Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 00:00

ቆይታ ከፓትሪክ ምቦማ ጋር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

41ኛ ዓመቱን የያዘው  የካሜሮን እና የአፍሪካ እግር ኳስ ምርጥ አጥቂ ፓትሪክ ምቦማ ጫማውን የሰቀለው ከሰባት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በሙሉ ስሙ ሄነሪ ፓትሪክ ምቦማ ዴም ተብሎ ይጠራል፡፡ የቀድሞው የአፍሪካ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች  ከካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ድሎች የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ያገኘ ነው፡፡ በተጨዋችነት ዘመኑ በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ 203 ጨዋታዎች አድርጎ 109 ጎሎች ያስመዘገበው ፓትሪክ ምቦማ በ5 አገራት በፈረንሳይ፤ ጃፓን፤ ጣሊያን፤ እንግሊዝና ሊቢያ በሚገኙ 8 ክለቦች በፕሮፌሽናል ደረጃ ተጫውቷል፡፡ ምቦማ በአሁኑ ግዜ በካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን በአማካሪነት እና በኤጀንትነት ያገለግላል፡፡

በቢዝነስ ስራዎቹ የተቃናለትና በፖለቲካ ጉዳዮች ባለው ተሰሚነት ከፍተኛ ክብር ያገኘ ስፖርተኛም ነው፡፡ የስፖርት አናሊስት ሆኖም በፈረንሳይ ለሚገኙ ትልልቅ የስፖርት ጣቢያዎች ሙያዊ ትንተና በመስጠት ይሰራል፡፡  ወደ እግር ኳስ ስፖርት ከተመለስኩ በአሰልጣኝነት ከመስራት ይልቅ በስፖርት አመራር በካፍ ወይም በፊፋ ለማገልገል ፍላጎት አለኝ የሚለው ፓትሪክ ምቦማ ለዚሁ እንዲያግዘው በስፖርት አስተዳደር ዲፕሎማውን ለመውሰድ እየተማረ ነው፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በስቴት ኦፍ ዩኒዬን ኮአሊሽን የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነቱ አዲስ አበባ ከነበረው ፓትሪክ ምቦማ ጋር ስፖርት አድማስ የሚከተለውን ልዩ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

ስለፕሌይ ፎር ዩኒዬን ዘመቻ

በስቴት ኦፍ ዩኒዬን ኮአሊሽን (SOTU) አስተባባሪነት የሚደረገው የፕሌይ ፎር ዩኒዬን ዘመቻ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ በሺዎች የሚገመቱ አፍሪካውያንን በማስተባበር በአፍሪካ አንድነት ስር  በፍትህ፤ በብልፅግና እና በመልካም አስተዳደር በጋራ ለመስራት የተጠነሰሱ እና ስምምነት የተደረገባቸው ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ላይ ቅስቀሳ በማድረግ ዘመቻው ይንቀሳቀሳል፡፡ በ1963 እኤአ በአፍሪካ ህብረት በመንግስታት መሪዎች ስምምነት ከተደረገባቸው 42 ድንጋጌዎች ተግባራዊ የሆኑት 25 ብቻ ናቸው፡፡ በተግባራዊነታቸው በፕሌይ ፎር ዩኒዬን ዘመቻ እየተደረገባቸው ያሉት 14 ድንጋጌዎች 10 ናቸው፡፡ የእነዚህ ድንጋጌዎች ተግባራዊ መሆን በሚሊዮኖች የሚገመቱ አፍሪካውያንን ህይወት በማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በፕሌይ ፎር ዩኒዬን ዘመቻ በበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት የሚሰሩት ሁለቱ የአፍሪካ የምንግዜም ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋቾች የካሜሮኑ ፓትሪክ ምቦማ እና የናይጄርያው ኑዋንኩ ካኑ ናቸው፡፡

ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ጉዳይ

እንደምታውቀው የስቴት ኦፍ ዩኒዬን ኮአሊሽን (SOTU) የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ነኝ፡፡ በዚህ ሃላፊነቴ የአፍሪካ መንግስታት በተለያዩ አህጉራዊ ጉባኤዎች ባፀደቋቸው ስምምነቶች ተግባራዊነት እንዲንቀሳቀሱ በማነሳሳት እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁትም ይህንኑ ስራ ለማከናወን ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ለህዝቦቻቸው በገቡት ቃል መሰረት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአህጉሪቷ እድገትና ልማት የሚያግዙ ስምምነቶችን ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡ የድጋፍ ፊርማዎችን በአህጉራዊ ደረጃ በማሰባሰብም ስንሰራ ቆይተናል፡፡ የእግር ኳስ ስፖርትን ለዚህ እንቅስቃሴ መሳርያችን አድርገናል፡፡ ፕሌይ ፎር ዘ ዩኒዬን በሚል  መርህ ከወር በፊት በማላዊዋ ከተማ ሊሎንግዌ የእግር ኳስ ወዳጅነት ጨዋታ አካሂደናል፡፡፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ከሚደረገው 19ኛው የመሪዎች ጉባዔ ጋር በተገናኘ አንዳንድ መሪዎችን ዘመቻችን እንዲደግፉ አግባባለሁ፡፡ በተለይ ከወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዝዳንት አገር ቤኒን መሪ ዣንፒንግ ጋር ስብሰባ አለኝ፡፡ አህጉራችን ለሚኖራት እድገት በሴቶች መብት መከበር፤ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ ስርዓት መዘርጋት፤ በሌሎች አጀንዳዎች የተደረጉ ስምምነቶች እና ውሎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቷ፤ በተማረ ኃይሏ እና በዳበረ የባህልና የቱሪዝም አቅሟ ተጠቅማ 21ኛው ክፍለዘመንን መሻገር አለበት፡፡  ስለፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ

ወደ እግር ኳስ ስፖርት ለመሳብ ዋናው ምክንያቴ ዓለም ዋንጫ ነው፡፡ በተለይ የአርጀንቲናው  ማርዮ ኬምፕስ የመጀመርያው ጀግናዬ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚያ በኋላም  ሚሸል ፕላቲኒን ተመለከትኩና እሱም ተምሳሌቴ ሆነ፡፡ በመቀጠል ማርኮ ቫንባስተንንም አየሁ፡፡ ከዚያ በኋላ  ወደስፖርቱ ገባሁና በወጣትነቴ ያደነቅኳቸውን ሁሉ በተምሳሌትነት ተከትዬ ፕሮፌሽናል ተጨዋች በመሆን ህልሜን አሳክቻለሁ፡፡

ያደግኩት በፈረንሳይ በመሆኑ ፕሮፌሽናል እግር ኳስን የጀመርኩት በታዋቂው የፓሪስ ሴንትዠርመን ክለብ  ነው፡፡ ከ1990 እስከ 1997 እኤአ  በ4 የፈረንሳይ ክለቦች በመዘዋወር ተጫውቻለሁ፡፡  በ3ቱ የውድድር ዘመናት የተጫወትኩት ለፓሪስ ሴንትዠርመን ነበር፡፡ ከዚያ በኃላ ገበያው ወደ ጃፓን እግር ኳስ እንድሄድ ምክንያት ሆነ፡፡ በካሜሮን ብሄራዊ ቡድን መጫወት ስጀምር ደግሞ ከጃፓን ተመልሼ በጣሊያን ሴሪኤ ሲወዳደሩ ለነበሩት ለካግሊያሪ እና ለፓርማ በመጫወት 4 የውድድር ዘመናትን አሳልፊያለሁ፡፡ በፓርማ በነበርኩበት ወቅት  በውሰት ወደ እንግሊዝ በመጓዝ ለሰንደርላንድ ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም በሊቢያው አልኢትሃድ አንድ የውድድር ዘመን አሳልፌ በድጋሚ ወደ ጃፓን በመመለስ እስከ 2005 እኤ በሁለት ክለቦች በመጫወት የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወቴን አሳልፊያለሁ፡፡ በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነት ቆይታዬ ከጆርጅ ዊሃ፤ ከጂያንሉጂ ቡፎን፤ ካናቫሮ፤ ከሊሊያም ቱራም፤ ከኤቶ ጋር በመጫወት ከፍተኛ ልምድ አግኝቻለሁ፡፡ በተለያዩ 3 አህጉራት ኳስን በመጫወቴ የብዙ ህዝቦችን ባህል አውቂያለሁ፡፡ ይህ ተሞክሮ በመልካም ባህርይ እና ተግባር ህይወቴን እንድመራ አድርጎኛል፡፡

በ27ኛው ኦሎምፒያድ ሲድኒ ላይ የማይበገሩት አንበሶች ስለተጎናፀፉት የወርቅ ሜዳልያ

በሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ ከካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ጋር የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት ስንበቃ  4 ጎል አግብቼ ነበር፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ አገርን ለሜዳልያ ክብር ማብቃት እጅግ ልዩ ስሜት የሚሰጥ እና ከፍተኛ ክብር የሚያጎናፅፍ ስኬት ነው፡፡ እንደ ኳስ ተጨዋች በኦሎምፒክ መድረክ ከፍተኛ ስኬት ለማግኘት ማንም ላያስብ ይችላል፡፡ በውድድር መድረኩ ማንኛውም አገሩን የወከለ አትሌት የሜዳልያ ስኬት ለማግኘት ያለውን ተስፋ እና ሲሳካለት የሚሰማውን ደስታ በእግር ኳስ ማግኘት በመቻሌ እኮራለሁ፡፡  ያኔ በኦሎምፒክ መንደሩ በነበረን ቆይታ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ አትሌቶች ጋር በመገናኘት ብዙ ተምረናል፡፡ በውድድር መድረኩ ለሁላችንም ስፖርትን የጋራ ቋንቋችን መሆኑን ምንግዜም የማልረሳው ትዝታ ነው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ አሸናፊ ሆነህ ሜዳልያህን አጥልቀህ የአገርህ ብሄራዊ መዝሙርን ስትሰማ እና ሰንደቅ አለማህ ሲሰቀል ወደ ሰማይ እንዳረግህ ያህል ይሰማሃል፡፡

