Saturday, 13 June 2020 13:50

ትርጉም የሥነፅሁፍ ስራዎች፤ ለምንና እንዴት?

Written by  በመኮንን ተሾመ ቶሌራ (በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ ሜ.ኤ.)
Rate this item
(1 Vote)

   ሥነ-ፅሁፋዊና ሥነ-ፅሁፋዊ ያልሆኑ ስራዎችን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላኛው መተርጎምና ለአንባቢዎች ማቅረብ በአለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት ሁሉ የተለመደ ተግባር ነው። የትርጉም ስራ ለተለያዩ አላማዎችና ውጤቶች ይሰራል። የትርጉም ስራዎች፤ በሌላ ቋንቋዎች የተፃፉ ፅሁፎችን ለአንባቢያን ወይም ለተገልጋዮች በራሳቸው ወይም በሚገባቸው ቋንቋ ለማቅረብ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በተጨማሪም የአንድን ማህበረሰብ ባህሎች ፣ ልምዶችና  ወጎች  ለሌሎች  ለማካፈል ወሳኝ ናቸው።
በሀገራችንም በተመሳሳይ ሁናቴ ትርጉሞች ከውጭ ቋንቋዎች ወደ አማርኛ በብዛት የሚሰሩ ሲሆን አልፎ አልፎም ወደ ሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎችም ይተረጎማሉ። ከአማርኛም ወደ ሌሎች ብሔረሰብ ቋንቋዎችም የትርጉም ስራዎች እንደሚሰሩ ይታወቃል።
ይህችን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ከትርጉም ጋር በተያያዘ በቅርቡ ወዳጄ ኪዳኔ መካሻ በሰሜን አሜሪካ  የኖርዝ ካሮላይና ፕሮፌሰር የሆኑት ኦማር ሁሴን አሊ፣ በ2016 እ·ኤ·አ· ያሳተሙትን “MALIK AMBAR (Power and Slavery Across the Indian Ocean)“ የተሰኘ  መፅሐፍ “ማሊክ አምባር ፦ ከቀንበር እስከ መንበር” በሚል ተርጉሞ ማውጣቱን  ተከትሎ፣ አንብቤ አስተያየቴ እንድሰጠው ስለጠየቀኝ ነው፡፡
ታዲያ  መፃፌ ካልቀረ እንደ ሥነፅሁፍ ተማሪነቴ፣ ባዲሱ መፅሐፍ ላይ ለሱ ለብቻው፣ ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ደግሞ ትንሽ ስለ ትርጉም ስራዎች የሚታየኝን ወርወር ባደርግ መልካም ሆኖ ስለተሰማኝ፣ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ እንዳሉት፣ ይችን ፅሁፍ “ልዶገዱግ” ወደድኩኝ።
ሌላው ከዚህ ቀደም ስለ ትርጉም ስራ ችግሮች ከቀድሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚደንት ከአቶ ጌታቸው በለጠ ጋር ባጋጣሚ ያወጋነው ሁልጊዜ ትዝ ስለሚለኝና በትርጉም  ስራዎች ላይ እኔ እስከማውቀዉ ድረስ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም (ILS)  ባሉት ተቋማት ካልሆነ በስተቀር ለምልአተ ህዝቡ በሚሆን መልኩ በቂ የሂስ ስራ ሲሰራ ባለማየቴ  ነዉ።
የትርጉም ስራ በኢትዮጵያ
