Saturday, 04 July 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አደን፤ ድሮና ዘንድሮ!
ድሮ ሰው ለቅሞና አድኖ ነበር የሚኖረው፤ ታዲያ ከእነርሱ የወረስነው ነው አሁንም የምናድነው?
አድኖ ሲባል ብዙ ሮማንቲሳይዝ አታድርገው.፤ የሚያድነው አሳ፣ አይጥ፣ ቅንቡርስ፣ ወፍ ምናምን ነው፤ አንበሳና ዝሆን አይመስለኝም፡፡ ለምን አልመሰለኝም? በሌላ ጊዜ. እንደውም ብዙ ጊዜ የሚያድነው ቅንቡርስና ትላትል ስለነበር ለቅሞና አድኖ ከማለት ለቃቅሞ ቢባል ይሻል ነበር፡፡ እያደር ግን አንበሳና ዝሆን ማደን ተጀመረ፡፡ አሁን ላይ የአደን አላማ የተለየ ነው፤ ለሃብታሞቹ መዝናኛ, ጊዜ ማሳለፊያ ነው፤ ለድሃው ደሞ የገንዘብ ምንጭ፡፡
ድሮ ግን አደን የክብር ምንጭ ነበር፤ የክብር የዝና፣ የስም ምንጭ ነው፤ አሁንም ቢሆን ክብር፣ ዝና፣ ስም የሰው ልጅ ፍላጎት ነው፤ ቅርፁ ግን ከዘመን ዘመን ይለያያል:: ዝና፣ ክብር፣ ስም የሚገልጠው ሌሎች ሰዎች ስላንተ ያላቸውን አመለካከት ነው፤ በአብዛኛው ሰው ዘንድ የላቀ ዋጋ ማግኘት ነው፡፡
የአብዛኛው ሰው የሃይል መገለጫ ነው፤ በአብዛኛው መለኪያ የላቀ ዋጋ መቀናጀት. ግን በጣም ተሰባሪ ዋጋ ነው፡፡ “አንተ ከገባህማ ምኑን ተቀኘሁት” ነው ያሉት የኔታ፣ የኔቢጤው ሲያደንቃቸው፡፡
የአብዛኛው ሰው መለኪያ ደሞ እንደየ ጊዜው ይለያይ ነበር፤ በአንድ ወቅት ግን ዋናው መለኪያ የራስን ጥቅም ከጥቃት የመጠበቅና የመከላከል አቅም ነው መከበሪያው፤ ይህን ደሞ ማሳየት ተገቢ ነው:: ሪስክ የመውሰድ ደፋርነትህ፣ ጥቃትን ለመበቀልና ለመከላከል ያለህ ዝግጁነት ነው የላቀ ዋጋ ያለው፡፡. ለሚስት መረጣ ይረዳሃል፤ ትከበርበታለህ.፤ማንም አጥርህን አይነቀንቅም፡፡
አደን ታዲያ አቅምህን የማሳያ መንገድ ነው፤ በተለይ መኳንንት ስትሆን ካንተ አደን ይጠበቅብሃል፡፡ መኳንንትነት በደም ቢተላለፍም ማንም ያላከበረው መኳንንትነት ፋይዳ የለውም፤ ስለዚህ አቅምህን ማሳየት አለብህ፤ አደን መውጣት፡፡ እየቆየ ግን ልምድ ባህል ይሆናል፤ የእንግሊዝ መኳንንት ጥንቸልና ቀበሮ በውሻ ያድናሉ፤ያሳድናሉ ቢባል ይቀላል፡፡
(ከሙሉጌታ መንግስት አያሌው)

የኦቦ ዳውድ ሃሳብ!
ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በቅርቡ ከአርትስ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያ የአሃዳዊና ፌዴራላዊ ቅይጥ አወቃቀር ይሻላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፤ “ሰበር ዜና!” ነው፡፡ “ዩኬን ውሰደው አሁን፤ዩናይትድ ኪንግደም፤ ዌልስ፤ አየርላንድ፤ ስኮትላንድና ዋነኛው ኢንግላንድ፡፡ ይሔ ነው ዩኬን የፈጠረው፤ ፌዴሬሽን ነው፡፡ መንግስታት ናቸው እነዚያ፤ ራሳቸውን የቻሉ ፓርላማ አላቸው፤ ካቢኔ አላቸው፤ አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት፡፡”
ኦቦ ዳውድ ኢብሳ የተመኙትም፤ ዩኬ የምታራምደው የፌዴራል ሥርዓት ነው ከሚለው መነሻ ስለ መሆኑም መገመት ይቻላል፡፡ እውነታው ግን ምን ይሆን? በአጭር ቃል ዩኬ ፌዴራሊስትም አሃዳዊም አይደለችም፡፡ ኦቦ ዳውድ “ፌዴሬሽን” የሚለውን ቃል ከየት አምጥተው እንደተጠቀሙት ግራ ያጋባል፡፡ ይልቁን በዩናይትድ ኪንግደም ሕገ መንግስትና አወቃቀር ላይ ጥናት የሚደርጉ አያሌ ምሁራን፤ ለዩኬ መንግስታዊ አወቃቀር የአንድነት መንግስት(...Union State...) የሚለው ስያሜ ሥርዓቷን የበለጠ ይገልፃዋል ብለው ያስባሉ፤ እናም ዩኬ “Union state” ነች፡፡
በዚህ ዙሪያ  ከሁለት መፅሐፍት ያገኘሁትን መረጃ እንደወረደ ላስቀምጥላችሁ፦
እንግሊዛዊው Colin Turpin እና ስኮትላንዳዊው Adam Tomkins ከላይ በጠቀስኩት መፅሐፋቸው በአራተኛው ምዕራፍ፣ በ“Devolution and the structure of the UK” ንዑስ ርዕስ ሥር ያስቀመጡት ይህን ይመስላል፦
“It is used to be generally thought that the UK has a unitary constitution, like those of France, Italy, and Japan,The Netherlands, Sweden and New Zealand and unlike the federal constitutions of Germany, Switzerland, the US, Australia, Brazil, Canada, India, Nigeria and the Russian Federation. However, it may be that the better view is that the UK has a Union constitution that is neither straightforwardly unitary nor systematically federal in character…”
ፕሮፈሰር Robert Schutze ደግም ገና በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ፤ ባነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደዚህ ይላሉ፦
“The United Kingdom is decidedly not a federal State. Centered on one –sovereign—Parliament, its legal structure is that of a unitary state; yet unlike classic ‘Unitary States’, it houses not just one but ‘four nations’ within its constitutional borders. The United kingdom is therefore sometimes described as a ‘Union’ or more often it is characterized as a ‘Union State’”
ዝርዝሩን ወደፊት የማነሳው ቢሆንም ‘Union State’ ሲባል መዋቅሩ የአሃዳዊውና የፌዴራል ቅይጥ ስለመሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ፕሮፌሰር Stephen Terney “The Paradox of Federalism, 2012” መፅሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ “Union State” የሚለውን ስያሜ ያገኘውን ቅይጡን የዩኬ መንግስታዊ አወቃቀር “Fedralism in a Unitary State” በማለት ይጠራዋል::