የሲድኒ ኦሎምፒክ ትዝታው

እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ኃይሌ ገብረስላሴን አግኝተን አብረነው ፎቶ ለመነሳት የነበረንን ሽምያ አልረሳውም፡፡ በወቅቱ እኛም የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ የተሸለምን ብንሆንም ኃይሌ ግን ብዙ የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰበ  ምርጥ አትሌት መሆኑን እናውቅ ነበር፡፡

ኃይሌ ገብረስላሴን በሲድኒ ኦሎምፒክ ብቻ ሳይሆን በአንድ አጋጣሚ በዱባይ ማራቶን ሲወዳደር የመመልከት እድሉ ነበረኝ፡፡ በወቅቱ ኃይሌ በማራቶን ውድድሩ ሲያሸንፍ እና የቦታውን ሪከርድ ለመስበር በአንድ ሰከንድ ዘግይቶ ሳይሳካለት ቀርቶ ሲናደድ ተገርሜ ነበር፡፡ 42 ኪሎሜትር ሮጦ አሸንፏል፡፡ ብዙ ገንዘብ የሚያሸልመውን የሪከርድ ሰዓት በአንድ ሰከንድ በመዘግየቱ ሲያጣ ግን አልተዋጠልኝም ፡፡

የኦሎምፒክ መድረክን ከዓለም ዋንጫ እና ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር ጋር ሲያነፃፅረው

በስፖርት ዋናው ነገር ማሸነፍ ነው፡፡ በየትኛውም ውድድር ስታሸንፍ ደግሞ ልዩ ኩራት ይፈጠርብሃል፡፡ በእርግጥ በአፍሪካ ዋንጫ ለሁለት ጊዜ ሻምፒዮን በመሆኔና በሁለት የዓለም ዋንጫዎች ለካሜሮን ቡድን በመሰለፍና በሁለቱም ተሳትፎዬ አንድ አንድ ጎሎች በማግባቴ ተደስቻለሁ፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ ግን ካሜሮን የወርቅ ሜዳልያ እንድታገኝ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመቻሌ ግን በስፖርተኛነቴ ከፍተኛውን ክብርና ደስታ አጣጥሚያለሁ፡፡ ልጅ ሆነህ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ስፖርተኞች የወከሉአቸውን አገሮች በድል አድራጊነት ሲያደምቁ ስትመለከት የሚፈጠርብህ ተስፋ አለ፡፡ አድገህ ይህን ተስፋ ስታሳካ ደግሞ በጣም ልዩ ደስታ ይፈጥርልሃል፡፡

የማይበገሩት አንበሶች በሚለው ቅፅል ስያሜ በካሜሮን ማልያ የተጫወትኩበትን ዘመን እኮራበታለሁ፡፡ እግር ኳስ ተጨዋቾች የአገራቸው አምባሳደሮች ናቸው፡፡ ከማይበገሩት አንበሶች አንዱ ሆኜ የአገሬን ማልያ እና ሰንደቅ አለማ በመወከል በነበረኝ ውጤት ሁሉ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ፡፡

ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ

ሃቁን ለመናገር ስለእግር ኳሳችሁ ደረጃ ብዙም አላውቅም ነበር፡፡   ዘንድሮ ግን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ያስመዘገበው ውጤት ትኩረቴን ስቦታል፡፡ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ያደረጉትን ግጥሚያ ተመልክቻለሁ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከቤኒን ጋር አቻ በመውጣት ለአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣርያ ያለፈበትንም ግጥሚያ ተከታትያለሁ፡፡ በአፍሪካ አህጉር የሚመዘገቡ ውጤቶችን መከታተል ስራዬ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሁላችን የምናውቃት በሯጮቿ ነው፡፡ ወደፊት ምናልባት በምርጥ ኳስ ተጨዋቾቿም እናውቃት ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከ32 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንድታልፍ የሰጠው ምክር

