Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 00:00

ለንደን ትጣራለች!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንግሊዛውያንም የኢትዮጵያን ኦሎምፒያኖች ይጠባበቃሉ

30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ ሊጀመር አንድ ሰሞን ሲቀረው የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በመላው ዓለም ትኩረት እያገኙ ናቸው፡፡ በተለያዩ ጥናታዊ ስሌቶች የተሰሩ የኦሎምፒክ ሜዳልያ ስኬት ትንበያዎች ኢትዮጵያ በለንደን አሎምፒክ ከቤጂንግ የተሻለ ስኬት በአጠቃላይ የሜዳልያ ስብስቧ እንደሚኖራት ገምተዋል፡፡ በሌላ በኩል በእንግሊዝ በርሚንግሃም የሚገኘው  የፔሪፊልድስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ሲታወቅ ከትናንት በስቲያ ደግሞ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ በለንደን አሎምፒክ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ባሰናዳው የሽኝት ግብዣ ለውጤታማነቱ መልካም እድል ተመኝቷል፡፡

ኦሎምፒያኖቹ እነማን ናቸው፤ ከምርጫው በኋላስ?

ለንደን በምታስተናግደው 30ኛው አሎምፒያድ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ 34 ኦሎምፒያኖች ስም ዝርዝር ይፋ የሆነው ከሳምንት በፊት ነው፡፡ በዚሁ የኦሎምፒያኖች ስብስብ  በታሪክ ለ3ኛ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ የሚካፈሉ፤ በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፉ ወጣትና አዳዲስ አትሌቶች፤ ባልና ሚስቶች፤ እህትማማቾች፤ ወንድማማቾች እንዲሁም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በውሃ ዋና ኢትዮጵያን ወክላ የምትሳተፍ ዋናተኛ ይገኛሉ፡፡ የኦሎምፒክ ቡድኑ ከታወቀ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ዶር ይልማ በርታ ለአሶሴየትድ ፕሬስ እንደሰጡት አስተያየት ከሆነ የዘንድሮው ኦሎምፒክ ቡድን በርካታ አዳዲስ አትሌቶችን በማካተት ልዩ ሆኗል፡፡ ለወጣት ኦሎምፒያኖች መብዛት መገለጫ የሆነው ደግሞ የማራቶን ቡድኑ ሲሆን የወንዶቹ አማካይ እድሜ 25 የሴቶቹ ደግሞ 24 መሆኑ ታውቋል፡፡ ከማራቶን ኦሎምፒያኖች አንዷ የሆነችው አሰለፈች መርጊያ ለኤፒ በሰጠችው አስተያየት በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ቢያንስ 3 የወርቅ ሜዳልያ እንደሚኖራት ስትገምት ሌላው ማራቶኒስት ዲኖ ሰፈር በበኩሉ እስከ 6 ወርቅ ቢገኝስ ማን ያውቃል ብሏል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በ800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች በነፍሰወከፍ አንድ አትሌት ማሳተፏም ሌላው ልዩ ገፅታ ነው፡፡ የ20 ዓመት ወጣቶቹ መሃመድ አማንና ፋንቱ ሚጌሶ ለኢትዮጵያ የሜዳልያ ድል ከፍተኛ ግምት ለማግኘት የቻሉ ኦሎምፒያዎች ናቸው፡፡ የቴክኒክ ዲያሬከተሩ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎ በለንደን ኦሎምፒክ በመካከለኛ ርቀት በተለይ በ800 ሜትር ጠንካራ አትሌቶች ለማሳተፍ መቻሉ በቀጣይ በብራዚል ለሚስተናገደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት 400ሜ እና 200 ሜትር ውድድሮች  ተሳትፎ እንዲኖራት መነቃቃት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

በመካከለኛ ርቀት ውጤታማ ይሆናሉ ከተጠበቁት ኦሎምፒያኖች አንዱ መሃመድ አማን ሲሆን በለንደን ለአገሬ የወርቅ ሜዳልያ ለማምጣት ጠንካራ ልምምድ በማድረግ ላይ ነኝ ብሎ ለአሶስዬትድ ፕሬስ ተናግሯል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ አንጋፋዎቹ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር ሻምፒዮናነታቸውን ለማስጠበቅ ይወዳደራሉ፡፡

በ30ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች

በ10ሺ ሜትር

በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፤ በላይነሽ ኦልጅራ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ (ተጠባባቂ አበሩ ከበደ)

በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፤ ታሪኩ በቀለ፤ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም (ተጠባባቂ ሌሊሳ ዴሲሳ)

በ5ሺ ሜትር

በሴቶች መሰረት ደፋር፤ ገለቴ ቡርቃ፤ ገነት ያለው (ተጠባባቂ ጥሩነሽ ዲባባ)

