Print this page
Saturday, 13 June 2020 13:52

የጨረቃ ፍቅር

Written by  ተመስገን
Rate this item
(9 votes)

    ህይወት የገባህና የምታውቀው፤ ያልገባህና የማታውቀው ገጠመኞች ድርድር ናት (life is a series of incidences እንዲሉ) … ዕንቁ ታደሰን ህይወት ምንድን ነው? ብለህ ብትጠይቀው… ያለ ጥርጥር… “እኔ እንጃ!!” ይልሃል፡፡ እንደሱ ዓይነቱን ሰው ዐዋቂዎች፤ absurd ይሉታል:: የተወለደው ጅጅጋ አካባቢ ነው፡፡… ገጠር ውስጥ፡፡ የተወለደበት መንደር ዛሬ የለችም፡፡… በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ሳቢያ ወድማለች፡፡ የነበረው እንዳልነበር ሆኗል፡፡
ዕንቁ ታደሰ የአስር ዓመት ልጅ ነበር… ያኔ:: ትንሽ፣ ትንሽ ትዝ የሚለው ነገር ቢኖር፣ አንድ ቀን ጠዋት የተደፋበትን ገሃነም ነው… ጩኸት፣ ፍንዳታ፣ ትርምስ፣ እሳትና ዋይታ!
ከእናቱና ከእህቱ ጋር እንዴት እንደተለያየ አያስታውስም፡፡ በደመ ነፍስ ሩጦ የት እንደደረሰና  ራሱን  ስቶ እንደወደቀም ዘንግቷል፡፡ ሲነቃና ወደ ህሊናው ሲመለስ ደግሞ ማንም ምንም በአካባቢው አልነበረም፡፡… ለጥ ብሎ ከተኛው አሸዋማ ሜዳ በስተቀር፡፡
ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት፣ ሙሉ ደማቅ ጨረቃ አዘቅዝቃ እያየችው ነበር፡፡ ዓይኑን እያሻሸ፤ ዕንባውን እየጠረገ ተመለከታት:: ቤታቸው ግድግዳ ላይ የነበረውን የእናቱን ፎቶግራፍ፣ በውስጧ የተመለከተ መሰሎት ደነገጠ፡፡ እንባው ተዝረከረከ፡፡ እማዬ!.. እማዬ! ነይ እያለ መጮህ ጀመረ፡፡
ቃኝ ወታደሮች ሲደርሱ ረሃብና እንቅልፍ እያንገላጀጀው ነበር፡፡ እነሱ ጋ በእንክብካቤ ሰነበተ። ቆይቶም እንደነሱ ቤተሰቦቻቸውን ካጡ ህፃናት ጋር ወደ አዲስ አበባ ተላከ:: ህፃናት ማሳደጊያ ገባ።… እየተማረም አደገ፡፡ ዕንቁ ታደስ ዛሬ አርባኛ ዓመቱ  ነው፡፡… አላስታወሰውም እንጂ፡፡ እሱ በተወለደበት ቀን በየዓመቱ ማህበር ታወጣ ነበር … እናቱ፡፡ ይህንንም ረስቶታ:: የማይረሳው ነገር አንድና አንድ ብቻ እየሆነ መጥቷል … ስለ ጨረቃ ማሰብ፣ ጨረቃን መናፈቅ፣ ስትገባና ስትወጣ ጠብቆ መሸኘት፡፡… ሙሉ በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ እናቱን ውስጧ ማየት፡፡
ዛሬ ጨረቃ ሙሉ ናት፡፡ ለሱ ግን “ልክ” አልመሰለችውም፡፡ ብርሃኗ ቀዝቅዟል፣ እናቱንም ውስጧ ማየት አልቻለም፡፡ ዕንቁ ታደሰ፤ ሃያ ዓመት ያህል ሲሆነው ራሱን ችሎ መኖር ጀምሯል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱ አንድ አንድ ደብዳቤ ፅፎላታል።… አላስተጓጎለም፡፡ ደብዳቤዎቼ አንድ ሺህ ሲሞሉ ራሴ እመጣለሁ ብሎ “ቃል” ገብቷል … ለራሱ… “Promise is debt” ይል ነበር እየደጋገመ፡፡
