Saturday, 27 June 2020 12:04

የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገዶች ዝርዝር ይፋ ተደረጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 - የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንደኝነት ይመራል
         - የግብፅና ሞሮኮ አየር መንገዶች ይከተላሉ
 
           በየአመቱ ስኬታማ የአየር ትራንስፖርት ዘርፎችን እየመዘነ ደረጃ የሚሰጠው “አፍሪካን ሎጅስቲክስ”  የቢዝነስ መጽሄት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2019 የአፍሪካ ቀዳሚው ስኬታማ አየር መንገድ መሆኑን ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል።
በ2019 በሰዎች ትራንስፖርት፣ በመዳረሻዎች ብዛት፣ በበረራ አቅምና የአውሮፕላኖች ብዛት እንዲሁም በሚያስገኘው አህጉራዊ ገቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ሁሉ የላቀ ነው ብሏል መጽሔቱ።
አየር መንገዱ ባለፈው የፈረንጆች አመት በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 13.3 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ወደተለያዩ የዓለም አገራት ማጓጓዙን የጠቀሰው መጽሔቱ፤ ይህም ከቀደመው አመት በ11.6 በመቶ እድገት ማሳየቱን ይገልፃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የአለም አገራትን በማገልገል በኩልም ከአለም በ4ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በመቀጠል የሁለተኛነት ደረጃ የተሰጠው የግብጽ አየር መንገድ በበኩሉ፤ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 8.9 ሚሊዮን ሰዎችን ከ70 በላይ የአለም መዳረሻዎች ማጓጓዙን “አፍሪካን ሎጀስቲክስ” ይገልፃል።
በሶስተኛነት የተቀመጠው የሞሮኮ ብሔራዊ አየር መንገድ ሲሆን አየር መንገዱን በዚህ ደረጃ ያበቃው በአለም ላይ ያሉት የመደረሻዎች ብዛት ከሌሎች የላቀ መሆኑ ነው። 94 መዳረሻዎች አሉት ብሏል - መጽሔቱ።
መጽሔቱ ባወጣው መረጃ መሰረት፤ የአልጄሪያ አየር መንገድ፣ የደቡብ አፍሪካው ኮማዬር አየር መንገድ፣ የኬንያ አየር መንገድ፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ፣ የቱኒዚያ አየር መንገድ፣ የደቡብ አፍሪካው ማንጎ አየር መንገድ እንዲሁም ሌላኛው የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ፍላይ ሳፋዬር ከ4ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

Read 1899 times Last modified on Saturday, 27 June 2020 12:44