 እዚያው መፅሐፍ ውስጥ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ሉአላዊ ሥልጣንን ሳያጎናፅፍ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣንን ከማዕከላዊው ከዩኬ መንግስት ወደ ንዑስ መንግስታት የሚሸነሽነውን “ዲቮሉሽን”ን ፕሮፈሰሩ “The poor cousin of Federalism” በማለት ይገልፀዋል፡፡ “Devolution” የፌዴራሊዝም የአጎት ልጅ መሆኑ ነው፡፡
ለመሆኑ ዩናይትድ ኪንግደም ለምን ከሁለት የወጣች “Union State” ሀገር ተብለ ልትጠራ ቻለች? ኦቦ ዳውድም በምላሻቸው የጠቀሱት “Devolution” ምንን ያመለክታል? እውን የዩኬው “Devolution” ኦቦ ዳውድ እንደተነተኑት፣ ለአራቱ የዩናይትድ አባል ኔሽንስ ዘላቂ ሉዓላዊነትን (sovereignty) ያጎናፀፈ ነው? የቀጣዩ ፅሑፌ ይዘት የሚያተኩርበት አንኳር ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻም በኦቦ ዳውድ ኢብሳ ቃለ ምልልስ ላይ ተንተርሰን “ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ለኢትዮጵያ “የአሃዳዊና ፌዴራላዊ ቅይጥ አወቃቀር ይሻላል” አሉ!! የሚል ሰበር ዜና ብንሰራ ጥፋተኞች አይደለንም ማለት ነው። ነገር ግን ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ሌሎችን በአሃዳዊነት “እየፈረጁ”፣ በተቃራኒው አያሌ የአሃዳዊ አላባዎችን የያዘውን የዩኬ አወቃቀርን ኢትዮጵያ ውስጥ አምጥተን እንተግብር ማለታቸው የዓመቱ ምርጥ ተቃርኖ (Paradox) ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፡፡
 በእኔ እምነት፤ ይህ አለማንበብ የወለደው ስህተት በፖለቲካው ዓለም ለ50 ዓመታት ከቆዩ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ አልነበረም፤ እሳቸውም ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የሀገራችን ፖለቲከኞች የንባብ ባሕል ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል::
በነገራችን ላይ ይህ የንባቡ ጉዳይ ጋዜጠኞቻችንንም የሚመለከት ነው:: የማደንቀው ጋዜጠኛ ደረጃ ኃይሌ በሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ዙሪያ በቂ የዕውቀት ትጥቅ ይዞ ቢገባ ኖሮ፣ ልክ ያልነበረውን የኦቦ ዳውድን መግለጫ፣ ከሥር ከሥሩ እየተከተለ “ሉዓላዊ..ምናምን” እያለ ባላፀደቀላቸውም ነበር..ቢያንስ የዩኬውን!
(ከጌታሁን ሔራሞ)

ሐምሌውን ጎርፍ በጨረፍታ...
ግብጽ ከሐምሌ በፊት ሶስቱ ሀገራት ሳይፈራረሙ ሙሌቱ እንዳይካሄድ የመጨረሻ ጥይቷን ተጠቅማለች። የአሜሪካም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ፈርደው “ግድቡን ሳይፈረም በሐምሌ መሙላት አትችይም የሚል የህግም ሆነ የሞራል” ተቀባይነት አይኖርም።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ውሳኔ ለመወሰን በ5ቱ ኃያላን ሀገራት፣ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ መሻር የሚችሉት ሀገራት ኢትዮጵያን የሚደግፉ ቻይና፣ሩሲያና ፈረንሳይ አንዱ ውሳኔውን ውድቅ የሚያደርጉት በመሆኑ ውሳኔው ተግባራዊ አይሆንም። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ምቹ ሁኔታ አላት።
ይህ አጀንዳ ኃያላኑን በቀላሉ አንድ ላይ እንዲቆሙ የሚያደርግ አይሆንም። በሊቢያ ላይ በወሰዱት የጋራ አቋም ሩሲያና ቻይና መሳሳታቸው ስለገባቸው ፤ በሶሪያ አሳድ ላይ ውሳኔ ማስተላለፍ አለመቻላቸው ይታወሳል። የአሜሪካው ኘሬዚዳንት ዶናልድ “እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ነች” ብለው ሲነሱ ፤ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አልፎ ለመሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ግብጽ ያረቀቀችው የውሳኔ ሀሳብ በመሪዎች ጉባኤ አብላጫ ድምጽ የትራምፕን