Saturday, 27 June 2020 12:09

የፀጥታው ም/ቤት ሰኞ የግብጽና ሱዳንን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ያሳልፋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   ግብጽና ሱዳን የህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ከስምምነታችን ውጪ እንዳይጀመር በሚል ለተመድ የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ አሜሪካ ከነገ በስቲያ ም/ቤቱ ተሰብስቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርታለች።
ሰኞ የሚካሄደውና ዋነኛ ትኩረቱ የህዳሴው ግድብና የሶስቱ አገራት በድርድር ያለመስማማት ጉዳይ የሆነው ስብሰባ የሚካሄደው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መሆኑም ታውቋል።
ስብሰባው በዋናነትም ግብፅና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ የውሃ አሞላል አስመልክቶ ያቀረቡትን አቤቱታ እንደሚመረምር ተነግሯል።
ግብፅ ያለ ስምምነት የግድቡ ውሃ ሙሌት ከተጀመረ የውሃ ድርሻዬ ይቀንስብኛል የሚል አቤቱታ ስታቀርብ፣ ሱዳንም በበኩሏ፤ ከህዳሴ ግድብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ግድብ ለውሃ እጥረት ሊዳረግብኝ ይችላል በሚል አቤቱታዋን አቅርባለች።
ቀደም ሲል አቤቱታው የቀረበለት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ም/ቤት ሶስቱ አገራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ጉዳዩን በውይይትና ድርድር እንዲቋጩት ማሳሰቡን የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴቪን ዲጃሪክ አስታውቀዋል።
የፀጥታው ም/ቤት ሰኞ በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። 

Read 5653 times