Saturday, 14 July 2012 07:27

ሰኔ 30 እና የእኛ ተማሪነት

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(8 votes)

ካለፈው የቀጠለ

“ወርቅ”ም በለው “ሳንቲም” መዝሙሩ እንደሆነ ያው ነው!

ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት “ሰኔ 30 እና የእኛ ተማሪነት” የሚል ፅሁፍ ላይ አስተያየት ለመስጠት የፈለገ ወዳጄ ስልክ ደወለልኝ፡፡

“የሆነ ነገር አሳስተሃል” አለኝ፡፡

“ምን አይነት ነገር?” ጠየቅኩት፡፡

“የመዝሙር ግጥም” መለሰልኝ፡፡

“ምን የሚለው መዝሙር?” መልሼ ጠየቅኩት፡፡

“…እነ ወለቴ ቤት

ጠጄን ስቀመቅም፣

ሚስቴ ወልዳ ቆየች

አባቱን አላውቅም፣

አራዳ ሸርሙጣ

ጉድ አደረገችኝ፣

አመዱን በጥብጣ

ጠጅ ነው አለችኝ፣

እኔም በበኩሌ

ጉድ አደረግኳት፣

ቆርቆሮ ቀጥቅጬ

ሳንቲም ነው አልኳት፣

…” የሚለው መዝሙር ላይ” አለኝ፡፡

እርግጥ ነው፣ ይህ መዝሙር ባለፈው ሳምንት ፅሁፌ “የሚገርመኝ የተማሪነት ዘመኔ መዝሙሮች ብዬ ከጠቀስኳቸው አንዱ ነበር፡፡

“ታዲያ ምኑ ላይ ነው የተሳሳትኩት?” በማለት ጠየቅኩት፡፡

“የመጨረሻው መስመር ላይ!...” ‘ሳንቲም ነው አልኳት’ የሚለው ተሳስቷል፡፡ ‘ወርቅ ነው አልኳት’ ነበር መሆን ያለበት” ሲል አስተያየቱን ሰጠኝ ወዳጄ፡፡ አስተያየቱን ለመቀበል አላመነታሁም፡፡ ምክንያቱም የገጠር ተማሪነት ‘ሳንቲም ነው አልኳት’ ብላ የደፋችውን ግጥም፣ የከተማ ተማሪነት ‘ወርቅ ነው አልኳት’ ብላ ልትደፋው ትችላለች፡፡

የሆነው ሆኖ፣ ‘ወርቅ’ም አልነው ‘ሳንቲም’ ሁላችንም የማታለል ጥበብ የሚያስተምረውን ይሄን ጠማማ መዝሙር ስናቀነቅን ያደግን የድሮ ተማሪዎች ነን፡፡

ለማንኛውም ቅን አስተያየትህን ፈጥነት ለሰጠኸኝ ወዳጄ፣ እነሆ ፈጣን ምስጋና - ያልረፈደበት!

“ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው!” የሚለውን ጥቅስ የትና መቼ እንዳነበብኩት አልረሳም፡፡

ተማሪ እያለሁ፣ የትምህርት ቤታችን ዋና በር ላይ ተለጥፎ ነው ያነበብኩት፡፡ ያኔ ልጅ እያለሁ “አርፋጅ” ተብዬ የት/ቤቱ በር እንዳይዘጋብኝ በመስጋት እጣደፍ ስለነበር ከበሩ ላይ የተለጠፈውን ጥቅስ ረጋ ብዬ የማስብበት ጊዜ አልነበረኝም፡፡

አሁን ግን ጥቅሱን እያሰብኩ አሰላሰልኩ፡፡ “ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው!” ብሎ ጥቅስ ጭፍንና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ አባባል እንደሆነ ተሰማኝ፡፡

በእኛ ዘመን የሚያረፍዱ ተማሪዎች ሁሉ ሰነፎች ነበሩ ለማለት ያዳግተኛል፡፡ እውነቴን እኮ ነው! … የዳቦ ቤት ወረፋ በመብዛቱ በሰአቱ ቁርሱን በልቶ ትምህርት ቤት መድረስ ያልቻለ አርፋጅ ተማሪ ሁሉ “ሰነፍ” ሊባል ነው እንዴ? በዚያ ዘመን ‘ላንች ቦክስ’ የት አለና? … በ‘ፔርሙዝ ሰሃን’ በወጉ የተቋጠረ ምግብ ይዞ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄድ ተማሪ መች ነበረና? …

እንደዚህ ዘመን ተማሪዎች ቁርስ በሰአቱ መብላት፣ ምሳ በ‘ባግ’ ቋጥሮ በጊዜ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ በእኛ ዘመን አልነበረም፡ (በነገራችን ላይ የብዙዎቻችን ‘ባግ’ ምን እንደነበር ታስታውሳላችሁ?.. የ‘ዱቤ ዱቄት’ ላስቲክ!)