አቋም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቃወሙት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በወቅቱ ፍልስጤምን ጨምሮ ድምጽ የሰጡትን ሀገራት የሚቀጣ የእርዳታ ማአቀብ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር። የጉዳዩን አቀነባባሪ ግብጽን ጨምሮ የዛቱባቸውን ሀገራት መቅጣት ግን አልቻሉም። የመሪዎች ጉባኤም ሆነ የጸጥታው ምክር ቤት፣ የትራምፕን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ተቃውሞ ቢገልጽም አሜሪካ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ ተጠቅማ ምንም አልሆነችም።
የግብጽ ኘሬዚዳንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ ኢትዮጵያን የሚያሳጣ ንግግር አደረጉ። የኢትዮጵያ ኘሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ምላሽ መስጠታቸውም ይታወሳል።ይህ አጀንዳ ሩሲያ ሶቺ ስብሰባ ድረስ የተከተላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሩሲያና የአሜሪካ አደራዳሪነትን “አመዛዝነው” አሜሪካ እንድታደራድራቸው ፈቀዱ።
ይህንን መሰል ድርድር ግብጽ “የአለም ባንክ ያደራድረን” የሚል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጊዜ አቅርባ ተቀባይነት አላገኘም ነበር።በወቅቱ የግብጽ ሀሳብ ሳይብራራ ድርድሩ ቀጠለ።
በሩሲያ ሶቺ በተደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ አልደራደርም ብትል፣ ለግብጽ ፕሮፓጋንዳ መጋለጧ አይቀርም ነበር። ግብጽ ኢትዮጵያን በኃያላኑ ጥርስ እንድትገባና የአሜሪካንና የአለም ባንክ ድጋፍ እንድታጣ ስውር ሴራ እንደነበረው መገመት አይከብድም። ከግድቡ ግንባታ ጀርባ የቻይና ድጋፍ እንደሚኖር ስውር ፕሮፓንዳ በመንዛት፣ ቻይናን የጠመዱት ትራምፕ በጉዳዩ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው እንደ መላምት ሊወሰድ ይችላል። ቻይና በጂቡቲ ጦሯን ማስፈሯ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ባቡር ግንባታና የባብ ኤል መንደብ ሰርጥን እየተቆጣጠረች መምጣት ለአሜሪካ ሌላ ስጋት መሆኑ አልቀረም።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰራት ለኢትዮጵያ የሚፈጥረው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጡንቻ የገመቱት አሜሪካና የአለም ባንክ በዚህ ድርድር ስም ፤ኢትዮጵያን ከቻይና ጉያ መንጠቅ አስፈላጊ እንደሆነ አምነውበት የገቡበት መሆኑን መጠርጠር ይቻላል።ግብጽ ደግሞ በሴራ የተቃኘና ውትብትብ ስምምነት በማስፈረም በሆነ ባልሆነው ኢትዮጵያ ስምምነት ጣሰች በማለት ግድቡ ቢያልቅ እንኳን የግብጽ ውሀ ማቆሪያ እንዲሆን ማድረግ ነው።
አሜሪካና የአለም ባንክ ወደፊት ግድቡ ለግል ኩባንያዎች በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ክፍት የሚሆንበት አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር የቻይናን ተጽኖ በመቀነስ የአሜሪካ ኩባንያዎች እንዲቆጣጠሩት ሊሆን ይቻላል።ከተሳተፉት ተቋማት ባህሪ ሲታይ ሁለቱ ሀገራት ግጭት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የሚነካ ነው ከሚል ትንታኔ ሳይሆን የአሜሪካ ትሬዥሪም ሆነ የአለም ባንክ ግድቡ የሚያስገኘውን የኢኮኖሚ ጡንቻ ለራሳቸው በሚመች ሁኔታ መቃኘትን መነሻ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።ድርድሩን አሜሪካ (የኘሬዚዳንቱ የኢኮኖሚ እይታ ይታወቃል) እና የአለም ባንክ ለወደፊት የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸውን ለመዘወር፤ግብጽ ደግሞ የፖለቲካ ጥቅምና “እምቢ የማይባሉ” አሸማጋዮች ኢትዮጵያን ጫናውስጥ በመክተት ማስፈረም ነበር።