የትርጉም ስራ በኢትዮጵያ በጣም እረዥም ታሪክ ያለው ነዉ። ሃገራችን  የቀደምት ስልጣኔዎች አካል  ከመሆኗና ከነበራት ሰፊ አለማቀፍ ግንኙነት አንጻር፣ ጥንታዊ መፃህፍትን የማግኘት፣ ወደ ራሷ ቋንቋ የመተርጎምና የማስተርጎምም እድሉ ነበራት፡፡ በተለይም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአክሱም ነግሶ የነበረው ንጉስ ኢዛና፣ የክርስትናን ሃይማኖት መቀበሉን ተከትሎ፣ በአቡነ ሰላማና በዘጠኙ ቅዱሳን አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በስፋት እንዲሰራ አድርጓል፡፡ ገና በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አራቱን ወንጌሎች፣ ቀጥሎም ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉመዋል:: ከጥንታዊ የግእዝ ትርጉም መፃሕፍትም መጽሐፈ ቄርሎስ እና ፊሳሎጎስ የተባሉት ይገኙበታል።
 በዘመናዊ ኢትዮጵያም በርካታ ድንቅ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ተተርጉመው ለንባብ እንደበቁ እናውቃለን። ለምሳሌ በ1940ዎቹ እነ ከበደ ሚካኤል የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌት የመሳሰሉ ስራዎችን አበርክተዋል፤ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንም በርካታ የሼክስፒር ስራዎችን በላቀና ድንቅ ብቃት፣ በ1960ዎቹ  ወደ አማርኛ     ተርጉሞልናል፡፡  በደርግ ዘመንም የ“ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት”፣ በአብዛኛው ከሶሻሊስት ሶቪየት ህብረት የተተረጎሙ የሥነጽሁፍ ስራዎችን በስፋት በአማርኛ አድርሶናል:: በዚያው ዘመን የዳኒኤላ ስቴልን፣ የሲድኒ ሸልደንንና የአርቪንግ ዋላስን እንዲሁም የጃኪ ኮሊንስን  ስራዎች ጨምሮ ሌሎች ልብወለዶች በአማርኛ ተተርጉመው ለማንበብ ችለናል፡፡  
የትርጉም ስራዎች ጠቀሜታ
ከላይ እንደተጠቀሰው፤ የትርጉም ስራዎች በአብዛኛው በሌላ ቋንቋዎች ተፅፈው የነበሩን አንዳንድ ፅሁፎችን ለሌላ ቋንቋ አንባቢያን ወይም ተገልጋዮች በራሳቸው ወይም በሚገባቸው ቋንቋ ለማቅረብ ሊሰሩ ይችላሉ። እንዲሁም የአንድን ማህበረሰብ ባህሎች፣ ልምዶች፣  ዘይቤዎች፣ ወጎች፣ እሴቶች፣ ስነቃሎች፣ ተረቶች፣ አፈ-ታሪኮች፣ ሀተታ-ተፈጥሮዎች፣ ሀገር በቀል እውቀቶችና የመሳሰሉትን ለሌላው ለማካፈልና ለማሳወቅ እንዲሁም እንደ መዝናኛ ለመጠቀምም የትርጉም ስራዎች ይሰራሉ።
በተጨማሪም የትርጉም ስራዎች ሥነፅሁፍን ለማጎልበትና ያፃፃፍ ስልትን ከሌሎች ለመማር ያግዛሉ። እንዲሁም ለትምህርትና ለመዝናናትም ጠቀሜታቸዉ የጎላ ነዉ። በሌላ በኩልም ለህትመት ኢንዱስትሪውና ለሥነፅሁፍ ባለሙያዎችም የስራ እድልን በመፍጠርም የራሱ ሚና ይኖረዋል።
ከጥሩ ተርጓሚዎች ምን ይጠበቃል?
ብቃት ያላቸው ተርጓሚዎች ሊኖሯቸው ይገባል ብለው ብዙዎቹ የቋንቋ ጠበብት የሚስማሙባቸው ክህሎትና ዕውቀቶች  የሚከተሉት ናቸው፡-
* ሞያዊና ጥልቅ የሆነ፣ ትርጉም የሚሰራበት ምንጭ ቋንቋ እውቀትና ክህሎት - Source Language (SL) skills
* ሞያዊና ጥልቅ የሆነ፣ ትርጉም የሚሰራለት መዳረሻ ቋንቋ እዉቀትና ክህሎት - Target Language (TL) skills
*ሙያዊ እውቀት /Specialisation/ (አንድ ጥሩ ተርጓሚ ትርጉሙ በሚሰራበት ጉዳይ ወይም ኢንዱስትሪ ዙሪያ  ጠለቅ ያለ እውቀት ቢኖረው በጣም ተመራጭ ነው)
* የፅሁፍ ችሎታ
* የትምህርት ዝግጅትና ጠቅላላ እውቀት
*  ለትርጉም ስራ የሚሆኑ ግብአቶች (ለምሳሌ፡- እንደ መዝገበ ቃላትና ማጣቀሻ መፃህፍት ወ·ዘ·ተ·)
*ባለንበት ዘመን ደሞ ኮምፒውተር ተጠቃሚ ቢሆን ይመረጣል፡፡
ሥነፅሁፋዊና ሥነፅሁፋዊ ያልሆኑ ስራዎች ትርጉም ልዩነትና አንድነት