በወንዶች ደጀን ገብረ መስቀል፤ ሃጎስ ገብረህይወት፤ የኔው አላምረው

በ800 ሜ

በወንዶች መሃመድ አማን

በሴቶች ፋንቱ ሚጌሶ

በ1500 ሜትር

በሴቶች አበባ አረጋዊ፤ ገንዘቤ ዲባባ ፤ መስከረም አሰፋ

በወንዶች መኮንን ገብረመድህን፤ ዳዊት ወልዴ፤ ተሾመ ዴረሳ (ተጠባባቂ አማን ዎቴ)

በ3ሺ ሜትር መሰናክል

በሴቶች ሶፍያ አሰፋ፤ ህይወት አያሌው፤ እቴነሽ ዲሮ (ተጠባባቂ ዘመዘም አህመድ)

በወንዶች ሮባ ጋሪ፤ ብርሃኑ ጌታሁን፤ ናሆም መስፍን

በማራቶን

በሴቶች ቲኪ ገላና፤ አሰለፈች መርጊያ፤ ማሬ ዲባባ (ተጠባባቂ ብዙነሽ በቀለ)

በወንዶች አየለ አብሽሮ ፤ ዲኖ ሰፈር፤ ጌቱ ፈለቀ (ተጠባባቂ ታደሰ ቶላ)

በ400 ሜትር በወንዶች በረከት ደስታ

በውሃ ዋና በሴቶች ያኔት ስዩም

የእንግሊዝ ኤምባሲ እና እንግሊዛውያኑ ተማሪዎች

ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምቤሲ ከኢስትአፍሪካን ቦትሊንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የሽኝት ግብዣ አድርጓል፡፡ በስነ ስርዓቱ በእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ሄነሪ ቢሊንግሃም፤ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ግሬግ ዶሬይ እና የስፖርት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አንበሴ እንየው የክብር እንግዶች ነበሩ፡፡ በስነስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሚር ሄነሪ ቤሊንግሃም የኢትዮጵያ አትሌቶች በኦሎምፒክ መድረክ ታላቅ ታሪክ እና አስተዋፅኦ ያላቸው መሆኑን ገልፀው የለንደን ኦሎምፒክ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ውጤት የአገራቸውን ገፅታ ለመገንባት የሚፈጠረውን መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አንበሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ ለሚኖራት ውጤታማነት አትሌቶች የተሟላ እና በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ማስተማመኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመላው የአለም አገራት የሚገኙ የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ከለንደን ኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ ለውድድሩ በቂ ትኩረት እና መሟሟቅ ለመፍጠር ሲሰሩ መቆየታቸውን ለስፖርት አድማስ የገለፀችው ደግሞ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ፕሬስና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኦፊሰር ቤተልሄም ተስፋዬ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የእንግሊዝ ኤምባሲ  ከኦሎምፒኩ ጋር በተያያዘ ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ የፕሬስና ፕብሊክ ዲፕሎማሲ ኦፊሰሯ በወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ እና በሬድዮ በተሰሩ ፕሮግራሞች የኦሎምፒኩን መሰናዶ ስናሟሙቅ ቆይተናል ብላለች፡፡ በተለይ ደግሞ በሶስት የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ስኬት ላይ ያተኮረ የኦሎምፒክ ተስፋዎች የሚል ርእስ ያለው ፊልም በእንግሊዝ ኤምባሲ ትብብር መሰራቱን ጠቅሳለች፡፡ ፊልሙ በ800 ሜትር ሯጩ መሃመድ አማን በውሃ ዋና ኦለምፒያኗ ያኔት ስዩም እና  በፓራ ኦሎምፒኩ አትሌት በሆነው ተስፋለም ገብረየስ የስኬት ታሪክ ላይ የተሠራ ነው፡፡ የእንግሊዝ ኤምባሲ በእነዚህ ኦሎምፒያኖች ላይ በማተኮር ፊልሙን የሰራው ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ስኬታማ እና ዝነኛነትን ከተጎናፀፈችባቸው የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ባሻገር በሌሎች የውድድር መደቦች ያላትን ተሳትፎ እውቅና በመስጠት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማበረታታት ታስቦ ነው መሆኑን ኦፊሰሯ ተናግራለች፡፡

