Print this page
Saturday, 14 July 2012 07:40

ለ‘አንድዬም’ የቸገረ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ሐምሌም ገባ፣ መስከረምም ጠባ፣ ሌላ ዓመትም ሽው ብሎ ሄደ…ይኸው ሆኗል ነገራችን-- አሮጌ ዓመት መሸኘት አዲስ ዓመት መቀበል፡፡ ‘አምና ከዘንድሮው እየተሻለ’… ከተረት አያልፍም ያልነው ነገር ሁሉ እውነት እየሆነ ይኸው እዚህ ደረስን፡፡

ስሙኝማ…ዘንድሮ ባህል እየሆነ እንደመጣው…አለ አይደል…ለአንድዬ አቤቱታ በማድረግ ከዓለም አንደኛ ምናምን የሚል መለኪያ ይውጣልንማ!

ምስኪኑ ሀበሻ አንድዬ ዘንድ ቀርቧል፡፡

ምስኪን ሀበሻ:-  አንድዬ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት እንዲሁ እንደ ዘንድሮ ነገሩ ሁሉ ግራ ቢገባን አስቸግረንህ ነበር፡፡

አንድዬ:- ማን ልበል?

ምስኪን ሀበሻ:- ይሄን ያህል ረስተኸኛል? ምስኪኑ የሀበሻ ልጅ ነኛ!

አንድዬ:- ይቅርታ… የሀበሻ ልጅ ነው ያልከኝ…ዘነጋሁ ልበል…

ምስኪን ሀበሻ:- እንዴት አንድዬ፣ እንዴት! ይኸው ስንት ክፍለ ዘመን ሙሉ እጆቻችንን  ወዳንተ እንደዘረጋን አይደል! እንደውም ወደ ሌሎቹ ስታተኩር እንዳትረሳን ብለን በዘፈኑም፣ በስብከቱም፣ በዲስኩሩም፣ በቃለ መጠይቁም…“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”  እያልንም አይደል!

አንድዬ:- እህ! አስታወስኩ…አሁን ትዝ አላችሁኝ፡፡ ጉድ እኮ ነው…ከፍጡሮቼ ሁሉ እንደ እናንተ ግራ ያጋባኝ የለም፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- ኽረ አንድዬ እንደሱ አትበል!  ግራና ቀኙ የጠፋን እኛ!

አንድዬ:- የሚገርም ነገር እኮ ነው፡፡ እንደማስታውሰው መጀመሪያ የፈጠርኩት አዳምን ነበር፡፡ የሰው ልጅ አባት ሁሉ እሱ እንዲሆን ነበር ያስቀደምኩት፡፡  የእናተን ነገር ሳስበው ግን… እንደው ድንገት ከአዳም ሌላ የሰው ልጆች አባት የሚሆን ፈጥሬ ዘንግቼው ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡  ለነገሩ ብዙ ሌሎች የማያቸው ፋይሎች ስላሉ ትኩረቴ ሁሉ ወደእነሱ ሆኖ ነው እንጂ… የእናንተን ስርወ መሠረትማ ማጣራት አለብኝ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ ኽረ ተው እንደሱ አትበል… ጠጋ ብለህ ጓዳ ጎድጓዳችንን ብታውቅ ኖሮ  በአሁኑ ጊዜ ከእኛ የሚብስብህ አይኖርም ነበር፡፡

አንድዬ:- ትዝ ይለኛል…ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከእነኚህ ምስኪኖች የሚበልጥብኝ የለም ብዬ ምን እንደማደርግላችሁ እያሰብኩ እያለ፣ ጭርሱን ወደ እኔ ዞራችሁ አረፋችሁት፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- ኽረ ተው አንድዬ!…ደግሞ ወደ አንተ እጆቻችንን ከመዘርጋት በስተቀር ምን ክፉ ነገር አሰብንብህና ነው!

አንድዬ:- አስባችሁ መተው ደህና…የክፋታችሁ ክፋት በገዛ ቤቴ፣ በገዛ መንበሬ መጥታችሁ ለእናንተ የማደርግላችሁን ነገር ትጠይቁኛላችሁ ስል…እናንተ ሆዬ የጎረቤታችሁን ንብረት፣ የጓደኛችሁን ትዳር፣ የአማት አማቻችሁን ህይወት እንዳበላሽ ትለምኑኛላችሁ!

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ እኛ እኮ ግራ ሲገባን አንዳንዴ የምንለውን ባለማወቅ…

አንድዬ:- በየቀኑ መጥታችሁ ሌላውን እንዳጠፋላችሁ የምትጠይቁኝ ባለማወቅ ነው!

ምስኪን ሀበሻ:- ተው አንድዬ፣ እንዲህ አታምርር!

