Tuesday, 30 June 2020 00:00

የጣና ሃይቅ ታሟል!?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - ጣና ከሌለ ባህር ዳር ላይ መኖር አይቻልም
     - ጣናን በመታደግ ጥረት የፌደራል መንግሥት ሚና ምን ይመስላል?
     - ማህበራዊ ሚዲያው ስለ እምቦጭ የሚያናፍሰው ጣናን ከእነ ጭራሹ የሚያጠፋ ነው
                

           ቅጠሉ አረንጓዴና ማራኪ ነው እጅግ አይን የሚስብ ወይን ጠጅ ቀለም አበባ አለው። ስነ ሕይወታዊ ባህሪው አስቸጋሪና ውስብስብ ነው። በቅጠሉም በግንዱም በስሩም በቀላሉ መራባት፣ በሳምንት አምስት እጥፍ ራሱን ማራባትና በሀይቁ ላይ እንደ ብርድ ልብስ ተዘርግቶ በውስጡ ያሉትን ብዝሃ ሕይወቶች ኦክስጅን በማሳጣት ድራሻቸውን ያጠፋቸዋል። እንደ ብርድ ልብስ የተዘረጋበትን የውሃ ክፍል ከሌላው አምስት እጥፍ በማትነን የውሃውን ህልውናም በእጅጉ ይፈታተናል። በዓለማችን ላይ ከሚገኙ 10 አደገኛ አረሞች አንዱ የሆነው እምቦጭ አረም፤ በእንግሊዝኛው “ዋተር ሀይሲን” እየተባለ ይጠራል። ይህ አረም በተለያዩ የዓለም አገራት ለብዙ ሀይቆች ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ቪክቶሪያ ሀይቅን ከዚህ አረም ለማላቀቅ የ20 ዓመት ተጋድሎ ጠይቋል። እንደ ዋዛ በአገራችን በሚሊኒየም (2000 ዓ.ም) መጨረሻ ነሐሴ ወር ላይ ነበር በጣና ላይ መልኩን አሳምሮ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው። ከአራት ዓመታት በኋላ ነው በጥናት አደገኛ አረም መሆኑ ተደርሶበት ርብርብ ማድረግ የተጀመረው።
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የአረሙ አደገኛነት ከተረጋገጠ በኋላ ከሌሎች ክልሎች የሚመጡትን ጨምሮ በየዓመቱ 250 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን አረሙን ለማጥፋት ርብርብ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እያደረጉም ነው። በኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ሀብቱ በተባበሩት መንግሥታት የባህል የትምህርትና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ሀብትነት የተመዘገበውና ለአባይ ወንዝ 60 በመቶውን ውሃ የሚገብረው ጣና፤ በአሁኑ ወቅት እንቦጭ ክፉኛ እያጠቃው ይገኛል። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? ለሚለው የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ምላሽ ይሰጣሉ።
የጣና አሁናዊ እውነታና ተግዳሮቶቹ
ይህ መልኩን ያሳመረ ሰይጣን ወይም ፈረንጆቹ “The Beautiful Devil” ብለው የሚጠሩት አደገኛ አረም ጣናን መውረሩን ተከትሎ፣ የክልሉ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እንደወሰደ ይናገራሉ ሀላፊው። እምቦጭ አደገኛና ሀይቁን ሊያጠፋ የሚችል አረም መሆኑን የክልሉ መንግሥት ሲያውቅ መጀመሪያ ያደረገው፣ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ ጉዳዩን የማሳወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ነበር። ከዚህ በኋላም ወደ ተግባር ለመግባት ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋላ፣ ግብረ ሀይል ተቋቁመ ይላሉ። ግብረ ሀይሉም ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከባህልና ቱሪዝም ከርዕሰ መስተዳድር፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣና የተሰባጠረ ነበር። ግብረ ሀይሉ በቀጥታ አረሙን ወደ ማስወገድ ተልዕኮ ሲገባ፣ በየአመቱ 250 ሚ ሰው በዘመቻው ላይ ይሳተፍና አረሙን ይነቅል ነበር።
