Saturday, 27 June 2020 13:27

“ሰኔ ነግ በኔ!” - (ክፍል ፪)

Written by  አዲሱ ዘገየ
Rate this item
(0 votes)

 የስደተኞች ቀን በሚከበርባት ሰኔ ወር ላይ የስደት ሕይወት እንዲያከትም የሚያደርግ የንቅናቄ ጥሪ ቢሰማም በገሃዳዊው ዓለም እውነታ ግን ለስደት የሚዳርጉ ወረራዎች፣ ጭቆናዎች፣ ኢፍትሐዊ ጫናዎች ወዘተ ሲከሰቱ ይታያል፡፡ ከነዚህ አንዱ በጣሊያን ወረራ ዘመን የሀገሪቱን ንጉሠ ነገሥት ለስደት የዳረገ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ንጉሠ ነገሥቱ ተሰደው የዓለማቀፉ ድርጅት በሚገኝበት ጄኔቭ ከተማ ለዓለም ሀገራት አቤቱታቸውን አመለከቱ፡፡--;
               
            የሰኔ እና ሰኞ መገጣጠም በአርሶ አደሩ ዘንድ ከመጥፎ ምልኪነቱ ይልቅ እንደ መልካም አጋጣሚ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ለዘር ከሚመረጡ ዕለታት መካከል አንዷ ሰኞ ናትና:: ለዘር ዝሪ ምቹ ከሆኑ የሳምንቱ ቀናቶች ሰኞ፣ ማክሰኞ እና ሐሙስ ተመራጭ ናቸው:: ዕለታትን በማወዳደር ለዝሪ እንደሚመረጡ ሁሉ የዘሪውን ማንነትና ማኅበረ-ባህላዊ ማዕረግ የሚያሳውቁ የመምረጫ መስፈርቶች አሉ፡፡ ከነዚህ አንደኛው ከቀዳሚ ወይም/እና ከመካከለኛ የባለጠግነት ደረጃ ላይ መገኘት (መናጢ ደሃ አለመሆን) ዋነኛው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ በአዎንታዊ ሥነምግባር መካን፣ ማለትም በለጋስነት፣ በአዛኝነት፣ በመጽዋችነት፣ ባስታራቂነት፣ ሸምጋይነት፣ ገላጋይነት ሚና ላይ ስኬታማ መሆን ያስመርጣል፡፡ ይህም አዝመራው እንዲያብብና እንዲያፈራ የሚያስችል ነው፡፡
ሰኔና ሰኞን ለመፈከር የሀገራችንን ዓለማቀፋዊ ግንኙነት መነሻ ማድረጉ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ በሀገሬው እምነት መሠረት ሰኞን መሆን ለአደጋ መጋለጥና አደጋውም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ሊያስከትል የሚችል የክፉ ገጠመኝ ተምሳሌት ነው፡፡ ይህም ሰኞ የሚለውን ቃል ያስገኘው “ሰኑይ” የሚለው ቃል ፍቺ ሁለት ማድረግ፤ ማጠፍ መደረብ፤ በመልክ በባህርይ መለወጥ፤ ሌላ መልክ/አካል /ባህርይ/ አመል ማውጣት /ማብቀል/መውረስ ያመለክታል፡፡
ይህን ፍቺ ይዘን ሰኔ የዘር ዝሪ ወር ናትና ሁለተኛ ገጽታዋን እንቃኝ፡፡ የምትዘራው ቅንጣት አፈር ለብሳ (ተቀብራና በስብሳ) ዳግም በትንሣኤ ታድሳ፣ የምትወጣበትን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግብዓተ መሬት የሚገልጠውን ፍቺ ዘር ዝሪ ብለናል፡፡ በጋና ክረምት፣ ልደትና ሞት፣ መጀመሪያና መጨረሻ፣ መሄድና መምጣት፣ ማግኘትና ማጣት፣ ቀንና ሌሊት፣ ወዘተ ተፈራራቂ መንታ መልኮችን እንደሚወክሉ ሁሉ ዝሪ ሞትና ትንሣኤን ወዘተ ወካይ ነው፡፡  