የእንግሊዝ አምባሳደር ሚር ግሬግ ዶሬይ የኦሎምፒክ ችቦ ለንደን በገባበት እለት እና 100 ቀን ኦሎምፒኩ ሲቀረው ይህን ሁኔታ ለማሰብ በአዲስ አበባ የለንደን ኤምባሲ ደጃፍ የለንደን 2012 ባንዲራን ሲሰቅሉ የረዳቻቸውን ኦሎምፒያን ያኔት ስዩም በተመለከተ አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ አምባሳደሩ ስለ ወጣቷ ኦሎምፒያን ያኔት ስዩም ሲናገሩ  ለኦሎምፒክ ብቻ ሳይሆን የኮሌጅ ፈተናዋን በብቃት ለመወጣት እየተዘጋጀች ያለች ወጣት መሆኗን ጠቅሰው በቂ ባለሙያና የልምምድ ስፍራ በሌለበት አገር ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚያበቃ ውጤት አስመዝግባ ለኦሎምፒክ ተሳታፊነት በመብቃቷ ለወጣት ኢትዮጵያውያን ምሳሌ ያደርጋታል ብለዋል - በውሃ ዋና ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል በታሪክ የመጀመርያዋ የሆነችው  ኦሎምፒያን ያኔት ስዩም በ50 ሜትር የጀርባ ዋና 38.06 ሰኮንዶች፤ በ50 ሜትር ፍሪ ስታይል 33.17 ሰኮንዶች በሆኑ ጊዜዎች ባለፈው 1 ዓመት ለኦሎምፒክ ያበቃትን ፈጣን ሰዓቶቿን አስመዝግባለች፡፡

በሌላ በኩል በእንግሊዝ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በ30ኛው ኦሎምፒያድ የሚሳተፉ አገራትን ለመደገፍ በሚያስችል መስተንግዶ ላለፉት 6 ወራት ሲዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ በዚሁ የመስተንግዶ ፕሮግራም መሰረት የኢትዮጵያን ኦሎምፒክ ቡድን ለመደገፍ እየተዘጋጁ ያሉት በበርሚንግሃም ኦልድ በሪ የሚገኘው የፔሪፊልድስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መምህራን ናቸው፡፡ የፔሪፊልድስ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ለመደገፍ የመረጡት በኃይሌ ገብረስላሴ የአትሌቲክስ ስፖርት ስኬቶች እና ክብሮች በመማረክ መሆኑን በለንደን2012 ድረገፅ የገለፁት የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰባስቲያን ኮው ሲሆኑ ይህንኑ የተማሪዎቹን ምርጫ አድንቀዋል፡፡ የፔሪፊልድስ ተማሪዎች ከኢትዮጵያ ባሻገር በፓራ ኦሎምፒክስ ለዛምቢያ ድጋፍ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ለኢትዮጵያ የተሰጡ የሜዳልያ ትንበያዎች

የለንደን ኦሎምፒክ ከመጀመሩ 100 ቀናት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ ሲሰጡ በነበሩ ትንበያዎች በቀነኒሳ በቀለ ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ ድል የተወሰኑ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለሚኒማ በተወዳደሩባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮችና የዳይመንድ ሊግ ክንውኖች ያሳዩት ብቃት ደግሞ ባለፉት ሁለት ወራት ለኢትዮጵያ የሜዳልያ እድል የሚቀርቡ ትንበያዎችን ለውጧቸዋል፡፡ 30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ ሊጀመር አንድ ሰሞን ሲቀረው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰሩ ትንበያዎችን በመዳሰስ ለመረዳት እንደሚቻለው በለንደን ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ስኬት ወደ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች ከፍ ብሏል፡፡

ጎልድማን ሳክስ ለለንደን ኦሎምፒክ የሜዳልያ ድሎች የሰራውን ትንበያ ከሳምንት በፊት ይፋ ያደረገው በባለ48 ገፅ ሪፖርት ነው፡፡ የኩባንያው ምሁራን በ30ኛው ኦሎምፒያድ  ሊገኙ የሚችሉትን ሜዳልያዎች ለመተንበይ የየአገራቱን የኦሎምፒክ ተሳትፎ እና ውጤታማነት ካሉበት ነባራዊ የኢኮኖሚ እድገት ጋር በማያያዝ በሰሯቸው ቀመሮች ተጠቅመዋል፡፡ በጎልድማንሳክስ ትንበያ መሰረት ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ ከ4ዓመት በፊት ቤጂንግ ላይ ካስመዘገበችው የወርቅ ሜዳልያ ብዛት በአንድ ቀንሳ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከዓለም 26ኛ ደረጃ እንደሚኖራት፤ በአጠቃላይ የሜዳልያ ስብስብ በቤጂንግ ከነበረው በአንድ ብልጫ ባሳየ የ8 ሜዳልያዎች ስብስብ ከዓለም 27ኛ ደረጃ እንደምታገኝ ተገምቷል፡፡ በሆላንዱ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ግሮኒገን የኢኮኖሚ እና የቢዝነስ ፋክልቲ በተሰራው ትንበያ ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ 3 የወርቅ፤ 2 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከዓለም 25ኛ ደረጃ ታገኛለች ተብሏል፡፡ አ ኤል ኤስ የተባለ ጥናት አድራጊ ተቋም በሰራው ትንበያ ደግሞ ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን ጨምሮ በድምሩ 8 ሜዳልያዎችን በማግኘት በዓለም 19ኛ ደረጃ ልታገኝ ትችላለች፡፡

 

 

Read 3094 times Last modified on Friday, 13 July 2012 16:50