በዚያ ወሳኝ ጨዋታ የሚመዘገብ ውጤት ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም እንዳለሁ እረዳለሁ፡፡ ግን በቅርብ ጊዜ በተካሄዱት የአፍሪካ ዋንጫዎች በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ የሌላቸው እንደኒጀር ኢኳቶርያል ጊኒ የመሳሰሉት አገራት ገብተዋል፡፡ ዋናው አስፈላጊ ነገር በቀና አስተሳሰብ ስኬትን ማግኘት እንደሚቻል ማሰብ ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አባላት ከጨዋታው በፊት በማያስፈለጉ መጨናነቆች ውጥረት ውስጥ መግባት የለባቸውም፤ በግጥሚያው ላይ በጥሩ ሞራል እና መነቃቃት ታሪክ ለመስራት መነሳሳት ይገባቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ የብሄራዊ ቡድኑን ተጨዋቾች በሁሉም ረገድ ብቁ ዝግጅት እንዲያደርጉ መስራት አለበት፡፡ ተጨዋቾችም በራሳቸው ጥረት ለውጤት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ላይ ከልክ በላይ ጫና የሚያሳድሩ ሁኔታዎችን ማብዛት አያስፈልግም፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ እና አባላቱ በራሳቸው ተማምነው በሚፈጥሩት  መነሳሳት የሚፈለገውን ታሪካዊ ውጤት እንዲያመጡ የሞራል ድጋፍ ማድረጉ ይበቃል፡፡

ለውጤት ማነስ ተክለሰውነት ምክንያት ነው

ዋናው ችግር የተክለሰውነት መግዘፍ ወይ ማነስ አይደለም፡፡ ተጨዋቾች እንደራሳቸው የአካል ብቃትና ተፈጥሮ ሊጫወቱበት የሚያስችል የታክቲክ እና የቴክኒክ ችሎታን አለማዳበራቸው ነው፡፡ በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በአካል ብቃት መግዘፍ ለውጤት ወሳኝ አለመሆኑን አሳይተውበታል፡፡ አንድ ውድድርን ለማሸነፍ የግድ ግዙፍ ጠንካራ እና ረጅም መሆን አያስፈልግም፡፡ በአካል ያነሰ ተፈጥሮ ከያዝክ ለዚያ የሚመች አጨዋወትን በማዳበር በየውድድር መስኩ ራስህን በመሆን ከቀረብክ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ፡፡

ኢትዮጵያውያን  በፕሮፌሽናልነት እንዲሳካላቸው

ወደ ፕሮፌሽናል ፉትቦል ለመግባት በአገር ውስጥ ውድድሮች ከፍተኛ እድገት እና የውድድር ጥንካሬ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ክለቦች ከአገር ወጥተው በአህጉራዊ ውድድሮች ውጤት ሲኖራቸው ተጫዋቾቹ በመልማዮቹ ዕይታ ውስጥ ይገባሉ ከዚህም በላይ በብሄራዊ በድን ደረጃ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ማግኘት ለፕሮፌሽናል ደረጃ በር ከፋች ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ለምታዘጋጀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማለፍ ከቻለ ተጨዋቾች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኙ እድሉን ይፈጥራል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ከእኔ የተሻለ ደረጃ ይኖረዋል ስለሚለው ልጁ

በፈረንሳይ የምኖረው ከምወዳት ባለቤቴ እና ከ5 ልጆቼ ጋር ነው፡፡ ልጆቼ በእድሚያቸው ከ8 እሰከ 19 ዓመት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 3 ወንድ ልጆቼ ኳስ ቢወዱም በተለይ እግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን የሚፈልገው ትንሹ የ10 ዓመት ልጄ ነው ፡፡ ይህ ልጄ አሁን በፓሪስ ሴንትዠርመን ወጣት ቡድን ገብቷል፡፡   ከኳስ ጋር ያለው ፍቅር በጣም ይገርማል በፊት ከመጫወት ይልቅ ኳሶችን መሰብሰብ ይወድ ነበር፡፡ ደስተኛ የሚሆነው ስለ እግር ኳስ ሳወራው ብቻ ነው፡፡ በእኔ ልጅነት አሁን እንዳለው ፕሌይስቴሽን፤ ልዩ ልዩ ጌሞች አልነበሩም፡፡ ድሮ ብቸኛ የልጅነት መዝናኛችን እግር ኳስ ነው፡፡ ያኔ ትምህርት ቤት ፤ቤትና ኳስ ነው፡፡ በዛሬ ልጅነት ግን ትምህርት ቤት፤ ቤት እና ከዚያም በጣም ብዙ ግዜ ማሳለፊያዎችና መዝናኛዎች አሉ፡፡ ይህ ልጄ እኔን መተካት ብቻ ሳይሆን ከእኔ የተሻለ ደረጃ እንደሚደርስ የማስበው ለዚህ ነው፡፡

 

 

Read 2442 times Last modified on Friday, 13 July 2012 16:46