በሀይቁ ዙሪያ ያሉ የዘጠኙም ወረዳዎች አርሶ አደሮች በዘመቻው ላይ መሳተፋቸውን የሚናገሩት ሀላፊው፤ ምንም እንኳን አዲስ አበባን ጨምሮ ከመላው አገሪቱ ሰዎች በዘመቻው ቢሳተፉም በዋናነት ግን የሐይቁ ዙሪያ አርሶ አደሮችና የአካባቢው ወጣቶች በየጊዜው በመደበኛነት የአረም ማስወገድ ስራውን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይህም አረሙን ከጣና ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በቂ ባለመሆኑ፣ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እያደረገም ነው ይላሉ። ምክንያቱም የክልሉ መንግሥት የጣና ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ አድርጎ ስለሚመለከት ነው ብለዋል።
አቶ ግዛቸው፣ “ጣና ከሌለ ባህርዳር ላይ መኖር አይቻልም፤ እንደ አገርም ሆነ በዓለም ደረጃ የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትል ግዙፍ ሀይቅ ነው፤ እንደውም ሀይቁ ከክልሉ ይልቅ በጣም የሚመለከተው የፌደራል መንግሥትን ነው” ይላሉ።    
ይህ እንዳለ ሆኖ የክልሉ መንግሥት ሀይቁን ለመታደግና ከአደጋ ለመጠበቅ በሀይቁ ዙሪያ የሚካሄዱ ግንባታዎችን ሙሉ በሙሉ ከመከልከልም ባሻገር ቀደም ብለው የተገነቡትም የንግድ ድርጅቶችና ሆቴሎች ወደ ሀይቁ የተበከለ ፍሳሽ እንዳይለቁ ለበርካታ ጊዜያት ኦዲት መደረጉንና አመርቂ ለውጥ ማምጣቱንም ከተጓዦች ጋር እሁድ ረፋድ በዩኒስን ሆቴል ባደረጉት ስብሰባና ውይይት ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት በእምቦጭ አረም ዙሪያ የተቋቋመው ግብረ ሀይል በቂ ነው ብሎ ባለማመኑ፣ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ኤጀንሲ ያቋቋመ ሲሆን ኤጀንሲው አጠቃላይ የጣናን ተፋሰስ ሥራ የሚሰራ ነው። ኤጀንሲው እቅድ አቅዶ ሰው ቀጥሮ፣ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፣ ለጊዜው ያለው የሰው ሀይል ጥቂት መሆኑን የሚናገሩት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊው፤ በሀይቁ ዙሪያ ስፔሻሊስቶችን ቀጥሮ ተደራጅቶ ወደ ተጠናከረ ሥራ እንዲገባ እየተሞከረ ነው ብለዋል።
ጣናን ወደ ጤናው ለመመለስ የገጠሙ ተግዳሮቶች
ጣናን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ አንዱና ዋናው ተግዳሮት የበጀት ጉዳይ ነው ይላሉ ሀላፊው። ይህንን ፈተና ለመጋፈጥና ሀብት ለማፈላለግ “ጣና ትረስት ፈንድ” መቋቋሙንና እስካሁን ባለው ሂደት 55 ሚ.ብር ገደማ መሰብሰቡን ጠቁመው፤ ይህንንም ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሌላኛው ተግዳሮት፣ ጣናን የወረረው ይህ አደገኛ አረም በሰው ጉልበት ብቻ ሊገፋ ባለመቻሉ፣ ምን አይነት ማሽን መጠቀምና አረሙን ማጥፋት ይቻላል በሚለው ላይ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ምሁራንን በማሰባሰብ፣ በተለይም ከባህር ዳር፣ ጎንደርና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንን በማስተባበር፣ ማሽኖች ተጠንተው እንዲገቡ የተደረጉ ሲሆን እነዚህን ማሽኖች ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር አዳዲስ በመሆናቸው የኦፕሬተሮች ሥልጠናና መሰል ስራዎች ብቻ ይቀራሉም ብለዋል።
ምንም እንኳ ቀደም ሲል የእምቦጭ ጉዳይ በፌደራል መንግሥት በኩል ትኩረት ያልነበረው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ይህንን ሀይቅ መታደግ፣ የህዳሴውን ግድብም መታደግ ነው በሚል የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶ አቋም የወሰደበት ከመሆኑም በላይ እስከ 300 ሚ.ብር በሚደርስ በጀት ማሽን ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
