Saturday, 20 June 2020 11:15

ኢዜማ ከጣና ሃይቅ 672 ስኩዬር ኪ.ሜ ያህሉ ወደ የብስነት መለወጡን አረጋግጫለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የእንቦጭ አረም በጣና ሃይቅ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የተመለከተ ጥናት በባለሙያዎች ማካሄዱን የገለፀው ኢዜማ፤ ከሃይቁ 672 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ያህል የውሃ አካል ወደ የስብነት መለወጡን ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ቡድን በሃይቁ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በተመለከተ ባለሙያዎች አሠማርቶ ሲያጠና መቆየቱንና በዚህም ጥናት፣ ሃይቁ በእንቦጭ ምክንያት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋለጡን ለመገንዘብ እንደቻለ አስታውቋል፡፡
በ14 ገፆች ሰንዶ ባወጣው የጥናት ውጤት ሪፖርት ላይ እንደሚጠቁመው፤ ሃይቁ ከነበረው ተፈጥሮአዊ የ3,672 ስኩየር ኪ.ሜትር የውሃ አካል፣ አሁን በእንቦጭ ምክንያት ወደ 3ሺህ ስኩየር ኪ.ሜትር መጠን እንደወረደና 672 ስኩየር ኪ.ሜትር አካል ደግሞ ወደ የብስነት (መሬትነት) መለወጡን አስታውቋል፡፡
ይህም የሃዋሣና የዝዋይ ሃይቅ ተደምረው ያለውን ስፋት ያህል ወደ የብስነት መቀየሩን ያመላክታል ብሏል በጥናቱ፡፡
በአካባቢው የተፋሰስና የተፈጥሮ ጥበቃ ልማት ባለመከናወኑም የገማራ ወንዝ በየጊዜው ወደ ሃይቁ በሚቀላቅለው ደለል ምክንያት የጣና ቂርቆስ ደሴት በውሃ ከተከበበ ደሴትነት ወደ የብስነት ተለውጧል ይላል ጥናቱ፡፡
ይሄን ተከትሎም የጣና ሃይቅ የነበሩት የደሴቶች ብዛት ከ37 ወደ 36 መውረዱም ተጠቁሟል፡፡
ለሃይቁ አደጋ ላይ መውደቅ ከእንቦጭ አረም በተጨማሪ የተፈጥሮ እንክብካቤና ጥበቃ አለመከናወን፣ በከተማ መስፋፋት ምክንያት ፍሳሽ ወደ ሃይቁ መለቀቅና በውሃ አካሉ ዳርቻ የእርሻ ስራ መከናወኑን በምክንያትነት በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
የእንቦጭ አረም ከጣና በተጨማሪ በአባይ ተፋሰስ ላይም እየታየ መሆኑ በቀጣይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብም ስጋት መደቀኑን ጥናቱ ያሳስባል::
መንግስት በዘላቂነት አረሙን ለመከላከል ሁነኛ ሣይንሳዊ መፍትሔ ከማፈላለግ ጐን ለጐን፤ አሁን በአፋጣኝ በሰው ሃይል የሚወገድበትን ወጥነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋ የጠየቀው ኢዜማ፤ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃዎች ከምንጊዜውም በበለጠ በትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲከናወኑ ምክረሃሳብ አቅርቧል፡፡

Read 7695 times