አንድዬ:- “የእሷን ነገርማ ካላሳየኸኝ”፣ “የእሱን ንብረት በውሀ ካላስበላህልኝ” እያላችሁ ዕንባችሁን ሽቅብ የምትረጩት ሞቀኝ አቀዝቅዙኝ አላልኳችሁ! …የዲያብሎስን ሥራ ወደ እኔ ስታዞሩ ምን እንዳልኩ ታውቃለህ…አይ፣ የእነኚህ ጉዳይ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ትኩረቴን ወደ ሌሎቹ ባዞር ይሻለኛል አልኩና ወደሌሎቹ ዞርኩኛ!

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ ተረዳን እንጂ፣ ቢጨንቀን እኮ ነው!

አንድዬ:- ደግሞ…ቤቴን ተሳልማችሁ ትወጡና የጸሎት መጽሐፍ እንኳን ገና ከኪሳችሁ ሳይወጣ እዛው በራፌ ላይ ጠጠር ብተና ትጀምራላችሁ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ…ጨነቀን አልኩህ እኮ! አንተ ዝም ስትለንና ሁሉ ነገር ሲጨላልምብን እሱ ከረሳን ሌላ ዘዴ እንሞክር ብለን ነው፡፡

አንድዬ:- ትገርሙኛላችሁ…ሌሎቹን አስተናግጄ ዘወር ባልኩ ቁጥር የምሰማው ሁሉ ወይ እርቧቸዋል፣ ወይ ጠምቷቸዋል፣ ወይ እርስ በእርስ ተበላልተው ሊያልቁ ነው…ችግር፣ ችግር፣ ችግር ብቻ ነው! አንዲት እንኳን ጥሩ ነገር ስለእናንተ የሰማሁበት ጊዜ ራሱ ከመራቁ የተነሳ ረስቸዋለሁ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- ይህን ያህል አንድዬ፣ ይህን ያህል!

አንድዬ:- ዶሮውንና ንፍሮውን በየሰዉ አጥር እየጣላችሁና እየበተናቸሁ…ቢርባችሁስ ምን ይገርማል!

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ…

አንድዬ:- አሁን ነገር አናብዛና…ዋናው ነገር ለምን ፈለግኸኝ?

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ ዛሬ ድንገት ዘወር ስትል ስላየኸኝ ነው እንጂ እኛ እኮ ሁልጊዜ እንደፈለግንህ ነው! ቤትህ ዘወትር በሰንበትም፣ በአዘቦትም የምንመጣው አንተን ፍለጋ አይደል እንዴ!

አንድዬ:- እሱን እንኳን ተወው… ገሚሶቻችሁ እኔን ልትፈልጉ አይደለም የምትመጡት፡፡  በእኔው ቤት መጥታችሁ ጽላትና መስቀል ሸጉጣችሁ የምትወጡ ጉዶች! እንደው አፍህን ሞልተህ እንደፈለግንህ ነው ስትል ያዝ እንኳን አያደርግህም!

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ ጥቂት ምግባረ ብልሹ…

አንድዬ:- ስማ… አይደለም እናንተ ምእመናን ነን የምትሉት አስተምራለሁ፣ እሰብካለሁ የሚለው በእኔ ስም እየተገዘተ፣ ዓለም ዘጠኝ እያለ አይደል እንዴ! አንዳንዴ እኮ በገዛ ቤቴ የምትሠሩትን አይና፣ ያኔ ሰዶምና ገሞራን ሳጠፋ ምህረት አድርጌላቸው የነበሩት ሀበሻ መሀል ተሰግስገው ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ እኛም እኮ እያየን እንዳንናገር ድንገት ቅስፈት ቢመጣ እያልን…

አንድዬ:- በራፌ ድረስ መጥተህ ይህንን ውሸትህን ተወኝ ነው እኮ የምልህ! እናንተ አይደላችሁ እንዴ የእኔ ቃል ተዛንፎ ሲሰበክ እያጨበጨባችሁ፣ ሆ እያላችሁ የልብ ልብ የምትሰጡት!

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ እንዴት መሰለህ፣ ዘመኑ እኮ…

አንድዬ:- ስማ፣ እውነተኞቹ የእኔን ቃል የሚያስፋፉት እኮ በባዶ እግራቸው እሾሁና ቆንጥሩ እየተለተላቸው፣ ጦማቸውን ውለው እያደሩ፣ ቁርና ቆፈን እየተፈራረቀባቸው ነው፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ እኛ ታዲያ ምን አደረግን?

