤተሰብ ነው፡፡ ጅማ የአባጅፋር ቤተመንግሥትን የሚመለከት ጉዳይ ገጥሞት እንደመጣ በነጋታው የአባጅፋርን ቤተሰብ ልጠይቅ ሄጄ ተረድቻለሁ፡፡ አባሚልኪ ከወንድሞቹ ጋር ሴንትራል ጅማ ሆቴል መጥቶ አገኘሁትና ከፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ ጋር ራት እንደሚኖረኝና ኢንተርቪው ላደርገው እንደምፈልግ ስነግረው፤

“ነቢይ፤ ገቢሳን እኮ አቀዋለሁ፡፡ እንዲያውም ቅርጫት ኳስ አብረን እንጫወት ነበርኮ” አለኝ፡፡

“The world is a village አልኩኝ (ዓለም እንዴት ጠባብ ናት?) ይገናኛሉ የማይባሉ ሰዎች እንዲህ ይገጣጠማሉ”

“እስቲ ስለቅርጫት ኳሱ ጠይቀው?” አለኝ

“በጣም ደስ እያለኝ ነዋ የምጠይቀው” ብዬው ተለያየን፡፡

ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታን፤ “መሐመድ አልሃቢብን ታውቀዋለህ?” ብዬ ጠየኩት፡፡

“አዎን አውቀዋለሁ፡፡ ዛሬ አግኝቼው ነበርኮ”

“ለኔም ወዳጄ ነው ስፖርት ትወድ ነበር?”

“አዎ - ቮሊቦልና ባስኬት እጫወት ነበር፡፡”

“ለኢንተር ኮሊጌት?” አልኩት፤ በዚያ ዘመን በኮሌጆች መካከል የሚደረገውን ግጥሚያ አስታውሼ፡፡

“ታዲያሳ!” አለኝ በኩራት፡፡

“ጥሩ ትጫወት ነበር?”

“ለናሽናል ቲም(ብሄራዊ ቡድን)ተመርጬ ነበር” አለኝ፡፡ ወደ መኝታ ክፍሉ መሄድ ነበረበትና ቸኮለ፡፡ ደህና እደር ተባብለን ተለያየን!

በነጋታው፤ ከአዲስ አበባ አንድ ወዳጄ፤ አግኘው ያለኝን ወንድሙን ለማግኘት ሸዋ በር ወደሚገኘው ታሬ ክርስቲያን ሥጋ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገልኝ፡፡ ከዚያ “ሥራ እንዴት ነው?” አልኩት፡፡

“ምንም አይል” አለኝ፡፡ ለእንግዳ ሰው የማይከብድ፣ ተግባቢ ልጅ ነው!

“ቁርስ እንብላ ና” አለና ይዞኝ ወደ አንድ መለስተኛ ቡና ቤት ሄድን፡፡ መንገድ ላይ “እንዴት ነው የዚህ አገር መንገድ?” ባለፈውም ስመጣ እንዲህ ጐርበጥባጣ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ብሶበታል?” ብዬ ጠየኩት ፡፡

“ባይሠራም ያስኬዳል” አለኝ፡፡ ሳቅሁኝ፡፡ “ስለ ጅማ መንገዶች የጠየኩት ሰው ሁሉ አንድ አንድ ኮሚክ ነገር ይነግረኛል” አልኩት፡፡

“ምን ያርጉ የምታየው አደል?”

“እዚህ አገር ባጃጅ በዛ ልበል?!“

“በጣም መዐት ናቸው፡፡ ሰውም በዝቷል፡፡ በየጉራንጉሩ ስለሚገቡ በጣም ጠቅመውታል፡፡

ከወሊሶ ድረስ እየመጡ ይሠራሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ዋጋቸው አልቀመስ እያለ ነው!”

“የበሬ ዋጋስ እንዴት ነው - አዲሳባ ወንድምህ ውድ ሆኗል ይለኛል”

“ደህና ነው - ችግሩ የህዝቡ የመግዛት አቅም መዳከም ነው!”

“ቫትስ?”

“ትልልቅ ሆቴል ጀምረዋል፡፡ እኛጋም ሊጀመር ነው!”

