Saturday, 04 July 2020 00:00

ዶ/ር ጫኔ ከበደ ስለ ኢትዮጵያ ፌደራሊዝም የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርቡም የኢኮኖሚውን ጉዳይም መመልከት አለባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በቅርቡ “የዘር ፖለቲካና የቋንቋ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በጥናት ላይ የተመሰረተ መጽሐፋቸውን ለንባብ ያበቁት አንጋፋው ፖለቲከኛና
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ጫኔ ከበደ በጥናታዊ ስራቸው ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል።


              ይሄን ጥናታዊ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ገፊ ምክንያት የሆንዎት ምንድን ነው?
ከለውጡ በፊት ለምን የአገሪቱ የፌዴራሊዝም አካሄድ ተጠንቶ አይቀርብም የሚል ጥያቄና ሀሳብ በውስጤ ይመላለስ ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ፖለቲከኞችን ሰብስበው የተጠና ነገር  ይዛችሁ ብትቀርቡ ለውይይት በጣም የተሻለ ይሆናል የሚል አቅጣጫ ሰጥተው ነበርና ያኔ ይሄን ጥናት ወደ ሰነድ ብቀይረው የሚል ሀሳብ አደረብኝና ነው ወደ ሥራው የገባሁት። በሌላ በኩል፤ በዚህ መልኩ ጥናት ቢቀርብ ፌደራሊዝሙን ለማስተካከል ይቻላል የሚል ሀሳብም ይዤ ነው ሥራውን የጀመርኩት።
እንዴት ነው ጥናቱን ያካሄዱት? ምን ያህል ጊዜስ ፈጀ?
ጥናቱ 1 ዓመት ከ6 ወር አካባቢ ፈጅቶብኛል። ጥናቶቹን ለማካሄድ የሞከርኩት ደግሞ በ3 አይነት መንገድ ነው። አንደኛ፤ ከስታትስቲክስ ባለሥልጣን በ1999 የሕዝብና ቤት ቆጠራ ያደረገበትን ሰነድ ወስጃለሁ። ሁለተኛ፤ ብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ይባል የነበረውና በደርግ ጊዜ የተቋቋመው ያጠናውን ሰነድ ለማጣቀስ ሞክሬያለሁ። ሶስተኛ ደግሞ በጀርመን ባህል ማዕከል ውስጥ በተለይ የብሄር ስብጥሩን በሚመለከት ተጠንተው የተቀመጡ መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦች ተፅፈው አግኝቻለሁ። እነሱንም ተጠቅሜባቸዋለሁ። ከዚህ ውጪ በፌደራሊዝም ላይ የተደረጉ የተለያዩ ወርክሾፕና ሴሚናሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ያገኘኋቸውን ሀሳቦች ለማመሳከሪያና ተአማኒ ለማድረግ ሰነዶች አገላብጫለሁ። ሌላው በሥራ ባህሪዬ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በምንቀሳቀስበት ወቅት በየአካባቢው የማገኛቸውን የማህብረሰብ ክፍሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ወስጄ አነጋግሬያቸዋለሁ። በተለይ የማህበረሰቡን ታላላቅ ሰዎች እያገኘሁ ለጥናቱ በሚያመች መንገድ አነጋግሬያቸዋለሁ። የዞን አስተዳዳሪዎችና የየአካባቢው የባህል ተቋማት ሃላፊዎችን ሀሳብም ለመውሰድ ሞክሬያለሁ።  የእነሱን ሀሳብና በሰነድ ያገኘሁትን ጊዜ ወስጄ ለማመሳከር ጥረት አድርጌያለሁ። በምሁራን የቀረቡ ሰነዶችንም ሀሳቦች ለማቀናጀት ጥናት አድርጌያለሁ። ሌላው አሃዙን ለመስራት የተጠቀምኩበት ዘዴ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይ በየአመቱ የሕዝብ ቁጥሩ በ2.9 በመቶ ያድጋል የሚል ስሌት አለ። ያንን የስሌት መንገድና የአለማቀፍ የትንበያ ቀመር ተጠቅሜ የህዝብ ቁጥሩ በ12 ዓመት ምን ያህል ይጨምራል የሚለውን ስሌት ሰርቼያለሁ። በየዞኑ በየወረዳዎቹ ያለውን የሕዝብ ብዛት በ1999 መገኛ አስልቼ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። አጠቃላይ የሕዝቡ ብዛት ያን ጊዜ 82 ሚሊዮን ነበር፡፡  አሁን በኔ ስሌት ወደ 107 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡ ለጥናቱ የተጠቀምኩት ስልት እነዚህን ሁሉ ያካተተ ነበር።
የዚህ ጥናት ዋነኛ ግኝት ምንድን ነው? በመጽሐፉስ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው?