አንድዬ:- እናንተማ… በቪላ ቤት እየተንደላቀቃችሁ፣ በዘመናዊ መኪና እየተንፈላሰሳችሁ፣ ቀን የለበሳችሁትን ልብሰ ተክህኖ ሻንጣ ቆልፋችሁ ያስተማራችሁትን ራሳችሁ እያፈረሳችሁ፣ በእኔ ስም የቀረቧችሁን እሀቶቻችሁን ለተራክቦ እያስገደዳችሁ… እባክህ ተወኝ፡፡

የእናንተን ጉድ ለመዘርዘር ሌላውን ዓለም ለመንፈቅ መርሳት ይኖርብኛል፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- ኽረ አንድዬ፣ ሀጢአታችንን እንዲህ አታብዛብን!

አንድዬ:- ደግሞ የሰውን ልጅ በማይለየው በእኔ መንበር በጎጥና በአምቻ ጋብቻ እየተሰባሰባችሁ…በጥቅም እየተቧደናችሁ… እንደው እኔ ዘንድ ስትመጣ ይህን ሁሉ አያውቅም ብለህ ነው!

ምስኪን ሀበሻ:- ምን መሰለህ አንድዬ፣ ጥቂቶች ትምህርቱን እየበረዙት…

አንድዬ:- ተወኝ አልኩ እኮ…የእኔን ቤት እንዲህ በስውር ጽላቱን፣ መስቀሉን፣ ጽናጽሉን እየተናጠቃችሁ እርስ በእርሳችሁ በጥርስ ብትቀረጣጠፉ፣ በጥፍር ብትቦጫጨሩ ምን ይገርማል! እኔ ዘንድ ከመምጣትህ በፊት ሰብሰብ ብላችሁ ሰጥቻችሁ የትም የተበኑትን ሰው የሚያደርጉ ባህርያት ብትመልሱ ደግ ነበር፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣  ምን መሰለህ… አንድም የመጣሁት እኮ እንደው መልሰን እንደ ሰው እንድናስብ አእምሮና ልቦናችንን ባርክልን ብዬ ልለምንህ ነው፡፡ ግራ ገባን እኮ! ተደነጋገረን…

መቼም ከአንተ የምደብቀው ነገር የለም…ሀበሻ ለሀበሻ እንዲሁ በሆነ ባልሆነው ተባልተን ልንተላለቅልህ ነው፡፡

መተማመን ጠፋ፣ ወዳጅነት ጠፋ፣ ሰብአዊነት ጠፋ፣ ሁሉም ለእኔ ብቻ ሆነ፡፡ አንድዬ አንድ የቀረኸን…ይበቃችሁ የምትለን አንተው ነህ፡፡

እጃችንን እስከ ዛሬ ወዳንተ ዘርግተን የኖርነውም እኮ… ይኸው ግራ ሲገባን ስንት ዘመናችን!

አንድዬ:- እኮ አሁን ምን አድርግ ነው የምትለኝ?

ምስኪን ሀበሻ:- ተአምሩን ላክልና አንድዬ! ተአምሩን ላክልን! የሚያስተቃቅፈን፣ የሚያዋድደን፣ እኔ ትብስ አንቺ የሚያባብለን ተአምሩን ላክልና!

አንድዬ:- ተአምር ነው ያልከኝ… እስከ ዛሬ እንኳን አሁን ያልከው አይነት ተአምር ሰርቼም አላውቅ፣ ተጠይቄም አላውቅ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ ታዲያ ምን ይሻላል?

አንድዬ:- ችግሬ ምን መሰለህ…እናንተ አሁን እየሠራችሁት ያለው ጉድ እንኳን ህገ መጽሐፌ ላይ ሊሰፍር እኔ ራሴ ብዙዎቹን አላውቃቸውም፡፡ ምን እንደማደርግ እነግርሀለሁ…

ምስኪን ሀበሻ:- ምን አንድዬ፣ ምን?

አንድዬ:- የምፅአት ቀን ሲመጣ…ደግሞ ሩቅም አይደል…ያኔ እናንተን የምቀጣበትም፣ የምምርበትም የህግ አንቅጽ ስለሌለኝና ነገራችሁ ሁሉ ለእኔም የቸገረ ነገር ስለሆነ፣ ለብቻችሁ አንድ ቦታ አሰባስባችሁና ከፈለጋችሁ ማንም ጣልቃ ሳይገባባችሁ ምድር ላይ የጀመራችሁትን እዛው ትጨርሱታላችሁ፡፡

ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ!

አንድዬ:- ጨርሻለሁ፡፡

አንድዬም ወደሌሎቹ አትኩሮቱን አዞረ… የምስኪኑ ሀበሻ እጆች አሁንም እንደተዘረጉ ናቸው፡፡

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

Read 2031 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:43