Saturday, 27 June 2020 12:11

የክልልነት ጥያቄዎች ላይ ውሣኔ እንዳይሰጥ ኢዜማ ጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  - ጥያቄዎቹ የህዝብ ፍላጐት ያንፀባርቃሉ የሚል እምነት የለኝም ብሏል
             - በአዲስ አበባ ከመሬት ወረራ እና ኮንደሚኒየም ቤት ማስተላለፍን እመረምራለሁ ብሏል

            በደቡብ ክልል የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች በህዝብ የተመረጠ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ምንም አይነት ውሣኔ እንዳይሰጥባቸው ኢዜማ የጠየቀ ሲሆን በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከመሬት ወረራ እና የኮንዶሚኒየም ቤት እደላ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡
በአሁን ወቅት በክልሉ እየቀረቡ ያሉ የክልል እንሁን ጥያቄዎች፤ በዋናነት የራሱ የመንግሥት ካድሬዎች የሚያነሱትና ለተፈፃሚነቱ እየገፉበት ያለ ጉዳይ እንጂ በትክክል የህዝብ ፍላጐት የተንፀባረቀበት ነው የሚል እምነት እንደሌለው ፓርቲው ገልጿል፡፡
ራስን በራስ ለማስተዳደር መብት እውን መሆን እንደሚታገል የገለፀው ኢዜማ፤ ይህ መብት የሚረጋገጠውም በካድሬዎች ፍላጐት ሳይሆን በህዝብ ፍላጐት ነው ብሏል፡፡ በዚህ መሠረትም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካላት እየቀረቡ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎች የህዝቡ ፍላጐት መሆናቸው መጣራት እንዳለበት፤ ይህን ለማድረግም አሁን ጊዜው ስለማይፈቅድ በይደር እንዲቆይ ኢዜማ ጠይቋል፡፡
በሁለት ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት የክልልነት ጥያቄን ማስተናገድ አይቻልም የሚለው ፓርቲው፤ አንደኛ አሁን ሀገሪቷ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ ወድቃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ጊዜ በመሆኑ የህዝብን ፍላጐት ለማወቅ የሚያስችለውን ህዝብ ውሣኔ ለማደራጀት የማያመች ነው ብሏል፡፡
“እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚገባቸው በህዝብ ፍላጐት ላይ በተመሠረቱ ውሣኔዎች ሊሆን ይገባል” የሚል ጽኑ አቋም እንዳለው ኢዜማ አስታውቋል፡፡
ኢዜማ ያቀረበው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አሁን ያለው መንግስት ስልጣኑ በህግ የተራዘመለት እንደመሆኑ ዘላቂና የሀገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ውሣኔ ማሳለፍ አይገባውም ብሏል፡፡ ስልጣኑ የተራዘመለት መንግስት፣ የውሣኔ ሰጪነት ሚናው መገደብ እንዲሁም የስልጣን ጊዜው መወሰን እንደሚኖርበት አስታውቋል - ኢዜማ፡፡
በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ የህዝብ መብት ሰጪና ነሺ ሆኖ የቀረበበት መንገድም ከለውጡ መንፈስና አካሄድ ጋር የሚቃረን በመሆኑ እንዲህ ያለው አካሄድ በአስቸኳይ እንዲቆምም ኢዜማ አበክሮ ጠይቋል፡፡  
ይህ በእንዲህ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ቅርምት እና ከኮንዶሚኒየም ቤት እደላዎች ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች ከወዲሁ ሊታረሙ እንደሚገባ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት ወረራዎች፣ ህገወጥ የኮንዶሚኒየም ቤት እደላዎች እና ከተማዋን በግለሰቦች በጐ ፍቃድ የምትንቀሳቀስ የማስመሰል አካሄድ መኖሩን ከከተማው ነዋሪዎች በሚደርሱት ጥቆማዎች እና በራሱ መዋቅር በኩል መረጃዎች ማግኘቱን የገለፀው፤ ኢዜማ እንዲህ ያለው ህገወጥ አካሄድ በጊዜ ካልታረመ የከተማዋን ችግሮች በማባባስና በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የሚፈጥረው ቅራኔ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም ብሏል፡፡
የሚደርሱትን ቅሬታዎች አቤቱታዎች መነሻ በማድረግም ኢዜማ ከመሬት ወረራ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለነዋሪዎች ከማስተላለፍ ጋር እና ማንኛውንም የመንግስት አድሎ አሠራሮችን መረጃ የሚያሰባስብ እና የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ከሰሞኑ “በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው የሚለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው ብሏል፡፡
እያካሄደ ያለውም በ13ኛው ዙር እጣ የወጣላቸውና የወሰን ችግር የሌለባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች የማስተላለፍ ተግባር ነው ይህም በሁለት ሣምንት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል ብሏል፡፡

Read 24430 times