ታዛቢ የተባሉት አካላት ታላላቅ ተቋማት ቢሆኑም ለጉዳዩ የቴክኒክም ሆነ የመደራደሪያ ጭብጥ ቅርበት የሌላቸው ናቸው። ወዲያው ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ተለውጠው አረቀቁት የተባሉትን ውል ግብጽ ሳታወላውል ለመፈረም መቸኮሏ የሚናገረው ነገር አለ። ግብጽ ያረቀቀችውን ሰነድ በጀርባ በር ሰጥታ በፊት ለፊት ፈጥና ረቂቁ ላይ ለመፈረም ብትቸኩል አይገርምም።
የሱዳን ተደራዳሪዎች የቀድሞ መሪያቸው የተስማሙትን ለማጤን እንደፈለጉ በመግለጽ ተመለሱ፤ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም ከመሪያቸው ጋር ለመነጋገር መመለሳቸው ተሰምቷል።
እንዲህ እንዲህ እየተባለ የኮቪድ ወረርሽኝ መጣ። የሀገራዊ ምርጫ መራዘሙ፣ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንበሮቿን መዝጋቷ የውስጥ ሁከትን ለመፍጠር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እድሉን እየቀነሰ መጣ።
 የግብጽን አዝማሚያ የተረዳው መንግስት፤ እስረኞችን በመፍታት የተካረረውን የውስጥ ፖለቲካ ለማርገብ ሞከረ።
አስበውበትም ይሁን በድንገት “የሽግግር መንግስት” ወይም “ምርጫ መካሄድ አለበት” የሚሉ ሁለት የተለያዩ መነሻ ያላቸው የፖለቲካ ሀይሎች መፈጠራቸው ሀገሪቱን ወጠራት። እነዚህ አጀንዳዎች ደግሞ እየተብላሉ ባሉበት ሁኔታ የመንግስቱ ቁንጮ መሪ፣ የሰላም ኖቤል ሽልማት አለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያጠይም የአምነስቲ ሪፖርት ወጥቶ አወዛገበ። በሀገራችን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ደረጃ አልደረሰም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች፣ መንግስትን በስልጣን ማራዘም አምርረው እየከሰሱት ይገኛሉ። ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት ቅቡልነት የለውም በሚል የተጀመረው መግለጫና ክስ፣ ለሽማግሌ የማይፈታበት ጽንፍ ላይ ደረሰ።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት በድንገት አዲስ አበባ መጥተው ከመንግስት ጋር ተነጋግረው ሲመለሱ፣ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ኃይል ሴራው ለኛ ነው በሚል ያብጠለጠሉት ሲሆን፤ የጋራ ወታደራዊና የደህንነት ስምምነት ያላቸው ሀገራቱ ከግብጽ የሚቃጣ ጥቃትን በጋራ ለመከላከል ተነጋግረው ይሆናል በሚል በቀና የቆጠሩትም አልጠፉም።
ይህ ወሬና ሹክሹክታ በሽግግር መንግስቱ ዘመን በለሆሳስ ይነገር የነበረውን የኮንፈደሬሽን ጭምጭምታ ካልታወቀ በኩል ተዛምቶ ለጊዜው ተዳፈነ። የኤርትራ ኘሬስ የተሰኘ የማህበራዊ ድረገጽ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር ኃይሎች የጋራ ልምምድ ጠቃሚነት ጠቆመ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወታደራዊ መኮንኖች ሰብስበው አሮጌ ሰነድ ዙሪያና የዘመናዊ ጦር አስፈላጊነት በቴሌቪዥን መስኮቶች መነገር እንደ መደበኛ ስራና ውይይት ከመውሰድ ይልቅ እየቀረቡ ያሉ አደገኛ ነገሮችን ለመመከት ሀገሪቱ ዝግጅት መያዟን መገመት አይከብድም። በዚሁ ጊዜ ስለ ወታደራዊ ልምምድ አስፈላጊነት መናገራቸው፤ግብጽ በየጊዜው በቀይ ባህር ላይ የምታደርጋቸው ተደጋጋሚ ዜናዎች ታወሱኝ።
በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ የሱማሊያ፣የጂቡቲና ኳታር የግብጽን አቋም መቃወማቸው በአካባቢው እየመጣ ያለውን ግዙፍና ውስብስብ ችግር ከወዲሁ ከመስከረም 30 በፊት ሀገሪቱ እንደምትጋፈጥ መገመት አይከብድም። ምርጫ ይካሄዳል አይካሄድም ሳይሆን ግዙፉ አጀንዳ በህዳሴ አንድ ባልዲ ውሀም ቢሆን ከሐምሌ በፊት ያለ ፊርማ ኢትዮጵያ ትሞላለች ወይስ አትሞላም የሚለው ይመስለኛል።
በሐምሌ ወር እንደተባለው ውሀው መሞላት ለኢትዮጵያ ትልቁ ድል ነው።ይህ ካልሆነ ግን መንግስት ቅቡልነት እንደሚያጣና የህዝብ አመኔታ የሚያጣ መሆኑን መገንዘብ አለበት።
(ከእስክንድር ከበደ)

Read 3327 times