ዕንቁ ታደሰ፤ “ቃል አለብኝ” ይበል እንጂ በኑሮው ምንም የጎደለበት ነገር የለም:: ሆኖም ሰው ኑሮው ቢጓደልበት… ሥራ፣ ትምህርት፣ ፍቅር፣ ጓደኝነትና ሌላም ነገር አልሳካ፣ አልዋጣላት ቢለው ተስፋ መቁረጥ የለበትም ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ የተዘጉ በሮችን በየተራ ማንኳኳት፣ አንዳንዱንም በግድ ለመክፈት መታገል መቻል አለበት፡፡ አንዱ ውስጥ የምንፈልገውን እናገኛለን ይል ነበር፡፡… በትግል የሚመጣ ደግሞ “ልክ” ነው ብሎ ያምናል፡፡ ዕድልና አጋጣሚን ተስፋ አድርጎ መቀመጥ ያላኖሩትን ዕቃ እንደ መፈለግ ይቆጠራል… እሱም ቢሆን የሚሆነው “ሲኖሩ” ነው ይለናል፤ እንቁ ታደሰ፡፡
… ዕውነት ነው፡፡ ሞት የሚጀምረው ሰው፤“ተስፋ የለኝም” ብሎ ማሰብ የጀመረ ጊዜ ነው፡፡ በተስፋ ጊዜ ይገዛል፣ በጊዜም ጊዜ ይቀየራል፡፡ የማይቀየር፣ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ ቢኖርም ራሱ “ለውጥ” የሚባለው ነገር ብቻ ነው፡፡… “Change is the unchanging reality” እንዲሉ፡፡
ምንም እንኳ ጨረቃዋ የቀዘዘችና የፈዘዘች ብትመስልም ወይም እሱ እንደሚለው “ልክ” ባትሆንም አየሩ ለስላሳና መንፈስ የሚያረጋጋ ነው። ዕንቁ ታደሰ ምቾት ተሰምቶታል፡፡ የመጨረሻውን ደብዳቤ ሊፅፍ የተዘጉትን በሮች አልፎ፣ ሁሌ ለሁሉም ክፍት ሆኖ ከሚጠብቀው የሞት በር ላይ ቆሟል፡፡ አንዴ ወደ ላይ አንጋጠጠ፡፡ “መጣሁ” እንደ ማለት ዓይነት፡፡… ፊቷን ያዞረች መሰለው፡፡
…ብዕሩን አወጣና መፃፍ ጀመረ፡፡
ይድረስ “ላንቺ”
አንቺ ከጥበብ በላይ ቆንጆ ነሽ፡፡ ቁንጅና ደግሞ መንፈስ ነው፡፡ መንፈስ ደግሞ ሚስጢር ነው። ሚስጢር ደግሞ የእውነቶች ሁሉ እምብርት ነው። ዕምብርቴ ከእምብርትሽ ተቋጥሯል፡፡ ያላንቺ ሰማይና ምድር ተረት ናቸው፡፡ አንቺ የሌለሽበት ሰማይ፣ አንቺ የሌለሽበት ምድር አይገባኝም:: አንቺ የሌለሽበት ዛሬ፣ አንቺ የሌለሽበት ነገ ትርጉም የለውም፡፡ ጊዜ ባንቺ ፊት አይቆምም፡፡ ጊዜ የሚገደበው በሰዓት ፍሬም ውስጥ ብቻ ነው፡፡ አንቺ ዘለዓለም ነሽ፡፡
ሰዎች ሁሉ ሲመለከቱሽ ውለው ሲመለከቱሽ ቢያድሩ የኔን ቅንጣት ያህል አይረዱሽም፡፡ መጽሃፍት እንደ ተራራ ቢከመሩ፣ እንደኔ ኮስማና ዓረፍተ ነገር አይገልፁሽም፡፡ ሰዓሊ ውቅያኖስን ያህል ቀለም በጥብጦ ቢቀባባሽ እንደኔ አይን ብሩሽ፤ እንደ ልቦናዬ ፎቶ አያስውብሽም:: ቀራፂ ከወርቅና አልማዝ ቢጠርብሽ እንደኔ በልክሽ አያንፅሽም። ገጣሚ ቅኔውን እንደ ዝናብ ቢያወርድብሽ፣ የኔን ዝምታ ያህል አያሞካሽሽም፡፡
እኔ ትዝታዎቼን አልፌ፤ ተስፋዎቼን ኖሬ “አሁኔ” ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ትናንትናና ነገ አያስፈልጉኝም። አሁን ማለት ፅድቅ፣ አሁን ማለት ኩነኔ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን “አሁን” ማለት “ጊዜ” ማለት እንዳይመስልሽ:: አሁን ማለት “መሆን” ማለት ነው፡፡ አሁን ወደ ቀለም አልባ ህላዌነት ስቀየር ተመልከቺኝ፡፡… እኔን እየሆንኩልሽ ነው… ይኸው!!