አንድ ተርጓሚ የትርጉም ስራ ከመጀመሩ በፊት ሊተረጉም ያሰበው ስራ ሥነፅሁፋዊ ወይም ሥነፅሁፋዊ ያልሆነ መሆኑን ማጤን ይኖርበታል። ምክንያቱም ሁለቱ ልዩነትና አንድነት አላቸውና፡፡
ሥነፅሁፋዊ የትርጉም ስራዎች
ሥነፅሁፋዊ ስራዎች በአብዛኛዉ ፈጠራና ምናባዊነት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ሥነፅሁፋዊ የሆኑ ፅሁፎችን ስንተረጉም ፊደላዊ ቅርፅን ብቻ ሳይሆን ዐውዳዊ ፍችውንም በትክክል ለማግኘት ማሰብ (analysing the text and the context) ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ የሥነፅሁፍ ባለሞያዎች ይህንን ለመግለፅ ”A literary translation must reflect the imaginative, intellectual and intuitive writing of the author” በማለት ይገልፃሉ።
በአብዛኛው ሥነፅሁፋዊ በሆኑ ፅሁፎች መልእክት በቀጥታ ስለማይነገር ፀሀፊው ሊል የፈለገውን በትክክል ለማግኘት ጥንቃቄን የተከተለ አካሄድ ያስፈልጋል። ቀደም ባለው ጊዜ በሥነፅሁፋዊ ትርጉም ጊዜ ምሁራን ፕራግማቲዝም (Pragmatism) የተሰኘውንና የደራሲውን ትክክለኛ መልእክትና ፍላጎት (Intentionality)፣ የሁኔታዎችን (Situationality) እና የትርጉሙን ተቀባይነት (Acceptability) ጨምሮ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም የትርጉም ስራን በትክክል ለመስራት እንደሚቻል ይመክሩ ነበር።
ባጠቃላይ የሥነፅሁፋዊ ስራዎች ትርጉም ሌሎችና ሰፊ የትርጉም መመዘኛዎችና አካሄዶች ያሉት በመሆኑ እራሱን የቻለ ትልቅ ሞያ ነዉ።
አጠቃላይ የትርጉም ስራ
የሥነፅሁፋዊ ትርጉምን ስናነሳ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂት ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ስላሉት ምናልባት በሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ። ላሁኑ ሥነፅሁፋዊ የሆኑም ይሁን ያልሆኑ ፅሁፎችን ስንተረጉም ባጠቃላይ ምን ምን ሞያዊ ሂደቶችን ልንከተል እንደምንችል ላንሳ።
አንድ ተርጓሚ አንድን ስራ ለመተርጎም ከወሰነ ወይም ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደየ ሁኔታው የሚተረጉምበትን መንገድ መወሰን የራሱ መብት ነው። ከታች ከተዘረዘሩት በአንደኛው መንገድ ሊተረጉም ይችላል። ነገር ግን በሁሉም መንገድ ብቃትንና ሞያዊ መንገድን ተከትሎ መተርጎም ይገባል።
ቀጥታ ትርጉም
ቀጥታ ትርጉም የሚባለዉ ትርጉም በሚሰራበት ምንጭ ቋንቋ - Source Language (SL) የሚገኙ ዐውዳዊ ትርጉሞችና ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ሳይነካኩ ወደ መዳረሻ ቋንቋ - Target Language (TL) መተላለፍ ሲኖርባቸው የሚሰራ ነው። በዚህ የቀጥታ ትርጉም ስር የሚካተቱት ደግሞ የውሰት (Borrowing)፣ የብድር (Calque or loan ) እና የቃል በቃል (Literal) የሚባሉት ናቸው። የመጀመሪያው የውሰት የሚባለው አንድን ቃል ወይም ቃላትን በቀጥታ ከአንድ ቋንቋ የመውሰድና የመጠቀም ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ለአማርኛ ከእንግሊዝኛ ቴሌቪዥን ወይም ካፌ የሚሉትን ቃላት እንደምንጠቀመው። ብዙ ጊዜ ተርጓሚዎች እንደዚህ ማድረግ ያለባቸው አማራጭ ሲያጡ ብቻ እንደሆነ ይገለፃል። ሁለተኛው የብድር ትርጉም የሚባለው ደግሞ በአንድ ቋንቋ ያለን አባባልና ገለፃ እንዳለ በሌላኛው ቋንቋ መተርጎም ነው። ለምሳሌ፡- አንድ በእንግሊዝኛ የሚናገር ሰው ስለ አንድ ንብረት አንስቶ “It is a white elephant"  ቢል እና ተርጓሚው ይህን አባባል “ይሄ ነጭ ዝሆን ነዉ።” ብሎ ቢተረጉመው፣ ትርጉሙ የብድር ትርጉም ይባላል። ይሄ ማለት ግን ተርጓሚው ተናጋሪው ሊለው የፈለገውን ጉዳይ በትክክል ተርጉሞለታል ማለት አይደለም። የእንግሊዝኛ ተናጋሪው እዚህ ጋ ንብረቱ ምንም የማይፈይድ ለታይታ ብቻ የተቀመጠ ነው ማለቱ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ነው ከላይ የተጠቀሰው የፕራግማቲዝም (Pragmatism) እና ሌሎችንም መንገዶች ማሰብ የሚያስፈልገው።
ሶስተኛው የቃል በቃል (Literal) ትርጉም  ደግሞ በአንድ ቋንቋ ያሉ ቃላትን በቃላት ደረጃ እያንዳንዱን በመልቀም ወደ መዳረሻ ቋንቋ መለወጥ ሲሆን ይሄ ትርጉም ይበልጥ ለጥንቃቄ የሚረዳ ሲሆን የትርጉሙን ሁኔታ ግን ባጠቃላይ ባረፍተ ነገር ደረጃ ሊያዛባ ስለሚችል ጥንቃቄ ያሻዋል።
ቀጥታ ያልሆነ (Oblique) ትርጉም
ቀጥታ ያልሆነ (Oblique) ትርጉም የሚባለው  ትርጉም በሚሰራበት ምንጭ ቋንቋ -  Source Language (SL) የሚገኙ ዐውዳዊ ትርጉሞችና ባህላዊ እሴቶች ተለውጠውና ለአንባቢዉ ወይም ለተጠቃሚው  በሚመች ወይም በሚመጥን ደረጃ ወደ መዳረሻ ቋንቋ - Target Language (TL) መተላለፍ ሲኖርባቸው የሚሰራ ነው።
እነዚህ የትርጉም ዓይነቶችTransposition፣ Modulation፣ Reformulation orEquivalence፣ Adaptation እና Compensation የተሰኙ እና ለተርጓሚው ነፃነትን የሚሰጡ አካሄዶችን ያካተቱ ሲሆኑ ተርጓሚው ከሚተረጉመው ስራ የተወሰነውን አንኳር አንኳር ጉዳዮች ወስዶ በራሱ አባባልና ቋንቋ ለራሱ አንባቢ ወይም አድማጭ/ተመልካች የሚያቀርብበት ናቸው።
የሀገራችን ድንቅ ፀሀፌ-ተዉኔት የነበረው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ከላይ የጠቀስኳቸውን “ጥሩ ተርጓሚ” መስፈርቶች ያሟላ ፀሃፊና ተርጓሚ ስለነበር በቀጥታ ትርጉምም ሆነ ቀጥታ ባልሆኑ ትርጉሞች በተለይ በርካታ የሼክስፒር ስራዎችን በድንቅ ብቃት በመተርጎምና በማዘጋጀት በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማድረሱን ትውልድ ሲዘክረው ይኖራል፡፡
በመጨረሻም የትርጉም ሥራ የመጨረሻ ቅጂዎችን አንባቢ ለሆኑ ጓደኞቻችን ከማስነበብ በተጨማሪ የቋንቋ ሞያ ወሳኝ ስለሆነ ሁልጊዜ ለቋንቋ ባለሞያዎች ማሳየት ጥሩ ይመስለኛል። ዝርዝር የቋንቋ ጉዳዮች (Semantics and Lexicogrammar··) እና ሌሎች ሁኔታዎችን በተመለከተ ባለቤቱ የቋንቋ ሰው እንጂ መሃንዲስ ወይም ሳይንቲስት እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡   
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡-   This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2287 times