Print this page
Sunday, 28 June 2020 00:00

በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

 በአንቲ ቦዲ ምርመራው ከ20-30 ሺ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዷልየሰዎች
                          
          በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስርጭት መጠን ለማወቅና ምላሽ ለመስጠት ያስችላል የተባለ የአንቲ ቦዲ ምርመራ ማድረግ ተጀመረ። ምርመራው ከሰኔ 15 አንስቶ የተጀመረ ሲሆን ሐምሌ 7ቀን2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ምርመራ መካሄድ ከተጀመረበት ከጥር 29ቀን2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ባጠቃላይ ለ237ሺ464 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን እስካሁን 5425 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። 89 ሰዎች ደግሞ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። በአገራችን ሲካሄድ የቆየው የምርመራ ዓይነት የኮቪድ 19 በሽታ ያለበት ሰው ላይ ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚረዳ የሞሎኪዩላር ምርመራ ሲሆን አሁን የተጀመረው ምርመራ ግን ሰዎች ቀደም ሲል በበሽታው ተይዘው መዳናቸውን ለማወቅ የሚያስችልና ሰውነታችን ለበሽታው ከተጋለጠ ከአንድ እስከ ሶስት ሳምንት ድረስ በሽታውን ለመከላከል ሰውነታችን የሚያመርተውን የበሽታ ተከላካዮች ለማወቅ የሚያስችል ነው።
ምርመራው ከሰውነታችን በሚወሰዱ ከ3-5 ሚሊ ሊትር የደም ናሙና የሚደረግ ሲሆን የምርመራው ውጤት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የበሽታ ስርጭት (Survellance) ለማወቅና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ተብሏል።
የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያውና በኮቪድ 19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ እንደሚናገሩት፤ ይህ የአንቲ ቦዲ ምርመራ በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ መኖሩንና ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መዳናቸውን ለማወቅ የሚያስችልና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል። በዚህ ምርመራ የሚገኘው ውጤት ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን ብለዋል ብዙ ውጤት ተገኘ ማለት ብዙ ሰዎች ቀደም ሲል በበሽታው ተይዘው መዳናቸውን የሚያመላክት፣ በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ መሰራጨቱን፣ በበሽታው የሚከሰተው የሞትና የፅኑ ህሙማን መጠን ከፍተኛ እንደማይሆንና ከቫይረሱ ጋር አብረን ለመኖር እንደምንችል የሚያመለክት ነው። ይህ ማለት ደግሞ እጅግ በጣም ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ጉዳይ ነው ብለዋል - ባለሙያው።
ምርመራው ይበልጥ ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን የበሽታውን ስርጭት በማወቅ ለሚደረገው ቅድመ መከላከልና ህክምናም ትልቅ ፋይዳ አለው ተብሏል።

Read 25189 times