ጥሩ ቁርስ በላን፡፡ ቢራም ጠጣን፡፡

“ሥጋ ቤትህን ታሬ ያልከው ታረቀኝ ለማለት ነው”

“እንደዛ ነው“

“አግብተሃል? ልጆች አሉህ?”

“አዎን፡፡ ሁለት ልጆች አሉኝ”

“ት/ቤት ገብተዋል? ባካባቢህ ት/ቤት አለ?”

“ብዙ የግል ት/ቤት አለ”

“መንገድ አትሠሩም እንጂ በትምህርትስ ምንም አትሉም! ይሄ ሆቴል ማን ይባላል?”

“ዱሮ ‘እኛ ለእኛ’ ነበር አሁን ‘እናት ጐጆ’ ተብሏል፡፡”

ስምን መልዐክ ያወጣዋል  አልኩኝ በሆዴና ሳቅሁኝ፡፡

“ሃዋሳ እና ወደ ደቡብ በጠዋት ጥሬ ሥጋ ይበላል - ከዛ ቢራ ወይም ድራፍት ይጠጣል፡፡ እዚህም ድራፍት በጠዋት ይጀምራል?”

“በጣም እንጂ! እንዲያውም ከማታው የጠዋቱና የቀኑ ጠጪ እየባሰ መጥቷል!”

ወደ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ አዲስ የሚሠራውን ሆስፒታል፣ የተማሪዎችን መኝታና የህፃናት መዋያውን ማየት ስላለብኝ ተደወለልኝ፡፡ ከሚጥመው የታሬ ጨዋታ ተለይቼ ተነሳሁ፡፡ እግረ መንገድ ፈረንጅ አራዳን እያሳየኝ መርካቶ ወርጄ ባጃጅ ተሳፈርኩ፡፡

ከመርካቶ ወደ ሴንትራ ሆቴል ለመሄድ ባጃጅ ውስጥ እንደገባሁ ፤

“አቦ ዝናቡ በዛ” አለ ከጐኔ የተሳፈረው ጅሜ!”

“ተው እንጂ! ይሄ ሁሉ ዱአ ተደርጐ የመጣ ዝናብ”

“ዱአ ያረግነው አምጣልን ብለን ነው እንጂ አብዛብን ብለን ነው እንዴ?!” አለ፡፡

ወይ እነዚህ ሰዎች እያልኩኝ በሆዴ ከባጃጅ ወረድኩ፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ የተሠራውን ሆስፒታል አየሁ፡፡ የዛሬን አያደርገውና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል (የዱሮው ልዑል መኰንን ሆስፒታል) በልጅነቱ እንዲህ ቻይናዎች እንደሠሩት ሆስፒታል ያምር ነበር፡፡

“ሆስፒታሉ በየክፍሉ ኦክሲጂን አለው” ሲሉኝ ፤ እሰይ ጅማ ገና ዛሬ በሣምባዋ ኦክሲጂን ልትተነፍስ ነው አልኩኝ፡፡ (የዱሮ ሆስፒታሏን ጆሮ ይድፈንልኝ!) መማሪያም ማከሚያም ነውና ለሜዲሰን ተማሪዎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ጅማም ትታከምበታለች፡፡ (የባለሥልጣኖቿ ዓይን እንዳይቀላ እንፀልያለን ወይም ዱዐ እናረጋለን)

ቀጥሎ የህፃናት መዋያዋን አየሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በቅጥር ግቢው መኖር ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውን እዚህ መዋዕለ ህፃናት ውስጥ የማስተማር ዕድል አላቸው፡፡ የታደሉ ልጆች! እዚህ ይማራሉ፡፡በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡ ምናልባትም ዩኒቨርሲቲ ይሆናሉ፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአሮጌ ከተማ ውስጥ አዲስ ከተማ የሚያዋልድ ዩኒቨርሲቲ ነው (Midwifing another new baby – city እንደማለት ነው) ማደሪያ መኖሪያዎቹን ሁሉ ካየሁ በኋላ ጉዳዬን ጨርሼ ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ወጣሁ፡፡

