Thursday, 25 June 2020 20:24

የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትህወሓትን ከጥምረቱ አባልነት ሰረዘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት፣ ህወሓትና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረትን (ኢዴሕ) ከጥምረቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሆነው ተገኝተዋል በሚል ከአባልነት መሰረዙን አስታወቀ። ጥምረቱ ይህን ያስታወቀው አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ካካሄደ በኋላ በሰጠው መግለጫ ነው፡፡
 ጥምረቱ በአደረጃጀቱ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጉን የጠቆመ  ሲሆን የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና የጥምረቱ ቀጣይ አቅጣጫ ላይ መወያየቱንም አስታውቋል፡፡ በዚህም ውይይት ላይ ጥምረቱ.፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥምረቱ ውስጥ ወዥንብር እየፈጠረ ነው ሲል ወቅሷል፡፡
የጥምረቱ የአደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ “ፓርቲው የጥምረቱ አባላትን ለመከፋፈል የተለያዩ ጫናዎች እየፈጠረ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ህወሓት ከዚህም ባሻገር፣ ጥምረቱን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ፣ አገርን ለማወክ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፤ሰብሳቢው በመግለጫቸው፡፡ በተጨማሪም ፓርቲው በጥምረቱ ስብሰባ ላይ እንደማይገኝና የጥምረቱ ስብሰባም መቀሌ ካልተካሄደ ተቀባይነት እንደሌለው እየገለጸ ነው ሲሉ ከስሰዋል።
 “ህወሓት እኔ ያልኩት ካልሆነና እኛ ካልመራን ትክክል አይደለም; የሚል ግትር አቋም ያራምዳል ሲሉም ነቅፈዋል፡፡  
የጥምረቱ ሊቀ መንበር አቶ ደረጄ በቀለ እንደሚሉት፤ ህወሓትና ኢዴሕ፣ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ታግደዋል፤ ይህንንም ሁሉም የጥምረቱ አባላት የተስማሙበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
 “በተለይ ህወሓት 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ተራዝሞ ሳለ ለጥምረቱ ሳያሳውቅ ምርጫ አካሂዳለሁ; ማለቱ የህገ ወጥነቱ ማሳያ ነው ብለዋል፤ሊቀ መንበሩ፡፡
ጥምረቱ 24 ፓርቲዎችን ያቀፈ ሲሆን በትናንቱ ጉባኤው 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፤ ሌሎች አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጥምረቱን መቀላቀላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 4120 times