አንደኛው ጥናት፤ የሕዝብ ቁጥሩን ሳይንሳዊ በሆነ ስሌት ማስቀመጥና ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች አካላት ይሄን ከግምት ውስጥ እያስገቡ ስራቸውን እንዲሰሩ ለማስቻል ነው። መንግሥትም ስሌቱ ለፌዴሬሽን ም/ቤት አሰራር ይጠቅመዋል የሚል ግምት አለኝ። ከዚያ ውጪ በኢትዮጵያ ውስጥ የከተማውና የገጠሩ ማህበረሰብ አኗኗር የተለያየ እንዳልሆነና በእያንዳንዱ አካባቢ የተለያየ ብሄረሰብ እንደሚኖር ያመላክታል። አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ግን ከዚህ እውነታ በተቃራኒው ያንን የተለያየ ማህበረሰብ ቋንቋህን መናገር አትችልም፤ የኔን ቋንቋ ብቻ ተናገር፣ የመሬቱ ተወላጅ አይደለህም መጤነህ ብሎ ሲፈረጅ ለሚውለው አካል ከዚያ ብሄረሰብ ውጪ ሌሎች ብሄረሰቦች ምን ያህል ነዋሪ እንደሆኑ፣ ምን ያህል ስብጥር እንዳለ የሚያሳይና የፖለቲካ ተሳትፎአቸውም በዚህ ልክ መስተካከል እንዳለበት ለመጠቆም ነው። ይሄ አንዱ የጥናቱ ግኝት ነው። በዚህ መሰረት የተዋቀረው ፌደራሊዝም የማይሰራ መሆኑን ነው ያመላከተው። ሁለተኛ ከግለሰብ መብት መመንጨት የሚገባው ፌደራሊዝም፣ በብሄርና በቡድን ብቻ የሚል መንገድ ይዞ መሄዱ የተሳሳተና ለወደፊት በዚህ መንገድ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከመፈራረስ እንደማይድን ለማሳየት ነው። እነዚህን እውነታዎች ለማሳየትም የ4 አገራትን የፌዴራል ሥርዓት እንደማሳያነት ጠቅሻለሁ። ለምሳሌ የህንድን ብንመለከት፣ ከአስተዳደር ፌዴራሊዝም በተጨማሪ የኢኮኖሚ ፌደራሊዝሙ ምን መምሰል እንዳለበት እንደ ተሞክሮ አሳይቻለሁ። በህንድ ፌደራሊዝም ክልል የተባሉት ህገ መንግሥት የላቸውም። በኛ አገር ደግሞ ክልል የተባሉት ሕገ መንግሥት አላቸው። ይሄ የተሳሳተና ለወደፊት ሕገ መንግሥት ያለው ክልል ካለ አንቀፅ 39ን ተጠቅሞ አገር የመሆን እድል ይኖረዋል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ሆን ተብሎ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊጋፋ የሚችል መሆኑን ለማመላከት ነው የሞከርኩት። ናይጄሪያም ተመሳሳይ ተሞክሮ ነው ያላት። የኛም ከአስተዳደር ፌደራሊዝም ይልቅ የኢኮኖሚ ፌደራሊዝም ላይ ያተኮረ አደረጃጀት ቢሆን ነው የሚሻለው።
አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ዋናው ችግሩ ምንድን ነው ይላሉ?
