Saturday, 04 July 2020 00:00

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ (1976-2012)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በአምቦ ከተማ በ1976 ዓ.ም ከአባቱ አቶ ሁንዴሳ ቦንሳና ከእናቱ ጉዲቱ ሆራ ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም በአምቦ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በመግባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እንዲሁም በዚያው በአምቦ ከተማ በሚገኘው አምቦ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተምሯል፡፡
በ1995 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በወቅቱ የኦሮሞ ተማሪዎች በሚያነሷቸው የተለያዩ የነፃነትና ዲሞክራሲ ጥያቄዎች ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ እንደነበረ የሚነገርለት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከ6 ጓደኞቹ ጋር ለእስር ተዳርጐ እንደነበር በሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ለ5 አመታት “በአምቦ ከርቸሌ” ታስሮ ሳለ በማረሚያ ቤቱ በትምህርት ብዙም ያልገፋ ወጣቶችንና ጎልማሶችን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ፊደል ያስቆጥር እንደነበርና በኋላም ይህ ጅምራቸው ሰፍቶና ለምቶ እንደ ቀላል የጀመረው ፊደል ማስቆጠር በአሁኑ ወቅት በማረሚያ ቤቱ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ድረስ ለሚሰጠው ትምህርት መሰረት ጥሏል፡፡
አርቲስት ሃጫሉ ከአምቦ ከርቸሌ የእስር ጊዜውን አጠናቆ ከወጣ በኋላ ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ ያለውን የሙዚቃ ፍላጐት በማጐልበትና በማረሚያ ቤት እያለ ያዘጋጃቸውን በርካታ የዘፈን ግጥምና ዜማዎች በመያዝ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት “በሠኚ ሞቲ”” የተሰኘውንና ከሕዝብ ጋር በሰፊው ያስተዋወቀውን የመጀመሪያ አልበሙን ሊያሳትም ችሏል።
በእስሩ ምክንያት አቋርጦት የነበረው የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን በመቀጠልም እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል፣ በርካታ የዘፈን ግጥሞችና ዜማ በመድረስም ለራሱም ለሌሎችም ድምፃውያን ማበርከቱን የሕይወት ታሪኩ ይናገራል።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከሌላኛው የኦሮሞ የነፃነት ሙዚቃዎች አቀንቃኝ አርቲስት ጃምቦ ጆቴ ጋር በመሆንም በጋራ የምስል ወ ድምጽ አልበም ያሳተመ ሲሆን በኮንሰርት ስራም ወደ ጅማ በሚያቀኑበት ወቅት ባጋጠማቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋም ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጎ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳት የተነሳም ለ9 ዓመታት ያህል ከመድረክ ርቆ እንደነበር ተገልጿል። ይሁን እንጂ በኦሮሞ የነፃነት የትግል ዜማዎች ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያላቸውን በርካታ ዘፈኖች የያዘውን “ዋኤ ኬኛ” (የኛ ጉዳይ) የተሰኘውን አልበሙን በ2007 አሳትሟል። በዚህ አልበሙ የተካተቱ “ማላን ጅራ” (ምኑን አለሁ)፣ “ቶኩማ” (አንድነት) የተሰኙ ዜማዎችና ሌሎች ከ10 በላይ ስራዎች በቀጥታ የነፃነት ፍላጎትህ የሕዝብ ጭቆናዎችን የሚያንፀባርቁ ነበሩ።
ይህን የአልበም ስራውን ተከትሎም ወደ አሜሪካ በማቅናት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ያቀረበ ሲሆን በወቅቱ በአገሪቱ ተቀጣጥሎ በነበረው አመፅና ተቃውሞ የተነሳ ወደ አገር ቤት እንዳይመለስና እዚያው አሜሪካ እንዲቀር ቢወተወትም “ማንንም ፈርቼ ከአገሬ አልሸሽም” በማለት ወደ አገር ቤት የተመለሰ ሲሆን በቀጥታ በአገር ውስጥ ይካሄዱ በነበሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ ያደርግና በሚያወጣቸው ነጠላ ዜማዎቹ የነፃነት ጥያቄዎችን መጠየቅ መቀጠሉን የአርቲስቱ የሕይወት ታሪክ ይናገራል።
“ያመነበትን ነገር ከመናገር ወደ ኋላ አይልም” የሚባለው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ ከጥበብ ስራዎቹ ጎን ለጎን በተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል። የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በነበሩበት ወቅት ቦታው ድረስ በተደጋጋሚ በመሄድ ድጋፍ አድርጓል፣ ውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ድጋፍ አሰባስቦላቸዋል። ተፈናቃዮቹን ለማገዝ በክልሉ መንግሥት በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የተጋበዘው አርቲስቱ፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጭምር በወቅቱ ያስደነገጠ ሙዚቃውን አቅርቧል።
ይኸ “ጅርቱ” (አላችሁ?) የተሰኘው ደፋር የሙዚቃ ሥራው፤ ከለውጡ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ሚሊኒየም አዳራሽ የቀረበና ቄሮ ቤተ መንግሥቱን እንዲቆጣጠር በቀጥታ የሚቀስቅስ ነበር። ይሄ ሥራው በኦቢኤን በቀጥታ መተላለፉን ተከትሎ በኢህአዴግ ባለሥልጣናት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ይነገራል።  
በ2007 አልበሙ “ማለን ጅራ” (ምኑን አለሁ) ሲል በደልና ጭቆናን ያንጸባረቀበትን ሙዚቃ ለተከታዮቹ ያቀረበው አርቲስቱ፤ ለውጡን ተከትሎም “ጅራ” (አለን) የሚል የፖለቲካ ስሜቱን ያንፀባረቀበትን ተወዳጅ ሥራውን ለአድማጮቹ አድርሷል። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በለውጡ አካሄድ ላይ የነበረውን ቅሬታ ለመግለጽም በቅርቡ “ኤስ ጅራ” (የት ነው ያለነው?) የሚል ነጠላ ዜማ እያዘጋጀ እንደነበር በቅርቡ በኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልፆ ነበር።
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 9 ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ በጥይት ተደብድቦ በ36 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት የተለየው ተወዳጁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤  ባለትዳርና ጊፍቲ (እመቤት) ብሎ የሰየማትን የአንድ ወር ጨቅላ ልጁን ጨምሮ የሶስት ሴት ልጆች አባት ነበር።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በአወዛጋቢ ሁኔታም የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በአምቦ ገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ተፈጽሟል።   

Read 1085 times