Saturday, 20 June 2020 11:16

በህዳሴ ግድብ ጉዳይ አሜሪካ የያዘችው አቋም ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     ግብጽ ለተመድ የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ አቀርባለሁ ብላለች

               በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ድርድር ላይ አሜሪካ እየፈጠረች ያለውን ወገንተኛ ተፅዕኖ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ፖለቲከኞች እየተቃወሙ ነው።
የአሜሪካ ብሄራዊ የጸጥታ ም/ቤት ረቡዕ እለት በትዊተር ገፁ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ውኃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አለባት ብሏል። ስምምነት ሳይደረስም ውሃውን መሙላት የለባትም ብሏል - ም/ቤቱ በመግለጫው።
ይህን የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ በደስታ የተቀበሉት የግብፅ መገናኛ ብዙኃንና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ኢትዮጵያ ለአለማቀፍ ምክረ ሀሳቦች ተገዥ መሆን አለባት ብለዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቀጣይም ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
ይህን የአሜሪካና የግብጽ አቋም በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበራት እየተቃወሙ ሲሆን ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኞችም በትዊተርና ሌሎች የማህበራዊ ገፆች ላይ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነትን ኮንነዋል። ኢትዮጵያውያን የተጋረጠባቸውን ብሄራዊ የደህንነት ስጋት በጋራ ቆመው እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካውያን ኢትዮጵያውያን የዜጎች ምክር ቤት፤ አሜሪካ በተደጋጋሚ ለግብፅ እያሳየች ያለው ወገንተኝነት ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑን ጠቁሞ አገሪቱ እጇን ከጉዳዩ  ላይ እንድታነሳ ጠይቋል።
የም/ቤቱ ሊቀ መንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ፤ የአሜሪካ መንግሥት አሁን ላይ የያዘው አቋም የኢትዮጵያና የአሜሪካንን የቆየ ጠንካራ አጋርነትና ወዳጅነት ወደ ጎን የገፋ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በድርድሩ ጉዳይ ወገንተኛ አቋም እንደያዘ በተደጋጋሚ መታየቱን በመጥቀስም፤ ይህ አይነቱ ወገንተኝነት እንዲቆም ጠይቀዋል።
በአሜሪካ የሚኖሩ አሜሪካ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ማቀዳቸውም ተገልጿል።  ፖለቲከኛና አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በትዊተር ባሰፈረው ሃሳብ፤ “የአሜሪካ ደህንነት ቢሮ በቲዊተር የለቀቀው መልዕክት በይፋ ከግብፅ ጋር በመወገን ግልጽና ከፍተኛ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር መወሰናቸውን ያሳያል” ብሏል።
 “ቀድሞውኑ አሜሪካና የአለም ባንክን በዚህ ድርድር እንዲሳተፉ መፍቀድ አደገኛ ስህተት ነበር፤ አሁን ዋጋ እያስከፈለን ነው። ይህን አይን ያወጣ ወገንተኝነታቸውን ሳናወላውል በአንድነት ልንቃወመው ይገባል” በማለት ተቃውሞውን ገልጿል ጃዋር አህመድ።
አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ፤ አሜሪካ በቀጠናው ኢትዮጵያን መፍራት አለባት፤ አንድም በዲፕሎማሲ ኮስተር ሊባልባቸውና ፊታችንን ልናዞርባቸው እንደምንችል ማሳየት በሌላ በኩል ደግሞ እንደለመዱት የውስጥ ፖለቲካችን ላይ እንዳይፈተፍቱ ቁርጠኛ የፖለቲካ ስራ መስራት ያስፈልጋል” ብሏል በማህበራዊ ገፁ።
ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ የማህበራዊ ገፆቻቸው “I cant breath” በሚል ሃሽታግ አሜሪካ ለያዘችው አቋም ያላቸውን ተቃውሞ እየገለፁ ሲሆን ይህን ጉዳይም አልሃራም የተሰኘው የግብፅ ጋዜጣ ዘግቦታል።
በአሜሪካ ታዋቂው የህግ ምሁር ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማሪያም በበኩላቸው፤ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ሃላፊ ስቴቭን መኑሽ በጻፉት ደብዳቤ፤ መንግሥታቸው ከወገንተኝነት ነፃ እንዲሆን ጠይቀዋል።
ግብጽ ለድርድሩ ቀናነት እንደሌላትና በየጊዜው የጦርነት ማስፈራራቶች እየፈፀመች መሆኑን የጠቆሙት ፕ/ሩ፤ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ቢሮ በማይመለከተው ጉዳይ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ባለፈው የካቲት ወር በሶስቱ አገራት እንዲፈረም የተዘጋጀውና ኢትዮጵያ ያልተቀበለችው የስምምነት ሰነድ ይፋ እንዲደረግና በግልጽ ውድቅ እንዲሆንም ፕ/ር አለማየሁ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።
አሜሪካ በድርድሩ ያላትን ሚና እንድትቀንስና ለአፍሪካዊው ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በማክበር ችግሩ በአፍሪካ ህብረትና አፍሪካ አቀፍ ተቋማት በኩል እንዲፈታ ትብብር እንድታደርግም ፕሮፌሰሩ መክረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በድጋሚ ለቀናት ሲያካሂዱት የሰነበተው ድርድር በግብጽ ግትር አቋሞችና “እኔ ብቻ ውሃውን ልጠቀም” እብሪቶች እንቅፋት እየገጠመው መሆኑን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ከዚህ በኋላ በግብፅ ምክንያት ድርድሩ የሚቋረጥ ከሆነ ኢትዮጵያ ለድርድር እንደማትቀመጥ አስገንዝበዋል፡፡
“ግብፅ በአንድ በኩል በድርድሩ ውስጥ ትሳተፋለች፤ በሌላ በኩል ለፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ ታቀርባለች” ያሉት አቶ ገዱ፤ ይህ ወላዋይ አካሄድ ለድርድሩ ክብር አለመስጠቷን ያሳያል።
“እየተደራደርን ያለነው ምንም መስጠት ከማትፈልግ፣ ሁሉንም መውሰድ ከምትፈልግ አገር ጋር ነው” ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከአባይ የመጠቀም ሉአላዊ መብታችንን በምንም መንገድ አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ በቁርጠኝነት ተናግረዋል።
ሱዳን በበኩሏ፤ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ ሶስቱም አገራት እኩል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ፍላጎትና አቋም እንዳላት አስገንዝባለች። ያሉ ልዩነቶችም በድርድሩ ብቻ መፍትሄ እንዲያገኙ አቋሟ መሆኑን ሱዳን አስታውቃለች።
በቀጣይ የሶስቱ አገራት መሪዎች እስካሁን በተከናወኑ ድርድሮች ላይ መክረው ውሳኔ እንዲያሳልፉም ሱዳን ፍላጎቷ መሆኑን በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል ገልፃለች።

Read 8796 times