Saturday, 04 July 2020 00:00

መንግስት ትዕግስቱ ማለቁንና እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


      - ሰሞኑን በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል
      - “በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት እርቅና ድርድር አይኖርም” - አቶ ሽመልስ አብዲሣ

                 የታዋቂውና ተወዳጁ የኦሮሚኛ የትግል ሙዚቃዎች አቀንቃኝ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣ ህልፈትን ተከትሎ፤ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በተፈጠሩ ሁከትና ግርግሮች ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና በተለያዩ ከተሞች በርካታ የዜጐች የመንግስት ንብረቶች መውደማቸው የተገለፀ ሲሆን፤ መንግስት ትዕግስቱ መሟጠጡንና ከዚህ በኋላ እርምጃዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታወቀ፡፡
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ገደማ በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ለጊዜው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተደብድቦ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ተከትሎ፣ ሌሊቱን በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ መረጃዎች ሲሰራጩ ያደሩ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ከሌሊቱ 8፡30 ገደማ የአርቲስቱን ህይወት ማለፍ አረጋግጠው ሃዘናቸውን የገለፁበትን መልዕክት ማስተላለፍ ችለዋል፡፡
የተወዳጁ አርቲስት የህልፈት መርዶ በማህበራዊ መገናኛዎች መነገሩን ተከትሎም፣ በትውልድ ከተማው አምቦና ህይወቱ ያለፈበት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በድርጊቱ የተቆጡ ወጣቶች መንገድ በመዝጋት፣ ጐማ በማቃጠል ቁጣቸውን ሲገልፁ ማደራቸውን ዩአዲስ አድማስ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከንጋት በኋላም የሃዘን መርዶውን የሚሰሙ ወጣቶች ቁጣውን እየተቀላቀሉ የመጡ ሲሆን፤  ሃዘንና ቁጣው ወደ ግርግርና ሁከት ተቀይሮ የዜጐች ንብረት ወደ ማውደምና የሰው ህይወት ማጥፋት መለወጡን የባቱ (ዝዋይ)፣ ሻሸመኔና አምቦ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ከፍተኛ ጉዳት ባስተናገደችው ባቱ (ዝዋይ) ከተማ፣ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰአት ገደማ ጀምሮ በጐዳናዎች ላይ ወጣቶች መሰባሰባቸውን፣ በዋና ዋና አስፓልት መንገዶች ላይም እየተዘዋወሩ ሀዘናቸውንና ቁጣቸዋን መግለፃቸውን፣ ኋላም ጉዳዩ ወደ ሁከትና ግርግር አምርቶ የበርካታ ግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ መደብሮችና የአበባ እርሻ ጣቢያዎችን ወደ ማውደም መሸጋገራቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በእለቱም በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና አምቡላንሶች ተጐጂዎችን ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ የሰው ህይወት ማለፉንም አስታውቀዋል፡፡
በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የትውልድ ከተማ አምቦና በአካባቢው ባሉ አነስተኛ ከተሞችም ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙን፣ ወጣቶች ጐዳናዎችን በድንጋይና በእንጨት መዝጋታቸውን፣ ቁጣቸውን በዋና ዋና አውራ ጐዳዎች ላይ በመመላለስ ሲገልፁ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ከባድ የመሣሪያ ተኩስ መሰማቱን፣ የቦንብ ፍንዳታ መከሰቱንና የሰዎች ህይወት ማለፉን ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነርም በከተማዋ በሀዘንተኞች ቤት ላይ በተወረወረው ቦንብ የአርቲስቱ አጐት ህይወት ማለፉንና በርካቶች መጐዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የቀብር ስነስርዓቱ በተፈፀመ እለትም በከተማዋ በተፈጠረ ሁከትና ግርግር የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በሻሸመኔ ከተማም በተመሳሳይ በርካታ የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎችና መኖሪያ ቤቶች መዘረፋቸውን፣ መስታወቶቻቸው በድንጋይ መሰባበሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሃረማያ፣ አሰላ፣ ጭሮ፣ ወሊሶ፣ ሞያሌን ጨምሮ በርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተመሳሳይ ክስተት ማስተናገዳቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ ወደ አብዛሃኞቹ የክልሉ ከተሞች የሚያስገቡ አውራ ጐዳናዎችም በድንጋይና በእንጨት በመዘጋታቸው እስከ ትናንት ድረስ በክልሉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኦሮሚያ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ፤ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች ከትናንት በስቲያ ጀምሮ አንፃራዊ ሠላም መስፈኑን አመልክቶ መደበኛ የሰዎች እንቅስቃሴም በትናንትናው እለት መጀመሩን፣ የተዘጋጉ መንገዶችንም የመክፈት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በአርቲስቱ ህልፈትና በአጠቃላይ በክልሉ በተፈጠረው ችግር በእንባ በታጀበ ገጽታ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ በበኩላቸው፤ “ግድያውን ያቀነባበሩት “ኦነግ ሽኔ” እና “ወያኔ” ተቀናጅተው ነው” ብለዋል፡፡ አላማውም ሀገሪቱን መበታተን፣ ኦሮሞን እርስ በእርሱ ማባላትና ኦሮሞን ከሌላው ብሔር ጋር ማጋጨት እንደነበር በመግለጽ፣ ያለሙት አልተሳካላቸውም፤ ለወደፊትም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
የአርቲስቱን ህልፈት ተከትሎ አስከሬኑን በማንገላታት የተፈፀመውን በደል በዝርዝር በመግለጫቸው ያስረዱት አቶ ሽመልስ፤ አስከሬኑ ወደ አምቦ እያመራ ባለበት ሁኔታ ከመንገድ ላይ በመመለስ ከ20 በላይ የተለያየ መሣሪያ በመታጠቅ ከፍተኛ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር መሞከሩን፣ በዚህም የአንድ ፀጥታ ሃይል አባል ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት በቤተሰቡ ጥያቄ መሠረት አስከሬኑን ወደ አምቦ ካደረሰ በኋላም የኦነግ ሽኔ እና ወያኔ ሃይሎች ተጣምረው በአምቦ ከተማ በቦንብና በመሣሪያዎች በመጠቀም ጦርነት ከፍተው በርካታ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የሃጫሉን አጐት መግደላቸውን የመንግስት ፀጥታ ሃይሎችም ላይ ግድያ መፈፀማቸውን አስታውቀዋል፡፡ “ሃጫሉ ለሰው ልጅ ነፃነትና እኩልነት እንጂ ለሰው ውድቀት ቆሞ አያውቅም ሃጫሉ አንድ ቀን ይገድሉኛል እንዳለ ነው የገደሉት” ያሉት አቶ ሽመልስ፤ “በአስከሬኑ ላይ በፈፀሙት ድርጊትም ደግመው ደጋግመው ነው የገደሉት” ብለዋል - በቁጣና በምሬት፡፡
“ድርጊቱን የፈፀሙት የኦሮሞን ህዝብ እርስ በእርሱ ለማጣላት፣ የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ጋር ለማባላት ነው፤ ይህም አልተሳካላቸውም፤ ለወደፊትም አይሳካላቸውም” ብለዋል አቶ ሽመልስ፡፡
የአርቲስት ሃጫሉን ጀግንነትና በጐ ተግባራት በንግግራቸው ያወሱት አቶ ሽመልስ፤ “ሃጫሉ የኦሮሞ ህዝብ በተፈናቀለበትና ሁላችንም ፈርተን ባለንበት ወቅት ፊት ለፊት ወጥቶ ኦሮሞ ድሉ ያንተ ነው፤ ፈጥነህ ድል አድርግ ብሎ መድረክ ላይ ፊት ለፊት በዜማው መልዕክት ያስተላለፈ ታንክና መድፍ የማያስፈራው ጀግና ነው ሲሉት አወድሰውታል፡፡
“ይሄን ጀግና የማንም መንገደኛ፣ ፈርቶ ተደብቆ የነበረ ሁሉ፣ ከሀገሩ ሸሽቶ ወጥቶ የነበረና ኋላም በለውጡ ፌስታሉን አንጠልጥሎ ሲመጣ የተቀበልነው ሁሉ ነው በጠላትነት ያየው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሃጫሉን ጠላት ያደረጉት ፊት ለፊት ስለተናገረ ነው ብለዋል፡፡
ከሣምንት በፊትም አርቲስቱን በቴሌቪዥን ጣቢያ በማቅረብ አስጨናቂ የሆኑ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለእርድ ሲያዘጋጁት ነበር ብለዋል - አቶ ሽመልስ በንግግራቸው፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ግድያም በርካታ ሴራ ያለበት የለውጠ ሂደቱን ለማኮላሸትና ሀገሪቱን ለማፈራረስ የተደረገ ጥረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ በኋላ ይህን ጥረት ሙሉ ለሙሉ አስፈላጊውን እርምጃ ወስደን እናስቆማለን፤ ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ የሚጥሩትን በሙሉ ጠራርገን ወደ መስመር እናስገባለን ብለዋል፡፡ የመንግስት ትዕግስት መሟጠጡንም አቶ ሽመልስ በዚህ መልዕክታቸው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም “የኦሮሞ ህዝብ ሆኖ ቀዬህን ጠብቅ፣ ከሌሎች ብሔሮች ጋር አትጋጭ” የሚል መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ሽመልስ፤ “እንደ ኦሮሚያ ክልል መንግስት የማረጋገጥላችሁ ያለ ምንም እርቅ የጀመርነውን ህግን የማስከበር ሂደት የምንቀጥል መሆናችንን ነው ብለዋል፡፡
የአርቲስቱን ህለፈት ተከትሎ በተፈጠሩ ሁከትና ግርግሮች በአዲስ አበባ ከተማ 3 የፀጥታ አካላትና 8 ግለሰቦች መገደላቸው እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል 4 የፀጥታ ሃይሎችና 87 ዜጐች መሞታቸውን የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Read 3117 times