Wednesday, 24 June 2020 20:22

ቦርዱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ ወድቅ አደረገ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበል ማስታወቁን ፋና ብሮድካስቲንግ የቦርዱን መግለጫ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ቦርድ ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ክልል ምክር ቤት ኮቪድ 19ን እየተከላከለ፣ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት፣ ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሷል፡፡
6ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሂድም ብሏል፤ ቦርዱ፡፡ በተጨማሪም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ፣ መቆጣጠርና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣
ምርጫውን ከተጽእኖ ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም መሆኑንም አውስቷል፡፡  
በኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ
እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውምም ብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፣ ምርጫውን፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ፣
የፌደራልና ክልል ምክርቤቶች የስልጣን ዘመን እንዲቀጥል እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ስልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጊዜ ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ
አንድ አመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

Read 5327 times