በመጀመሪያ የሀይቁ 4ሺህ ሄክታር ቦታ በእምቦጭ አረም ተወረሮ እንደነበር የሚገልፁት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ በክልሉ መንግሥት ቁርጠኝነት፣ በአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች እርብርብ ከሁሉም የአገራችን ክፍል እየመጡ በተሳተፉ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን ጉልበት ከአራት ሺህ ሄክታር አረም አሁን በተጨባጭ ሀይቁ ላይ ያለው 500 ሄክታር ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም የክልሉ መንግሥት ለችግሩ ትኩረት አልሰጠም እየተባለ ለሚነገረው ሀሰትነት ማሳያ ነው ብለዋል። የክልሉ መንግሥት፣ የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች ጣናን ለመታደግ የሚሰስቱት ጉልበትም ሆነ ሀብትም ወይም እውቀት እንደሌለም ሃላፊው አስረግጠው ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በዚህ ደረጃ ለሀይቁ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም አሁንም ፈተናዎች እንዳሉ የሚናገሩት ሀላፊው፣ አረሙ ከሀይቁ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ በዋናነት ተግዳሮት የሆነው በሀይቁ ዙሪያ መንገድ አለመኖሩ ሲሆን ይህም ሰው እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ አረሙን እንዳያጠፋ ዋና መሰናክል መሆኑን ይናገራሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በተጀመረው ስራ ከማክሰኚት ተገንጥሎ ወደ ሀይቁ የሚገባ የ20 ኪ.ሜትር መንገድ  ቢገነባም በቂ ባለመሆኑ የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሌላው ሀላፊው እንደ ተግዳሮት ያነሱት የእንቦጭን ሥነ ሕይወታዊ ባህሪ አደገኛነት ነው። ሰዎች ነቅለው አፅድተውት ሲሄዱ፣ አንዲት ብጣቂ ቅጠል ብትቀር እንኳን ወዲያው የማንሰራራትና የመስፋፋት ስነ ሕይወታዊ ባህሪ ስላለው ይሄ ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው በምሬት ይናገራሉ። (በነገራችን ላይ አረሙ “እምቦጭ” የሚለውን ስያሜ እንዴት እንዳገኘ በእምቦጭ ነቀላ ሥራ ላይ እያለን የአካባቢው አርሶ አደሮች የነገሩንን እዚህ ላይ መጥቀስ የሀላፊውን ሀሳብ ያንፀባርቃል። አረሙ ገና እንደመጣ ጣናን እያለበሰው ሲሄድ አርሶ አደሮች ሰግተው እልም አድርገው ነቅለው ከሀይቁ ላይ አስወግደውት ሄዱና ሌላ ቀን ተመልሰው ሲያዩት፣ መጀመሪያ ካዩት በእጥፍ ጨምሮ አገኙት። አሁንም ሙልጭ አድርገው አርመው ሄዱና ሌላ ቀን ሲመለሱ፣ በእጅጉ ተስፋፍቶ አገኙት። ከዛ ከአርሶ አደሮቹ አንዱ “አይ ይሄ ነገር ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው” በማለታቸው የአረሙ አገርኛ ስያሜ “እምቦጭ” ሆኖ መቀጠሉን አጫውተውናል…)
ሕዝቡ አረሙ ላይ ከመረባረቡ የተነሳ በ2007 ዓ.ም አረሙ ከሀይቁ ላይ ጠፋ ተብሎ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ ተሸልመው ሁሉ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ ከአረሙ ባህሪ አኳያ ትንሽም ነገር ከቀረ በቅጠሉም በግንዱም በስሩም ስለሚራባ፣ ወዲያውኑ ሀይቁን መውረር መጀመሩን ጠቁመው፣ ችግሩ ውስብስብ በመሆኑ ከዚህም በላይ ጉልበት፣ ጥናትና በጀት የሚጠይቅ ነው በማለት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያስረዳሉ። ስለዚህም አሁን ከገቡት ማሽኖች በላይ ዘመናዊ ማሽኖችና በኬሚካል የሚጠፋውም በኬሚካል እንዲጠፋ ለማድረግ፣ ቀን ከሌት መስራት እንደሚጠይቅ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ሌላው ሀይቁን ለመታደግ ተግዳሮት የሆነው፣ ወደ ጣና ውሃ የሚገባበት ሰፊ የተፋሰስ ቦታ ነው። እንደ ሀላፊው ገለፃ፤ ወደ ጣና ውሃ የሚገባበት 1.5 ሚ ሄክታር የሚሸፍን ተፋሰስ አለ፤ ይህን ተፋሰስ ማልማት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑንም ሃላፊው ያሰምሩበታል። ከዚህ ሁሉ ሄክታር ተፋሰስ ተጠራርጎ የሚገባው አፈር ሙሉ ለሙሉ ወደ ጣና መግባቱ ለአረሙ እንደ ልብ መስፋፋት