“ያንቺው” ብሎ ስሙን መፃፍ ሲጀምር፣ ብዙ ሴቶች እየተሳሳቁ ብቅ አሉ፡፡ ገመዱን ከቋጠረበት ዛፍ አጠገብ ባለችው ጠባብ መንገድ ተግተለተሉ፡፡… እንዳያዩት ተሸሸጉ:: ሞቅ ያላቸው፣ ፅዋ የሚሸኙ ማህበርተኞች መሆናቸው ያስታውቃል፡፡
ወደ ሁዋላ ከቀሩት ሴቶች አንዷ ከመንገዱ ዳር ወጣ ብለው ቁጭ አሉ፡፡ ቀሚሳቸውን ሰብሰብ አርገው መሽናት ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ እንቁ ታደሰ፣ አንድ ሃሳብ መጣለት፡፡ በኪሱ ውስጥ የያዘውን ገንዘብ ሊሰጣቸው ፈለገ፡፡ እስኪጨርሱ ጠበቃቸውና “እማማ” ብሎ ጠራቸው፤… ወደ እሳቸው እየተጠጋ። ሴትየዋ ወንድ መሆኑን ሲያውቁ፤ “በስመአብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ.. ማነህ?” አሉ ደንገጥ ብለው፡፡ የተጠቀለለውን ገንዘብ፣ ሰዓቱንና ሃብሉን የጨበጠበትን እጁን እየዘረጋላቸው፤ “አይዞት… ይህንን ገንዘብና ዕቃ አልፈልገውም ውሰዱት..እን…”፣ “እንኩ” ለማለት የመጨረሻዋን ፊደል ሳይጠራ፣ ደንገዝገዝ ብላ የነበረችው ጨረቃ ድንገት የባውዛ ያህል ፏ አለች፡፡ ሁለቱም ደነገጡና ወደ ላይ ተመለከቱ፡፡ ዕንቁ ታደሰ፤ የሴትየዋን ፊት ሲመለከት ፍርሃት፣ ፍርሃት አለው፡፡ ሴትየዋም ዓይን ዓይኑን ትክ ብለው እያዩት፣ መንቀጥቀጥ ጀምረዋል፡፡ እንደ ምንም ከንፈሩን አላቆ፤ “እ.. እን..” እያለ ሲንተባተብ፣ ሴትየዋ እንደ መባነን አሉና፤ “ቁ” በማለት የመጨረሻዋን ፊደል ሲጠሩ… “እ…እ” ሲላቸው…እየደጋገመ፤ “ዕንቁ! ዕንቁዬ!” ብለው ጮሁ፡፡ ዘሎ ተጠመጠመባቸው፡፡ ከእቅፋቸው የተላቀቁት “እማዬ ምን ሆነሽ ነው?” የሚለውን ድምፅ ሲሰሙ ነበር፡፡
“ቃል” እዚህ ጋ ተሰረዘ!!
***
ከአዘጋጁ፡- (ከአዲስ አድማስ ዌብሳይት ላይ ተወስዶ በድጋሚ ለንባብ የቀረበ አጭር ልብወለድ ነው፤ ሴፕተምበር 11 2017)


Read 2367 times