“አንድ ሰኔ የተከለው ካመት ዓመት አተረፈው! አንድ ሰኔ የጣለውን ሰባት ሰኔ አያነሳውም!” የሚል የአምራች ገበሬን ሙያዊ ሥነምግባር የሚያወሱ አባባሎች አሉን፡፡ ለምሳሌ ያህል በአይስላንድ ሀገር የሚገኘው ተራራ በ1775 (ሁሉም አቆጣጠሮች ዓመተ ምሕረት ናቸው) በእሳተ ገሞራ ሲፈነዳ፣ ከ9 ሺ በላይ ሰዎችን ለሕልፈት ዳርጓል፡፡ ይህም በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ጥረት ሊመለስ ያልቻለ የረሃብ አደጋ አስከትሏል፡፡ በወርኀ ሰኔ የሚከበሩ/የሚታሰቡ ዓለማቀፍ በዓላት አሉ:: የውሃ ባህርይ በሚሾምበት ወር ላይ የእሳት ባህርይ ገናን መሆን የተነሳ አደጋዎች ያጋጥማሉ:: ከዚህ ጎን ለጎን መሬትና ውሃ ተጋግዘው አደጋን ይፈጥራሉ፤ በዚህም ልዩ ልዩ መጠሪያ ያላቸው የውሃ ማጥለቅለቆች፣ ውሽንፍሮች፣ የመሬት መንሸራተቶች፣ ርዕደ መሬቶች፣ የግድብ ጥሰቶች ጥቂቶች ናቸው::
የዓለሙ ማኅበረሰብ ነባር በዓላትን ጥሎ ወይም ከነባሮቹ ጋር መሣ ለመሣ የሚያከብራቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡ ሀ. የውቅያኖስ ቀን ለ. የደን መመናመን /ምድረ በዳነትን/ ድርቅን መከላከያ ቀን ሐ. የዓለም የስደተኞች ቀን መ. የዓለም የሙዚቃ ቀን ሠ. የዓለም የሕዝብ አገልግሎት/ፐብሊክ ሰርቪስ ቀን ረ. ዓለማቀፍ የጸረ-አደንዛዥ ዕጽ እና የስቃይ ሰለባዎችን መርጃ ቀን ሰ. የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ቀን ሸ. ከእንስሳ ወደ ሰው ተላላፊ በሽታዎች ቀን የተወሰኑት ናቸው፡፡ እነዚህ በዓላት በየአህጉራቱና ሀገራቱ ልዩ ልዩ ይዘቶችና ዓላማዎች አላቸው፡፡ ወቅቶችን ተከትለው ከሚበረከቱ ገጸበረከቶች ጋር የተሳሰሩ ቢመስሉም፣ “የባህል ወረራን ለማስፋፋት የተፈጠሩ ናቸው!” የሚል ተቃውሞ ይሰማባቸዋል:: ለአብነት ያህል ከአየር ጠባያት ጋር ከሚዛመዱ በዓላት መካከል (የውሃ ባህርይ የሚሾምበት) በመሆኑ የውቅያኖስ፣ የደን ጥበቃ፣ የድርቅ መከላከል ወይም የአረንጓዴ አሻራ፣ የጸረ-ስደት፣ የስፖርት ጋዜጠኝነት ቀናት ከወቅታዊ ዐውዶች ጋር የተጣጣሙ ይመስላሉ::  
ፈጠራና ግኝቶች፡- “እሾህ በእሾህ ይነቀሳል! ካሣ በካሣ ይመለሳል!” እንዲል ከእንስሳ ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች መካከል የዕብድ ውሻ ሕመም አንዱ ነው፡፡ ለዚህ የጤና ጠንቅ ሁነኛ ማዳኛን የፈጠረው ፈረንሳዊው ሉዊስ ፓስተር ነው፡፡ ይህ ግለሰብ የተጠበበበትን የሕክምና አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በታማሚ ላይ የተገበረው በ1877 ሰኔ ላይ ነው፡፡ ኮሮና ከነዚህ ዓይነት በሽታዎች የሚመደብ መሆኑ ይታወቃል:: ለዚህ ወረርሽኝ የሚበጀው የማዳኛ ጥበብ በወርኀ ሰኔ ሊገኝ እንደሚችል ታሪክን በማስታወስ ተስፋ መሰነቅ አያዋጣም?