ቁርስ እስኪደርስ ጠብቆ ለመብላት ማርፈድ የግድ ነበር፡፡ እንፋሎቱ ያልበረደ ትኩስ ቂጣ እየጐመደ ቁርሱን በመንገድ ላይ ሩጫ የበላ አርፋጅ ተማሪ ሁሉ ሰነፍ ሊባል ነው እንዴ?

ወደ ትዝታችን እንመለስ … ወደ እኛ ተማሪነት … ‘ዴይ ፓርቲ’፣ ‘ላንች ቦክስ’፣ ‘ፕላዝማ’ … ሁሉንም ወደማታውቅ ወደ እኛ ተማሪነት እንጓዝ - በኋላ ማርሽ!

ይህ የ‘እጅ ስራ’ ክፍለ ጊዜ ነው!

‘በየካቲት ወራት

ቦንድ ፈንድቶ

አገሬ ታጠቀች

የህብረት ቀበቶ…’ ብለን የዘመርንበት የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ አልቆ፣ በስፖርት ክፍለ ጊዜ ‘ጃ ቀኝ መንገዱ ራቀኝ’ እያልን ሰልፍ ስንለማመድ ቆይተን፣ ደወሉ ተደወለና የእጅ ስራ ክፍለ ጊዜ ላይ ደረስን፡፡ ‘የእጅ ስራ’ ትምህርት ተማሪው የተለያዩ የዕደ ጥበብ ስራዎችን የመስራት ክህሎቱን እንዲያሳድግ በሚል የሚሰጥ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል … ለትምህርቱ የተመደበውን ጊዜ የምናሳልፈው ግን የ”እጅ ስራ” ሳይሆን ‘የጅል ስራ’ በመስራት ነበር፡፡

ክፍለ ጊዜው ሲደርስ ከክፍል ወጥተን በሰልፍ ወደ እጅ ስራ ማዕከል እናመራለን፡፡ በእድሜ ገፋ ያሉት በተለይም ከገጠር አካባቢ የሚመጡት ተማሪዎች ገመድ ይፈትላሉ፣ ሰሌን ይሰራሉ፣ የወለል ምንጣፍ ያበጃሉ፡፡

(ሁሉም የወላጆች ቀን ሲደርስ የሚሸጡ ናቸው) ሌሎቻችን ወለል ላይ ቁጭ እንላለን፡፡

‘በሉ የእጅ ስራችሁን አውጡ’ ይሉናል መምህሩ፡፡ አንዳንዶቻችን የከብት ቀንድ አንስተን በስባሪ መስታወት እየፈቀፈቅን የወፍ ቅርፅ ወይም ዋንጫ ለመስራት እንሞክራለን፡፡

ሌሎቻችን ቆርኪ ውስጥ የምትገኘዋን ላስቲክ እርስ በርስ በማስተሳሰር ቀበቶ ለመስራት እንተጋለን፡፡ ሌሎቻችንም ሌላ…ሌላ… የእጅ ስራን ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም ግርም የሚለኝ ችሎታችንን የሚያሳድግ ትምህርት እንደማንማር ሁሉ፣ መቻላችንን የሚያረጋግጥ ፈተና አለመፈተናችን ነው፡፡

“ፈተና ደርሷል..የእጅ ስራችሁን አስረክቡ” እንባላለን፡፡ ይሄኔ ነው ሩጫ  - የእጅ ስራ ውጤታችንን ከየትም ብለን ለማምጣትና ለመምህሩ ለማቅረብ፡፡ መምህሩ ስማችንን በየተራ እየጠሩ ያመጣነውን ነገር ይቀበላሉ፡፡

ተቀብለው ያዩትና አገላብጠው ከገመገሙት በኋላ በማርክ መስጫ ደብተራቸው ላይ የመሰላቸውን ውጤት ይፅፋሉ፡፡ ተማሪው ያቀረበው ነገር የራሱ ስራ ውጤት ይሁን አይሁን ጉዳያቸው አይደለም፡፡