ከዚህ በኋላ ሁሉም ክልል የመሆን ጥያቄያቸው አይቋረጥም ይቀጥላል። አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል ዝም ካልን ሲዳማ ክልል በሆነበት አግባብ ሌላውም ክልል መሆኑን ይቀጥላል። ሁሉም የየራሳቸውን ክልልና የክልል ባንዲራ እያወጡ እያሳዩ ነው። ወራቤ መግቢያ ላይ “እንኳን ወደ ስልጤ ብሄራዊ ክልል ደህና መጣችሁ” የሚል ተለጥፏል። ይሄን መሰሉ ታፔላ ሀዋሳ መግቢያ ላይም ነበር። ወላይታ ደግሞ ከታፔላውም በላይ ቤቶች በሙሉ የወላይታ ሰንደቅ አላማ ብቻ ተቀብተው በየቦታው የዎላይታ ክልል የሚል ነው የሚታየው፡፡ ሌላውም ጋር ተመሳሳይ ነው።  ይሄ የሚያሳየው ሁሉም ከማን አንሳለሁ የሚል ስሜት ውስጥ እንዳለ ነው። የሕዝብ ቁጥራቸው በዝቶ ሳይሆን ላለፉት 27 ዓመታት ክልል ሆነው፣ የክልሉ ባለሥልጣናት ምን ያህል በሀብት መደራጀታቸውን፣ ምን ያህል በስልጣን የሙስና ሰንሰለት እንደሰሩ፣ ምን ያህል ወገኖቻቸውንና ዘመዶቻቸውን እንደጠቀሙ ይታወቃል። ስለዚህ አሁን ያለው የፖለቲካው ተዋናይ ያንን ማድረግ ይፈልጋል። ከዚህ ውጪ እያንዳንዱ ክልል የሚጠይቅ ዞን “እራሳችሁን ለማስተዳደር ምን ሀብት አላችሁ” ተብሎ ሲጠየቅ ምንም የላቸውም። ምን ያህል ገቢ ታገኛላችሁ? ተብለው ቢጠየቁ ምንም መልስ የላቸውም። አካባቢው እንኳን የራሱ የሀብት ምንጭ ሊኖረው ቀርቶ ሰዎች በጣም ተጠጋግተው ተጣበው የሚኖሩበት የመሬት ችግር ያየለበት አካባቢ ነው። የመስኖ ልማት እንኳ ለማከናወን የሚያስችል ወንዝ የሌላቸው አሉ፡፡ ወላይታን እንደ ምሳሌ ብናነሳ፣ ወላይታ ያለው የመሬት ስፋት በጣም አነስተኛ ነው። የህዝብ ብዛቱ ደግሞ ከፍተኛ ነው። በየገበሬ ማህበሩ ውስጥ ስገባ የማገኘው አንድ ገበሬ ትልቅ መሬት አለው ከተባለ 50 ካሬ ሜትር ነች። 50 ካሬ ሜትር ላይ ምርት አምርቶ፣ ቤት ሰርቶበት እንዴት ነው የሚኖረው? ስለዚህ የወላይታ ወጣት ከቀዬው ተሰድዶ ቤተሰቡን በሽቀላ  ነው የሚያኖረው። ህብረተሰቡ በፌደራል ደረጃ በድጎማ የሚኖር ሕዝብ ነው። ስለዚህ ክልል ልሁን ከተባለ ቢያንስ ራስን ችሎ መኖር ይቻላል ወይ የሚለውን ነው መጀመሪያ መጠየቅ የሚገባው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከሌሎች ክልሎች በሚሰበሰብ ግብር ነው እነዚህ ክልሎች ሊኖሩ የሚችሉት። ለምሳሌ አማራ ክልል ቁጥር 1 ግብር ከፋይ ነው። ይሄ ክልል የራሴን ሀብት ብቻዬን ልጠቀም የሚልበት ሕገ መንግሥታዊ አሰራር የለም እንጂ እንዲህ ያለ ነገር ቢፈጠር፣ እነዚህ ክልል እንሁን የሚሉ ሁሉ ችግር ውስጥ ነው በቀጥታ የሚወድቁት። ሁኔታው ወደ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ግጭት ነው የሚያመራው። ስለዚህ መሆን ያለበት አሁን ያለውን አስተዳደራዊ ፌደራሊዝም ከፊሲካል (ኢኮኖሚያዊ ፌደራሊዝም )ጋር አዋህዶ መተግበር ነው።  የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርቡም የኢኮኖሚውን ጉዳይም መመልከት አለባቸው።
አንቀጽ 39 የመገንጠል መብትን ለክልሎች ሳይሆን ለብሄሮች ነው የሚፈቅደው፡፡ እርስዎ በመጽሐፉ ያስቀመጡት ሁኔታ የሚያስረዳው ደግሞ በክልሎች ውስጥ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ ነው። ከዚህ አንፃር መገንጠል እውን መሆን የሚችልበት እድል ምን ያህል ነው?