በ1939 በታላቋ የሶቭየት ኅብረት አዲስ የጦር መሣሪያ ተፈለሰፈ፤ ይኸውም በካላሽኒኮቭ አማካይነት ኤ.ኬ. 47 የተሰኘው የክላሽ ጠመንጃ ነው፡፡ ከሶቭየት ሳንወጣ የ26 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋዋ ወጣት መቶ አለቃ ቫለንቲና፣ ፈር ቀዳጅ የጠፈር ጉዞዋን ያደረገችው በሰኔ 1955 ነው፡፡ ከወደ ሀገረ እንግሊዝ ደግሞ በ1940 ላይ የመጀመሪያው “ማንቸስተር ስሞል ስኬል ኤክስፐርመንታል ማሽን” የተሰኘው ትእዛዛትን መዝግቦ የሚተገብር የኮምፒዩተር መሣሪያ ባገልግሎት ላይ ዋለ፡፡ ከ400 ሚሊየን በላይ ተመልካቾች ለመጀመሪያ ጊዜ በሳተላይት አማካይነት የሚሰራጭ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መመልከት የቻሉት በ1967 ሰኔ ውስጥ ነው፡፡ ከጠፈር እስከ ሰፈር ይሉሃል ይህ ነው፡፡ ዕለተ ሰኞ በሥነፍጥረታት ታሪክ ከውሃ ጫና ነጻ የወጣች ጠፈር የተፈጠረባት ዕለት ናት፡፡ በውሃ ዘመን፣ ወቅት፣ ዕለትና ሰዓት የብስ የተገኘችባትን ዕለት ሰኔና ሰኞ ብንላትስ?
ዜና ልደት ወዕረፍት፡- ከስመ-ጥር ግለሰቦች ዕለተ ልደትና ሞት ጋር በተያያዘ ሰኔ የሚከተሉትን ስትቀበልና ስትሸኝ ኖራለች:: ከነዚህ አንዱ አርጀንቲናዊው የነጻነት ታጋይ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ አንዱ ነው፡፡ ይህ ታጋይ ከሕክምና ዘርፍ የወጣ ሐኪም ነው፡፡ ነገር ግን የነጻነት ትግል ጎራን ፈጥሮ ታግሏል:: በሀገራችንም ከተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ ፈልቀው ወደ ትግል ከገቡ ሰዎች መካከል ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ አንዱ ናቸው፡፡ የሁለቱም ታጋዮች የትውልድ ዘመን 1920 ወርኀ ሰኔ ነው:: እንዲሁም በዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ካበረከቱት መካከል 14ኛው የቲቤት መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማ፣ ደቡብ ኮርያዊው የተ.መ.ድ. ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን፣ 43ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ወከር ቡሽ፣ እና ታዋቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የትውልድ ዘመናቸው 1927፣ 1936፣ 1938፣ 1974 ወርኀ ሰኔ ላይ ነው፡፡ ዕለተ ዕረፍትን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስ ላሊበላ፣ እንግሊዛዊው ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ በ1882፣ ኢትዮጵያዊው የቀለም ቀንድ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ /1936፣ ነቢዩ መሐመድ/ 624፣ የዓለም የሙዚቃ ቀን በሚከበርበት ወር ላይ በግል ሐኪሙ ስህተት ህይወቱ ያለፈው ታዋቂው የሙዚቃ ባለሙያ ማይክል ጃክሰን፣ በ2001 ወርኀ ሰኔ ላይ ዕለተ ረፍታቸው ይዘከራል፡፡