ምቹ ሁኔታም ፈጥሮለታል ይላሉ። (በሌላ በኩል ከተፋሰሱ በብዛት ወደ ሀይቁ የሚገባው ደለል የሀይቁን ጥልቀት እየቀነሰው በመሆኑ ይህም ይታሰብበት ሲሉ የሊቦ ከምከም ወረዳ ወጣቶች ለጋዜጠኞች በተማጽኖ ተናግረዋል)፣ ሀላፊውም ተፋሰሱን ማልማት ትልቅ ትኩረትና ቅድሚያ ሊያገኝ እንደሚገባው ጠቁመው፣ ተፋሰሱ ካልለማ ግን ጣናን መታደግ እንደማይቻል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ሀላፊው እንደሚሉት፤ ጣናን ከእምቦጭም ሆነ ከተፋሰሱ ከሚገባው ደለል ለመታደግ የሚያስፈልገው በጀት ብዙ ቢሊዮን ብር እንደሚጠይቅና ከክልሉ አቅም በላይ እንደሆነ አብራርተው ይህንን ሀይቅ ለመታደግ ከፌደራል መንግሥትም ከውጭም፣ ከሌሎችም ረጂ አካላት ሀብት በማፈላለግ አቅምን አጎልብቶ፣ ሀይቁን መታደግ ዛሬ ነገ የማይባል ሥራ ነው ብለዋል። ሌላው ለሀይቁ ለአደጋ መጋለጥ እንደ ተግዳሮት የተቀመጠው፤ ጉዳይ በሀይቁ ዙሪያ የ“በፈር ዞን” አለመኖር ነው አንድ በዓለም ሀብትነት የሚመዘገብ ቅርስ ወይም ሀብት ጥበቃ የሚደረግለት ራሱ ቅርሱ ወይም ሀብቱ ብቻ ሳይሆን ዙሪያው ሁሉ ያሉ ከሀይቁ ጋር ተዋሳኝነት ያላቸው ቦታዎች ናቸው። ከዚህ አኳያ ጣና ምንም አይነት የበፈር ዞን ጥበቃ እንደሌለው የሚገልፁት የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ፣ በሀይቁ ዙሪያ ባሉ ዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ጣና ዳር ላይ መሬት ያላቸውና በጣና አልምተው የሚኖሩ መሆናቸው ተጨማሪ ችግር መሆኑን ይናገራሉ። ስለዚህ ጣና “በፈር ዞን” እንዲኖረው እነዚህን አርሶ አደሮች ከኖሩበትና ተወልደው ካደጉበት ቀያቸው ማንሳት ይጠበቅብናል ይላሉ። ይህን ለማድረግ ትልቅ ካፒታል፣ መተማመንና እነሱን ማሳመን ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ ይህንንም መስራት በቀጣይ አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል። የሀይቁ ዙሪያ ቢያንስ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ዙሪያውን በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ወይም በጤናማ ሳር መሸፈንና ከሰውም ሆነ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ መስራት የግድ የሚል ቢሆንም ይህም ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ከፊት ለፊት የተደቀነ ጉዳይ ነው ይላሉ።
ሌላውና በመጨረሻ ያነሱት ጣናን ለመታደግ እንቅፋት የሆነው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ችግር ነው። “የፖለቲካ አክቲቪዝሙና ሶሻል ሚዲያው ስለ እምቦጭ የሚያወራው ጣናን ከነጭራሹ የሚያጠፋ እንጂ የሚታደግ አይደለም”    
ያሉት ሃላፊው፤ በሶሻል ሚዲያ የሚናፈሰው የተዛባ መረጃ፤ በፖለቲካ አክቲቪዝሙም ቢሆን የክልሉ መንግስት ለጣና ምንም ዴንታ እንደሌለው እያደረጉ ሃሰተኛ መረጃ ማናፈስ ከስነ ምግባርም ሆነ ከሞራልም አንፃር ያልተገባና ጣናን ለመታደግ ፋይዳ የሌለው ነው ሲሉ ማህበራዊ ሚዲያውን ወርፈዋል፡፡ ደብረ ማርቆስ የሚገኙት መሪጌታ በላይ አዳሙ አገኘሁ ያሉት መፍትሄም በማህበራዊ ሚዲያው ክልሉ አልተቀበላቸውም ተብሎ እንደሚናፈሰው ሳይሆን የሚያስከትለው ተፅዕኖና መሰል ነገር መጠናትና ማረጋገጫ ማግኘት አለበት መባሉን አስታውሰዋል።  
በውይይቱ ላይ የተገኙ የሚዲያ ባለሙያዎችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ስለ ጣና የሚሰራውን ትክክለኛና መሬት የነካ ሥራ በማየት ትክክለኛውን ገጽታ ለህዝብ በማስተላለፍ፣ ያለውን ብዥታ በማጥራትና እውነታውን በመግለጽ እንዲያግዟቸው ጥሪ አቅርበዋል:: ጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንደ ክፍተት ባነሷቸው አማራጮችን አቀናጅቶ ወደተግባር ያለመግባት ጉዳይ ላይ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተው ውይይቱ ተቋጭቷል፡፡


Read 22734 times