Saturday, 04 July 2020 00:00

ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በ1972 ዓ.ም በቀድሞው የጋሞጐፋ ዞን ጋርዱላ አውራጃ፣ ጊዶሌ ከተማ፣ ከአባቱ ከአቶ አሰፋ ግዛውና ከእናቱ ወ/ሮ እቴነሽ በሃሶ የተወለደው ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ በደረሰበት የስትሮክ ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትላንት አርብ ሰኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከ1-4ኛ ክፍል በትውልድ ቀየው ጊዶሌ ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እስከ 8ኛ ክፍል መማሩንና ከ8ኛ-12ኛ ክፍል ወደ ትውልድ ቀየው በመመለስ መከታተሉን የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡
በ1990 ዓ.ም ከአርባ ምንጭ መምህራን ኮሌጅ በሰርተፍኬት ተመርቆ በጋርዱላ አውራጃ በጋማሽሌ የተባለ የገጠር ት/ቤት ሲያስተምር የቆየ ሲሆን፤ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቆ፣ በየማነ ብርሃን ት/ቤት አስከ 1996 ዓ.ም ማስተማሩም ታውቋል፡፡ ታታሪውና ተግባቢው ካሳሁን እያስተማረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርቱን በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ በፋና ሬዲዮ ለ8 አመታት ያህል በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን፤ ከዚያም ወጥቶ በግሉ ኢካሽ ፕሮሞሽንን በመመስረት በብስራት 101.1 ሬዲዮ “አሻም” የተሰኘ ማህበረሰብ ተኮር ፕሮግራም ከጓደኞቹ ጋር በማዘጋጀትና በማቅረብ ተወዳጅነትን አትርፏል:: ካሳሁን ከጋዜጠኝነቱም በተጨማሪ የተዋጣለት የማስታወቂያ ባለሙያም ነበር:: በተጫዋችነቱና በቅነ አመለካከቱ በብዙ የሙያ አጋሮቹ ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ካሳሁን፤ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ባህርዳር ለስራ (ለእቦጭ ነቀላ) ከሙያ አጋሮቹ ጋር በተጓዘበት ወቅት ባጋጠመው የስትሮክ ህመም በቤተዛታ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በትላንትናው ዕለት ከቀኑ 10፡00 ህይወቱ አልፏል፡፡
የቀብር ስነ ሥርዓቱ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9፡00 ለቡ በሚገኘው ምስራቅ ፀሐይ ገብርኤል ዘመድ ወዳጆቹና ጓደኞቹ በተገኙበት እንደሚፈፀም ቤተሰቦቹ ገልፀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ካሳሁን ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባትም ነበር፡፡  

Read 1198 times