ጥቁር አንበሳ የዐርበኞች ማኅበር፡- ይህ ስመጥር ማኅበር በ1928 ሰኔ ላይ ወራሪውን የጣሊያን ጦር በነቀምት አካባቢ ድል ያደረገ ነው፡፡ ማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንቡን ያጸደቀው በዚህቺ ወር ላይ ነው፡፡ ይህ የትግል ማኅበር እንዲቋቋም ካደረጉ መስራቾች መካከል ኢትዮጵያዊው የመጀመሪያ ሐኪም/አዛዥ ወርቅነህ እሸቴ ከሕክምና ዘርፍ ወደ ነጻ አውጭዎች የትግል ጎራ በመሰለፍ ማኅበሩን በመሪነት አገልግሏል፡፡
1965 ወርኀ ሰኔ ላይ በሕክምናው ዘርፍ አንድ ርምጃ ሀገራችን መራመዷን የሚያሳይ የርዳታ ስምምነት በስዊድንና ኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ተከናውኗል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ስሙ መስፍነ ሐረር፣ ባሁኑ ስሙ የጥቁር አንበሳ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ የቀ.ኃ.ሥ. የሕክምና ትምህርት ማዕከልን ለማቋቋም የስዊድን መንግሥት 5.4 ሚልየን ብር ብድር ለመስጠት የተስማማበት ነው፡፡ ከዚሁ ስምምነት ሳንወጣ የወባ በሽታን ለማጥፋት የሚረዳ ስምምነት፣ በኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት መካከል የተፈረመው በ1963 ሰኔ ላይ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመትና ወር በኢትዮጵያ የታላቋ ብሪታኒያ አምባሳደር አለን ካምቤል የተመራ ልዑክ፣ ከእንግሊዝ ሕዝብና መንግሥት የተበረከተውን ለምግብ ዋስትና የሚያግዝ 2.4 ሚልየን ብር በርዳታ ለመስጠት የስምምነት ፊርማውን አኖረ:: ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ የዓለም አቀፉ የልማት ድርጅት፣ ለሀገራችን የግብርና ልማት የሚውል 21 ሚልየን ዶላር ብድር ያጸደቀበት ጊዜ ነው፡፡ ወርኀ ሰኔ ላይ ከነጻነት በኋላ የቤተ ሳይዳ ሆስፒታል በአዲስ መልክ አገልግሎቱን የጀመረበት ጊዜ ነው፤ ዘመኑም 1938 ነበር፡፡ ይህ ሆስፒታል የካቲት 12 ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ሲቋቋም የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ባመራር አባልነት ካገለገሉ መካከል ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ አንዱ ናቸው፡፡
የባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ላይ ሰኔ 16 ቀን የስደት ሕይወት እንደተጀመረ አውስቻለሁ:: ነገር ግን ዕለቲቱ ስደት የተጀመረባት ሳትሆን ስደተኞቹ የሕፃኑን ነፍስ ለማትረፍ ይረዳ ዘንድ የተቀሰቀሱባት ዕለት ናት፡፡ የስደተኞች ቀን በሚከበርባት ሰኔ ወር ላይ የስደት ሕይወት እንዲያከትም የሚያደርግ የንቅናቄ ጥሪ ቢሰማም በገሃዳዊው ዓለም እውነታ ግን ለስደት የሚዳርጉ ወረራዎች፣ ጭቆናዎች፣ ኢፍትሐዊ ጫናዎች ወዘተ ሲከሰቱ ይታያል:: ከነዚህ አንዱ በጣሊያን ወረራ ዘመን የሀገሪቱን ንጉሠ ነገሥት ለስደት የዳረገ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ንጉሠ ነገሥቱ ተሰደው የዓለማቀፉ ድርጅት በሚገኝበት ጄኔቭ ከተማ ለዓለም ሀገራት አቤቱታቸውን አመለከቱ፡፡ ወደ እንግሊዟ ለንደን ተሻግረውም ጊዜያዊ ተገን አበጁ፤ በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሽርክናን ፈጠሩ፡፡ በመጨረሻም እሾህን በሾህ ለመንቀስ ይረዳ ዘንድ የእንግሊዝ ጦር ንጉሠ ነገሥቱን አጅቦ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ከዚያ የሰማነውን ሁሉ አደረገ፡፡ ሰኔና ኅዳር የቅዱስ ሚካኤል ታቦት የሚከበርባቸው ዕለታት አሏቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በጣሊያን ወረራ ወቅት ግን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የየካ ሚካኤል ደብር የቆመለትን መንፈሳዊ ተግባር እንዳይወጣ ግብሩን የማስታጎል ተጽዕኖ ደርሶበታል፤ ዘመኑ 1929 ነበር፡፡
ክረምትን በሰኔ በኩል ለመቀበል ከሚደረጉ ሽር ጉዶች አንዱ ጸሐይን መጋረድ፣ ለዛውም ከጸሐይ ተለቅታ/ተበድራ በሚኖራት የብርሃን መጠን የምትታወቅ ጨረቃ መድመቅ አንዱ ነው፡፡ ይህም እያደገ ሲመጣ ከጸሐይ እኩል የሚያበሩ አካላትን (ማለትም ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ተቋማት፣ ሀገር፣ አህጉር ወዘተ) በማጨለምና ብርሃናቸውን በመንሳት የማስታጎል እኩይ ድርጊት ገላጭ ነው፡፡
ወርኀ ሰኔ ከሀገራችን ሥነመንግሥታዊ ታሪክ ጋር የተገናኙ አጋጣሚዎችን አስተናግዳለች:: በዚህ የመጀመሪያ የሚባለው በ1965 የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደራሴዎች ምርጫ እስከ ሰኔ 30 ቀን መካሄዱ አንዱ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ ለሽግግር መንግሥት ምስረታ የተመረጠችው ከሃያ ዓመታት በኋላ ነበር:: በዚህም ከ20 ፓርቲዎች በተወከሉ ልዑካን አማካይነት ሀገረ ኤርትራ ለሻዕቢያ መራሹ የትግል መደብ ተላልፋ እንድትሰጥ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በሰኔ 24ቱ ጉባዔ ላይ ዩኒቨርስቲያቸውን (አ.አ.ዩ) ወክለው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ሰኔ 24 ቀን በ1983 አዲሱ መንግሥት ሕዝባዊ ምርጫ አድርጎ አሸናፊነቱን ያወጀባት ወር ስትሆን፣ ለሻዕቢያ መንግሥት ኤርትራን ያስረከበው ቡድን ሁለቱን እትማማች ሕዝብ ወደ ጦርነት ለማስገባት ስምንት ዓመት ብቻ ነበር የፈጀበት፡፡ ጦርነቱ ተቀጣጥሎ ከሁለቱም ወገኖች በርካቶች ካለቁ በኋላ ደግሞ ገዥው መንግሥት ዳግም በ1992 ጦርነቱን ለማቆም የተስማማበትና “ቀኝ ኋላ ዙር!” ያወጀባት ወር ናት፡፡ ወርኀ ሰኔ የጦር መሣሪያዎች ከወዲያ ወዲህ ፍሬያቸውን የሚያሳዩባት ለመሆኗ ከሩቅ እማኝ ሳንጠራ 1997ን 2010ን እና 2011ን ማውሳት ይበቃል፡፡