ዋነኛው ሕገ መንግሥት መገንጠልን በክልሎች ሳይሆን በቀጥታ ለብሄሮች ነው የሚሰጠው፤ ነገር ግን ክልሎቹ ባወጡት የየራሳቸው ሕገ መንግሥት ውስጥ በውስጣቸው ያሉ አናሳ ብሄረሰቦችን ደፍጥጠው፣ ክልሉ እንደ ክልል መገንጠል እንደሚችል ነው ያስቀመጡት። ከዚህ አንፃር የፌደራሉና የክልሎች ሕገ መንግሥት እርስ በእርሱ በጣም የሚቃረን ነው። ክልሎች ባስቀመጡት የየሕገ መንግሥታቸው አንቀፆች፤ የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቁ መገንጠል እንደሚችሉ ጭምር ነው የሚገልፀው። ሌሎች በውስጣቸው ያሉ አናሳ ብሄረሰቦች መብት በዚህ ውስጥ አልታየም። ማንንም አንጠይቅም በሚል ነው የሚደፈጥጡት፡፡ አንቀፅ 39 ከጅምሩ ጀምሮ እስከ ትናንትናው ድረስ ችግር ያለበት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነቀርሳ ሆኖ የተቀመጠ ነው። አሁንም ክልል እንሆናለን፤ አገር እንሆናለን እየተባለ የሚፈጠሩ ረብሻዎች የዚህ አንቀጽ ውጤት ናቸው።
አሁን ባለው የክልል አደረጃጀት ላይ በመፅሐፉ ሰፊ ትንታኔ ከሰጡ በኋላ የራስዎን የቢሆን ትንተናዎችም አስቀምጠዋል። በዚህ ትንተናዎ 12 ክልሎች ወደ ሶስት ራስ ገዝ አስተዳደሮች መዋቀር እንዳለባቸው አስቀምጠዋል። ይሄን አወቃቀር ሲያዘጋጁ በዋናነት ምንን እንደ መስፈርት በመጠቀም ነው? አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታስ እውን መሆን የሚችል ነው ብለው ያምናሉ?
የቀረቡት ምክረ ሀሳቦች እኔ ጨምቄ ባቀርባቸውም የበርካታ ምሁራን አስተያየቶች ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ ታች ድረስ ወርጄ ማህበረሰቡን አናግሬ ያገኘሁት ግብዓት ነው። ከእነዚህ ጋር ብትካለሉስ እያልኩ የአገር ሽማግሌዎችንና ህብረተሰቡን ጊዜ ወስጄ ጠይቄያለሁ። ትልቁ ችግር ያለው የፖለቲካ ልሂቃኑ ጋር ነው እንጂ ህብረተሰቡ የሚፈልገው አከላለል በመጽሐፉ በተቀመጠው መልኩ ነው። ለምሳሌ ከውድድር መንፈስ ወጥተው እኔ ባስቀመጥኩት መሰረት ሃድያ፣ ስልጤ፣ አላባ፣ ከንባታ፣ ጉራጌ፣ በተወሰነ ደረጃ የየም ብሄረሰብ በመልከ ምድራዊ አቀማመጥና በማህበራዊ መስተጋብራቸው አንድ ላይ ሆኖ ለመከለል የሚመች ነው። የአገር ሽማግሌዎችና ያነጋገርኳቸው የየገበሬ ማህበሩ ሊቃነ መናብርት ይሄንን ይፈልጉታል። በዚህ መልኩ ቢዋቀር ይጠቅመናል የሚል እምነት ነው ያላቸው። ለምሳሌ አሁን ሃዲያ በሚያቀርበው የክልልነት ጥያቄ መሰረት፤ ራሱን ችሎ ይካለል ቢባል፣ ከንባታን አልፈው ያሉት የምስራቅና ምዕራብ ባይዋቾ የሃድያ ወረዳዎች እንዴት ሆነው ነው በሃድያ ስር የሚተዳደሩት? ይሄ የማይቻል ነው። እነሱንም ሳነጋግር የማይቻል መሆኑን ነው የነገሩኝ። ብሄረሰቦቹ በየተናጠል ክልል ከሚሆኑ ይልቅ ኢኮኖሚን ታሳቢ አድርገው፣ በአንድ ክልል ሆነው የከተማ ማዕከላትን መከፋፈል ይችላሉ። ለምሳሌ ሆሳዕና የዲፕሎማሲ ማዕከል ቢደረግ፣ ጉራጌ የኢኮኖሚ ማዕከል ቢደረግ፣ ከንባታ የግብርና ወይም ደግሞ የግብርና መካናይዜሽን ማዕከል ቢደረግ ያዋጣናል ነው ያሉኝ። ይሄን ግብዓት የሰጡት የየራሳቸው ምሁራን ናቸው።