ይሄን ስለምናውቅ ታዲያ … የእጅ ስራ ማስረከቢያ ቀን ሲደርስ ሩጫችን ወደ ገበያ ነበር፡፡

መንፈቅ ሙሉ እጁ እየተላላጠ ቆርጦና ቀጥሎ ‘የጣውላ ክላሽ’ የሰራ ትጉህ ተማሪ ከ50ው 20 ሲያገኝ፣ ገበያ ወርዶ በገንዘብ የገዛውን የቡና ሙቀጫ ያስረከበ ተማሪ ከ50ው 50 ይሰጠዋል፡፡

እውነቱን ለመናገር የእጅ ስራ በሚሉት ትምህርት ከተማሪው ይልቅ አስተማሪው የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይሄን የምለው በወቅቱ የነበረውን የትምህርት ስርአት ለመተቸት አይደለም፡፡ የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ከገበያ ገዝቼ ለእጅ ስራ ፈተና ያስረከብኳትንና ከ50ው 50 ያገኘሁባትን የፎቶ ፍሬም የእጅ ስራ አስተማሪያችን ቤት ውስጥ ስላየኋት እንጂ፡፡ ትዝ ይለኛል… አስተማሪያችን ወንድማቸውን ቀብረው ሀዘን ተቀምጠው ስለነበር እኛ ተማሪዎቻቸው የእዝን አዋጥተን ቤታቸው ሄድን፡፡ አስተማሪያችን ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ የተንጠለጠሉት ፎቶግራፎች በሙሉ (ከሟች በስተቀር) በባህላችን መሰረት ተገልብጠው ነበር፡፡ ከእነዚያ ተገልብጠው የተንጠለጠሉ የፎቶግራፍ ፍሬሞች መካከል አንደኛው የእኔ መሆኑን ያወቅሁት ከጥቂት ማንጋጠጥ በኋላ ነው፡፡ ፍሬሙ የእኔ የእጅ ስራ መሆኑን ያረጋገጥኩት ከበስተጀርባው ባለው የእኔ የእጅ ፅሁፍ አማካይነት ነው፡፡ እንዲህ በሚለው፡-

“ስም፡- አንተነህ ይግዛው

ክፍል፡- 4ኛዲ

የት/አይነት፡- የእጅ ስራ”

***

ሦስተኛው ‘ፔሬድ’ መጣ … የአማርኛ ክፍለ ጊዜ … “በዚህ ግቢ ውስጥ አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው!’ የሚል ማስጠንቀቂያ በተለጠፈበት ‘እንትን አካዳሚ’ ውስጥ የምትማሩ የዛሬ ዘመን ተማሪዎች ሆይ … ብታምኑም ባታምኑም በአንድ ወቅት በዚህች አገር ላይ ‘አማርኛ’ የሚባል የትምህርት አይነት ነበር፡፡ የአማርኛ ክፍለ ጊዜ፣ የአማርኛ መምህር፣ የአማርኛ መፅሐፍ፣ የአማርኛ ደብተር ወዘተ የነበረበት የተማሪነት ጊዜ ነበር - የእኛ ተማሪነት! ይህ ‘የአማርኛ ክፍለ ጊዜ’ ነው!... ይህን ‘ክፍለ ጊዜ’ ጊዜ አይሽረውም፡፡ የአማርኛ ትምህርት ትዝታዎቼን የስርአተ ትምህርትም ሆነ የጊዜ ለውጥ አይደመስሳቸውም! የአንደኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መፅሐፌን ወደ ሁለተኛ ክፍል ስዛወር ለሆምሩም ቲቸሬ መልሼ ባስረክብም ትዝታው ግን አሁንም ከእኔው ጋር ነው፡፡

የሆነ አልበም የሚመስል በስዕል ያሸበረቀ መፅሐፍ ነበር፡፡ የተለያዩ ስዕሎች ነበሩት - ከስራቸው ደግሞ የስዕሎቹን ምንነት የሚገልፁ ፅሁፎች፡፡

ቀ - ቀበቶ

ፓ - ፓስታ

ቂ - ቂጣ

ሸ - ሸሚዝ … ምናምን የሚሉ …

እና ደግሞ ምንባቦች፡፡ ‘ዘበርጋ ተመረጠ’፣ ‘ቶሎሳና ወርቅነሽ’፣ ‘የአጠባ ቀን’፣ … እና የመሳሰሉ አይረሴ ታሪኮች፡

በነገራችን ላይ … በአማርኛ መፅሐፍት ውስጥ (በተለይ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በነበሩት) የነበሩት ምንባቦች በልጅነት ልቦናችን ውስጥ ሰርፀው የመግባት አቅም የነበራቸው ይመስለኛል፡፡ ‘የአለሙ ድንክ አልጋ’፣ ‘ሽልንጌን’፣ ‘ታታሪው አየለ’፣ ‘የሃብቶም አበባ’፣ ‘ከቀንድ የሚሰራ የጫማ ማስገቢያ ማንኪያ’፣ ‘የአመቱ ወራት’፣ ‘ፋኖስና ብርጭቆ’፤ …ኧረ ስንቱ!