ከግቢው የወጣሁት ከአባጅፋር የልጅ ልጅ ልጆች አንዱ ከሆነው ከላይ ከጠቀስኩት የአባ ሚልኪ ወንድም ከፔሌ (አብዱል ከሪም) ጋር ነው፡፡ በዚህ ቀን ወደ አዲስ አበባ መመለስ ሲኖርብኝ የአባጅፋርን ቤተሰብ ሳላይ አልመለስም ባልኩት መሠረት እሱም “አንተ ከቀረህ የአጋሮ ጉዞዬን እሰርዛለሁ” ብሎ አመቻችቶ ነው ወደ እኔ የመጣው፡፡

“ዛሬ ምሣ እምጋብዝህ አባጅፋር ሬስቶራንት ነው! የባህል ምግብ!” አለኝ፡፡

“በጣም አሪፍ! እኔኮ የባህል ሰው ነኝ!” አልኩት፡፡

መናኸሪያ አካባቢ በሚገኘው አባጅፋር ሬስቶራንት ደረስን፡፡ እንደ ባህሉ መሬት ላይ በተመጀለሱት መቀመጫዎች ላይ ተቀምጠን፤ ምግቡ በትሪ መጣ፡፡ ምን ምን እንደሆኑ ምግቦቹ ጠየኩት፡፡ ፔሌ በጣም የማስረዳት አቅም ያለው፣ ዕውቀቱን የማይሰስትና ሰው ስለጅማ እንዲያውቅ ሳይታክት የሚጥር ሰው ነው! እኔ “አንተኮ Mayor of Jimma መሆን ይገባሃል- ነህ ከንቲባ” እለዋለሁ፡፡

የቀረቡት ምግቦች ዓይነት በዓይነት ናቸው፡፡ ማህበራዊ ናቸው፡፡ የሚበሉትም ክብ ተሠርቶ በማህበራዊ መንገድ ነው፡፡ ሞፎ፣ ሐኒድ፣ ሱኩሚ (በዝነኛ ስሙ ሆላንዶ/ሆላኮ)፣ ጩጳ፣ ጉደሬ፣ ዶቆ (በደቡብ ዝነኛ ስሙ “ዳጣ” ወይም “ቆጭቆጫ”) ይባላሉ፡፡ ስለጥፍጥናቸው ከመናገር መቅመስ ይሻላል ብዬ ልለፈው!

ከምሣ በኋላ ወደ አባጅፋር ቤተሰብ ሄድን፡፡ ቤተሰቡን በአንድ ሀረግ ለመግለጽ “ፍቅር ነው” ማለት ይበቃል፡፡ አያሌ ጉዳዮች ላይ ተወያየን፡፡ እኔም ያነበብኩትን ያህል አጫወትኳቸው፡፡ “ይሄኮ ትልቅ ትምህርት ነው! እግዚአብሔር አንጐልህን አሁንም ያስፋልህ” አለኝ ፔሌ፡፡ ዱሮ እነ አባቴ ሲመርቁ “ትምህርትህን ይግለጽልህ” ይሉ ነበረ፡፡ ፔሌ እንደዛ ያለ ነው የመሰለኝ፡፡

ጽሑፌን የማሳርገው የእነ ፔሌ እናት ዱዐ ላይ ሲመርቁ በሚሉት አባባል ነው፡፡ ይመርቁን ይመርቁንና በመጨረሻ እያንዳንዱ ታዳሚ በተለምዶ እጁን እየተሳሳመ የሚበራረክበት ሁኔታ ሲደርስ ፤ እማማ ያንን ያሳጠሩበት መንገድ አለ፡፡ “እጅ ለእጅ ተያያዙ” ይላሉ፡፡ ከዚያ “ኮረንቲ! ኮረንቲ! ኮረንቲ!” ይላሉ፡፡ እኛም እንላለን፡፡” አንድ እንሁን! ማለታቸው ነው!!

ምነው የኢትዮጵያ ህዝብ “ኮረንቲ” መባባል በቻለ! ምነው እንደ እማማ ያሉ መሪዎች በኖሩት!

- ተፈፀመ -

 

 

Read 2685 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:46