በሌላ በኩል ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ ደግሞ የባህል መስተጋብራቸው የኢኮኖሚ ትስስራቸው ተመሳሳይ ነው። የቋንቋ ግንኙነት አላቸው፡፡ በፊት ላይ አንድ አይነት ማህበረሰብ እንደነበሩ መስተጋብራቸው በሚገባ ያሳያል፡፡
በመጽሐፉ እንደተገለፀው፤ የተደራጀ የኢኮኖሚ መዋቅር ዘርግተው ተያይዘው ማደግ ይችላሉ። ሌላው በመጽሐፋ የተጠቆመው፤ የራስ ገዝ አስተዳደሮች ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ወልቃይት፣ ጠዬ፣ ፀለምት፣ ሁመራ አካባቢዎች በልዩ ራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ መግባት ይችላሉ። ትግርኛ፣ አማርኛ ሌላም ቋንቋ ሊነገርባቸው ይችላል። ራያ አካባቢ አላማጣ፣ መሆኒ፣ ኮረም፣ ዋግህምራ፣ ከአፋር አንድ ወረዳ አንድ ላይ ተደርጎ ልዩ ራስ ገዝ አስተዳደር ቢመሰረት የተሻለ ይሆናል፤ ማህበራዊ መስተጋብራቸው ቋንቋቸው  ተመሳሳይ ነው። ሌላው በመጽሐፉ በዝርዝር ቀርቧል። የድሬዳዋ፣ የአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች እንዴት ይደራጁ? የሚለውን በጥናቱ ግኝት በመጽሐፉ ለማመላከት ተሞክሯል። የቻርተር ከተሞች እነ ማን ይሁኑ የሚለውንም ከዝርዝር ምክንያቶችና የጥናት ግኝቱ ጋር ተቀምጧል።
ይሄ ሀሳብዎ  በሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ አሁን ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ አመቺ ይሆን?
መቼ ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ለሚለው፣ እውነተኛና ቀና መንግሥት ካለ፣ ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይቻላል። የድንበርና የማንነት ኮሚሽን በሚል የተቋቋመው አካል ይሄን ጥናት ተጠቅሞ ቢሰራበት በቀላሉ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ይህ ተግባራዊ ቢሆን የተሻለ መረጋጋት መፍጠር ይቻላል። መንግሥት አጥንቶ ያቀረበው ከኔ ጋር በጣም የተራራቀ ነው። በዚህም አንዳንዶች ከወዲሁ አንቀበለውም እያሉ ነው። ስለዚህ ይሄን ጥናት መፈተሽና እኔ ያቀረብኩትንም መመልከት በእጅጉ ጠቃሚ ነው።  

Read 1151 times