የሚገርመው ግን እነዚህ ምንባቦች በማን እንደተፃፉ የሚገልፅ ነገር በመፅሐፍቱ ላይ አለመገለፁ ነው፡፡ ‘ሽልንጌ’ን የመሰለ ትራጄዲ አንብቤ ከተገረምኩ ከአስራ ምናምን አመታት በኋላ፣ በቅርቡ የ‘ሽልንጌን’ ደራሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ መሆናቸውን ሰምቼ እንደገና ተገረምኩ፡፡

አማርኛ ትምህርትን ሳስብ ሁሌም የማይረሳኝ ምንባቦቹን ተከትሎ የሚመጡት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እርግጥም ‘መልመጃ አንድ’ እና ‘መልመጃ ሁለት’ እምብዛም አስቸጋሪ አልነበሩም፡፡ የ‘መልመጃ ሶስት’ን አስቸጋሪነት ለመግለፅ ግን አሁንም ይቸግረኛል፡፡

ከአማርኛ ‘መልመጃ 3’፣ ከሒሳብ ‘ማካፈል’ን አጥብቄ እጥላ ነበር፡፡ ከ‘እጅ ስራ’ና ከ‘ሙዚቃ’ በተሻለ፣ ‘አማርኛ’ ትምህርት የተማሪዎችን ችሎታና ተሰጥኦ በማዳበር ረገድ የተሳካለት የትምህርት አይነት እንደነበር ይሰማኛል፡፡

ቢያንስ ግጥም እንድንፅፍ የቤት ስራ ይስጠን ነበር፡፡ እርግጥ ብዙዎቻችን ከጋዜጣና ከመፅሐፍት የምናገኛቸውን ግጥሞች ገልብጠን፣ ወይንም መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን የራሳችን አስመስለን ነበር የምናቀርበው፡፡ የራሳቸውን ፈጠራ የሚያቀርቡ ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ - እንደ ብርሐኑ ያሉ፡፡ የ5ኛ ክፍል ተማሪዎች እያለን ከብርሐኑ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ ነበር የምንማረው፡፡

አንድ ዕለት መምህራችን ግጥም እንድንፅፍ አዘዙን፡፡ በነጋታውም ተራ በተራ እየወጣን ግጥሞቻችንን እንድናነብ ዕድል ሰጡን፡፡ የብርሐኑ ተራ ደረሰና ግጥሙን ሊያነብ ወጣ፡፡ እናም የሚከተለውን ግጥም (?) አቀረበ፡፡

“ከእኛ መንደር በታች

ይሸጣል ፓፓዬ

የዚህ ግጥም ደራሲ

ብርሃኑ ገላዬ ”

…. በቃ! … የሚገርመው ግን መምህሩ ‘ግጥሙ አጠረ’ ወይም ‘የየትኛው ግጥም ደራሲ?’ ብለው አልጠየቁም፡፡ (ምናልባት ‘ግጥም በባህሪው አጭር ነው’ የሚለውን ነገር ስለሚያውቁ ይሆናል)

‘እጅግ በጣም ጥሩ’ ብለው ከረጅም ‘ራይት’ ጋር ችሎታውን መሰከሩለት፡፡ ብርሐኑ ከዚያ በኋላ ግጥም ይፃፍ፣ አይፃፍ … የስነ ፅሁፍ ችሎታውን ያሳድግ፣ አያሳድግ አላውቅም፡፡ የማውቀው የእኔ የስዕል ችሎታ አለማደጉን ብቻ ነው፡፡ 3ኛ ክፍል እያለሁ የምስላትን ጐጆ ቤት ነው አሁንም የምስለው፡፡ በአማርኛ ክፍለ ጊዜ ስለ ስዕል ማውራት ተገቢ ባይሆንም አንዲት ነገር ብቻ ልበል፡፡ ሰው የመሳል ጥበብ የተማርነው ከየት እንደነበር ትዝ ይላችኋል? … ከኤርትራ፡፡

ታዲያስ! ..

ብለን ወደታች እንፅፍና ‘ኤ’ን ከ‘ራ’ ጋር በጠማማ መስመር እናገኛታለን፡፡ ሰው ሳልን ማለት አይደል?

ከአስሩ ስንት ሰጣችሁኝ? ሳምንት እንቀጥላለን፡፡

 

 

Read 7088 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:41