ሰኔ 1878ን ይዘን ፈረንሳይ በ110ኛው የነፃነት በዓል ላይ ለአሜሪካ ያበረከተችውን ስጦታ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ስጦታው የነጻነት ሐውልት ነው፡፡ ተምሳሌትነቱም ዓለማቀፋዊ ይዘት ያለው ነጻነትን ቢወክልም፣ በውስጠ ታዋቂነት በፈረንሳይና አሜሪካ መካከል ያለን የወንድማማች/እትማማችነት መንፈስና በሀገራቱ መካከል ያለ የወል አስተሳሰብ የሚያመለክት ነው፤ በዚህም ሀገራቱ ነጻነትን በጋራ መሻታቸውን የሚገልጹበት ነው፡፡ አሁን ግን ያ ተምሳሌትነቷ ጠፍቶ የስደተኞች/የግዞተኞች እናት ተደርጋ ሐውልቷ ትቆጠራለች:: በርካታ የአፍሪቃ ሀገራት ከቅኝ ገዥዎች ነጻ የወጡባት ወር ሰኔ ናት፡፡ በዚህቺ ወር ከ14 ያላነሱ ሀገራት ቅኝ ገዥዎቻቸውን አሰናብተዋል:: በተለይም የምስራቃዊ አፍሪቃ ሀገራት በርካታ ናቸው:: እኒህ ሀገራት ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጣሊያን፣ ከቤልጅየም ነጻ የወጡ ሲሆን፣ በ1955 ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት በተነሳ ጫና ቀ.ኃ.ሥ. ከፖርቱጋል ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ፡፡
በ1937 ሰኔ ወር ላይ በሀገረ አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ በተካሄደ የተ.መ.ድ ምስረታ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ብላታ ኤፍሬም ተወልደመድኅን ተሳትፈዋል:: ከሰኔ 6-16 ቀናት በተደረገው 2ኛው የነፃ አፍሪቃ ሀገራት ያዲስ አበባ ጉባኤ ላይ ከ250 በላይ ልዑካኖች ተገኝተዋል:: በዚህም የጥቁሮች ነጻነት፣ ፖለቲካዊ አመለካከት፣ የጸረ-ቅኝ ግዛት ዐውድ፣ እኩልነት ወዘተ የመወያያ ርዕሶች ሆነዋል:: ነገር ግን በቃል እንጂ በተግባር ያልወረደው የይስሙላ ሕገ መንግሥት በአሜሪካ ሲተገበር ቆይቶ፣ በ1956 ሰኔ ላይ ሶስት ጥቁር የሰብዓዊ መብት ታጋዮች በነጭ የዘር ቀለም የበላይነት አራማጆች በፊላደልፊያ ሚሲሲፒ ታንቀው ተገደሉ። ከሶስት ዓመት በኋላ ግን ታሪክን የቀየረ የሚመስል ሀሳብ ተሰነዘረ፤ ይኸውም በወርኀ ሰኔ ላይ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ ሊንደን ቢ. ጆንሰን ለሀገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣንነት የመጀመሪያውን ጥቁር አሜሪካዊ በዕጩነት ማቅረቡ ነው፡፡
በዚህ ዘመን በደቡብ አፍሪቃም ተመሳሳይ የዘር መድልዎ እየተፈጸመ ነበር:: የደቡብ አፍሪቃው የጸረ-አፓርታይድ ትግል መሪ ማንዴላ “ዕድሜ ይፍታህ!” ተፈርዶበት ወኅኒ የተጋዘበት ዓመትና ወር ስትሆን፣ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ሸንጎ (ኤ.ኤን.ሲ.) በወኅኒ ላይ በነበረው ኔልሰን ማንዴላ የቀረበለትን የትጥቅ ትግል ጥሪ የተቀበለው ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ “እምብዛም ሳይዘገይ” በ1972 ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚደገመው ይህ ዐውዳዊ ክስተት ነው:: በተለይ ደግሞ ያደጉ በሚባሉ ሀገራት ብሶ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ያህል የጥቁር አፍሪካውያን ቀን ሲከበር ጥቁርን መግደል የሠለጠነው ዓለም መገለጫ ሆኗል፡፡ በዚህ ጊዜም የየሀገራቱ የሥነመንግሥት መሪ ቃል መሣሪያ እንጂ ቃል እንዳያሸንፍ፣ ጉልበት እንጂ ዕውቀት እንዳይፈለግ፣ የተግባርና ቃል እየቅልነት የሚያሳይ ሆኗል፡፡

Read 1906 times