Print this page
Saturday, 27 June 2020 12:18

ከአለማችን የኮሮና ተጠቂዎች ከግማሽ በላይ ያህሉ አገግመዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  *በመላው ዓለም በአንድ ቀን 183 ሺ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተመዝግበዋል

             ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለወራት ነጋ ጠባ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ዜናዎችን ስትሰማ የዘለቀችው አለማችን፣ አልፎ አልፎም ቢሆን እንደ ትናንት በስቲያው ያለ ተስፋ ሰጪ ወይም በጎ ነገር አድምጣ ለጊዜውም ቢሆን መጽናናቷ አልቀረም፡፡
ዎርልዶሜትር ድረገጽ ያወጣውን መረጃ ጠቅሰው አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከትናንት በስቲያ ባወጡት መረጃ፣ በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ከበሽታው ማገገማቸውን አስነብበዋል፤ እስከ ሃሙስ በመላው አለም በኮሮና ከተጠቁት ከ9.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል፣ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከቫይረሱ ማገገማቸውን በመግለጽ።
እንዲህ ያለው ተስፋ ሰጪ ነገር በየመሃሉ ብልጭ ቢልም፣ ቫይረሱ ግን መላውን አለም በጭንቅ ውስጥ እንደከተተ ነጋ ጠባ በፍጥነት መስፋፋቱን፣ ብዙዎችን ማጥቃቱንና መግደሉን እንዲሁም በአገራት ላይ ሁለንተናዊ ቀውስ መፍጠሩን ገፍቶበታል፡፡
በየዕለቱ የሚመዘገቡ የተጠቂዎች ቁጥሮችም አስደንጋጭ እየሆኑ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት፣ በአለማችን ባለፈው እሁድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ የማይታወቅ፣ ከፍተኛው የ183 ሺህ ዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መመዝገቡን ባስታወቀበት አስደንጋጭ መረጃ ነበር ሳምንቱ የጀመረው፡፡
በዕለቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ 54 ሺህ 771 የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙባት ብራዚል፤ ከፍተኛ ብዛት ያላቸው ተጠቂዎች የተመዘገቡባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ስትሆን፣ በአሜሪካ 36 ሺህ 617፣ በህንድ 15 ሺህ 400 የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል፡፡
በሳምንቱ ቀናት ተባብሶ የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ9.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ487 ሺህ በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ዎርልዶሜትር ድረገጽ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ ከ2.47 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተጠቁባትና 125 ሺህ ያህል ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፣ በቫይረሱ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር አሁንም ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት የተቀመጠች ሲሆን፣ ብራዚል ከ1.193 ሚሊዮን በላይ፣ ሩስያ 614 ሺህ ያህል፣ ህንድ ከ481 ሺህ በላይ፣ እንግሊዝ 308 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተውባቸዋል:: ከአሜሪካ በመቀጠል ብራዚል ከ54 ሺህ በላይ፣ እንግሊዝ ከ43 ሺህ በላይ፣ ጣሊያን 35 ሺህ ያህል፣ ስፔን ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ሳቢያ ለሞት የተዳረጉባቸው አራት የአለማችን አገራት ናቸው፡፡
 
የአለም ኢኮኖሚ ቀውስ ተባብሶ ይቀጥላል
በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ቀውስ ውስጥ የወደቀው የአለማችን ኢኮኖሚ ቀውሱ አሁን ካለበት ደረጃ ተባብሶ እንደሚቀጥል አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ትንበያ አመልክቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለማችንን ታይቶ በማይታወቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደዘፈቃት የጠቆመው ተቋሙ፣ አለማቀፉ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በ2020 የፈረንጆች አመት በ4 ነጥብ 9 በመቶ መቀነሱንና ቀውሱ በሁለት አመታት ውስጥ የ12 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ያስከትላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡
በአመቱ እንግሊዝ የ10.2 በመቶ፣ አሜሪካ የ8 በመቶ፣ ጣሊያንና ስፔን የ12.8 በመቶ፣ ሩሲያ የ6.6 በመቶ፣ ህንድ የ4.5 በመቶ፣ ብራዚል የ9.1 በመቶ የኢኮኖሚ ቅናሽ ያጋጥማቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

በአሜሪካ ኮሮና ዳግም እያንሰራራ ነው
በአሜሪካ የኮሮና ቫይረስን ጉዳይ በበላይነት በመምራት ላይ የሚገኙት እውቁ የህክምና ሊቅ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ ኮሮና ከዚህ በፊት ከታየው በባሰ አስደንጋጭ ሁኔታ ዳግም ሊያንሰራራና የባሰ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ከሰሞኑ አስጠንቅቀዋል፡፡
በአብዛኞቹ ግዛቶቿ የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣባት አሜሪካ፣ በድጋሚ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በወረርሽኙ ሊያዝባት ይችላል ያሉት ዶክተር ፋውቺ፤ ወረርሽኙ በአዲስ መልክ ሊያንሰራራ እንደሚችል የሚጠቁሙ አስፈሪ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ መግለጻቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ በቀጣይ ቀናት ወረርሽኙ በአደገኛ ሁኔታ ሊያንሰራራባቸው ይችላል ብለው ዶክተር ፋውቺ ከጠቀሷቸው አካባቢዎች መካከል ደቡባዊና ምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙበት ሲሆን አሪዞና፣ ናቫዳ፣ ቴክሳስ በየዕለቱ የሚመዘገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከሚገኝባቸው ግዛቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ተነግሯል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን በበኩሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ በአሜሪካ ቫይረሱ ዳግም ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ እስከ መጪው ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ በአገሪቱ ተጨማሪ 180 ሺህ ያህል ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ተንብዩዋል፡፡

አፍሪካና እያሻቀበ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ
ደ. አፍሪካ ባለፉት 90 ዓመታት ታሪኳ የከፋውን የኢኮኖሚ ውድቀት ታስተናግዳለች
እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ከ336 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባትና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ8 ሺህ 900 በላይ በደረሰባት አፍሪካ፣ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 161 ሺህ ያህል መድረሱን ዎርልዶሜትር ድረገጽ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ የከፋ ጥፋት እንደሚያስከትልባት በሚነገርላት አህጉረ አፍሪካ የሚገኙ ሁሉም አገራት በአሁኑ ወቅት ኮሮና ቫይረስን መመርመር የሚያስችላቸውን ቤተሙከራ ማደራጀታቸውንና የምርመራ አቅም መፍጠራቸውን የአለም የጤና ድርጅት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከአህጉሩ ቀዳሚነቱን በያዘችውና በወረርሽኙ ሳቢያ ባለፉት 90 አመታት ታሪኳ የከፋውን የኢኮኖሚ ውድቀት ታስተናግዳለች ተብላ በምትጠበቀው ደቡብ አፍሪካ፣ ምስራቃዊ ኬፕታውን ግዛት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ 196 ትምህርት ቤቶች ዳግም አገልግሎታቸውን አቋርጠው እንዲዘጉ መደረጉን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ከሰሞኑ ኮሮና ቫይረስ ከተገኘበት ግለሰብ ጋር ንክኪ ስላላቸው ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ ቢሆኑም፣ ለሁለት ሳምንታት ያህል፣ ራሳቸውን ከሌሎች አግልለው እንደሚቆዩ ለህዝባቸው በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በኮሮና ስጋት ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶችን በቀጣዩ ሳምንት ዳግም ለመክፈት በዝግጅት ላይ የነበሩት የላይቤሪያ ትምህርት ሚኒስትር አንሱ ሶኒ እና ምክትላቸው ላቲም ዳቶንግ፣ ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ሆስፒታል መግባታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
 
የክትባቱ ነገር…
በመላው አለም ከ120 በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒት ምርምሮች በመደረግ ላይ እንዳሉ ከተዘገበና የአለም ህዝቦችም አንዳች የምስራች ለመስማት ጆሯቸውን ቀስረው በተስፋ መጠበቅ ከጀመሩ ብዙ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን ተስፋ ሰጪ እንጂ ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ የተዘገበ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ የክትባት ሙከራ የተመረጠችው በዘርፉ ባሏት ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ቀዳሚዋ አፍሪካዊት አገርና ወረርሽኙም በፍጥነት እየተስፋፋባት በመሆኑ ጭምር ነው መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኦኤክስ1ኮቪድ-19 ተብሎ የሚጠራውና ዊትስ ዩኒቨርስቲ፣ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲና ኦክስፎርድ ጀነር ኢንስቲቲዩት፣ በጋራ የሚያካሂዱት ይሄ የክትባት ሙከራ ከሰሞኑ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በእንግሊዝ የኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ተመራማሪዎች የተፈጠረውና ከዚህ በፊት በእንስሳት ላይ ተሞክሮ አበረታች ውጤት በማሳየቱ ተስፋ የተጣለበት የኮሮና ቫይረስ ክትባት፣ ከሰሞኑ ደግሞ በአገሪቱ በጎ ፈቃደኞች ላይ መሞከር መጀመሩንና ስኬታማ ከሆነ እስከሚቀጥለው የፈረንጆች አመት አጋማሽ ድረስ በመላው አለም ይሰራጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
ብራዚል በበኩሏ፤ ChAdOx1 nCoV-19 የተሰኘ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን የበለጠ ተጋላጭ በሆኑት የጤና ባለሙያዎች ላይ መሞከር መጀመሯን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በመላው አለም በምርምር ላይ ከሚገኙ 120 ያህል የኮሮና ክትባቶች መካከል አብዛኛዎቹ ከቤተ ሙከራ አለመውጣታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በክሊኒካል ሙከራ ደረጃ የሚገኙትም 13 ያህሉ ብቻ መሆናቸውንና 5ቱ በቻይና፣ 3ቱ በአሜሪካ፣ 2ቱ በእንግሊዝ፣ እንዲሁም በጀርመን፣ በአውስትራሊያና በሩሲያ አንድ አንድ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 28019 times
Administrator

Latest from Administrator